Monday, 06 April 2015 07:53

ባህርዳር ዩኒቨርስቲና ተመራቂ የርቀት ተማሪዎች እየተወዛገቡ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)
“ህገ መንግስታዊ መብታችንን በቀላጤ ተቀምተናል” ተማሪዎቹ ባለፈው ዓመት የ6 አመት የርቀት የህግ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የአዲስ አበባ ማዕከል ተመራቂ ተማሪዎች፣ “የህግ መውጫ ፈተና” ካልተፈተናችሁ ድግሪያችሁን ማግኘት አትችሉም መባላቸውን በመወቃወም ከዩኒቨርስቲው ጋር እየተሟገቱ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ፤ ከትምህርት ሚኒስቴር የወረደልኝን መመሪያ ነው ተግባራዊ ያደረግሁት ብሏል፡፡ 135 የሚሆኑ ተማሪዎች በፊርማቸው አስደግፈው በተወካዮቻቸው አማካይነት ለዝግጅት ክፍላችን ባቀረቡት መረጃ፤ ለ6 አመት የህግ ትምህርታቸውን በLLB ደረጃ በርቀት ሲከታተሉ ቆይተው ካጠናቀቁ በኋላ በትምህርት ውላቸው ላይ የሌለውን “የህግ መውጫ ፈተና” መውሰድ አለባችሁ እንደተባሉና ካልሆነ ድግሪያቸው እንደማይሰጣቸው ከዩኒቨርሲቲው እንደተገለፀላቸው ጠቁመዋል፡፡ “ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያ ነው” በሚል እያንዳንዳቸው 674 ብር እስከ የካቲት 30 ቀን 2007 ዓ.ም በመክፈል ፈተናውን እንዲወስዱ ሰሌዳ ላይ በተለጠፈ ማስታወቂያ እንደተገለፀላቸው የጠቆሙት ተማሪዎቹ፤ “ይሄ ቀድሞ የማናውቀው መመሪያ፤በህገ መንግስቱ የተሠጠንን መብት የሚያሣጣን ነው” ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ የተመራቂዎቹ ተወካይ አቶ ሙሉጌታ ጉግሣ ለአዲስ አድማስ እንደገለፀው፤ ተመራቂዎች ፈተናውን ይውሰዱ ቢባልና አንድ ተማሪ በፈተናው ቢወድቅ የ6 አመት ልፋቱን ዋጋ ቢስ የሚያደርግ በመሆኑ አመክንዮአዊ አይሆንም ብሏል፡፡ ፈተናውን ለመውሰድ 674 ብር ክፈሉ መባሉም ዩኒቨርስቲው ያለ አግባብ የገንዘብ መሰብሰብ ሥራ ውስጥ የገባ ያስመስለዋል ሲል ተወካዩ አክሎ ገልጿል፡፡ የተማርንበትን የምስክር ወረቀት የማግኘት ህገ መንግስታዊ መብት አለን ያለው አቶ ሙሉጌታ፤ “አሁን ግን ህገመንግስታዊ መብታችንን በአንዲት ደብዳቤ (ቀላጤ) እንደተቀማን እየተነገረን ነው” ብለዋል፡፡ የለፋንበትን ያለቅድመ ሁኔታ የማግኘት መብት በደብዳቤ መቀማት የሚያስችል የህግ ድንጋጌ የለም፤ ቢኖርም ህገ መንግስቱን የሚቃረን ነው ያለው የተማሪዎቹ ተወካይ፤ “በተደጋጋሚ በበላይ አመራሮች በፖሊሲ ደረጃ የተተገበረ አሠራር ነው” የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው ጠቁመው፤ ፖሊሲው ግን ምን እንደሆነ በግልጽ አይታወቅም ብለዋል፡፡ “ይህ የህግ መውጫ ፈተና ፖሊሲ ነው ካሉ ለምን በሚገባ አያረጋግጡልንም” ያሉት ተመራቂዎቹ፤ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች በተመሳሳይ በLLB ለሚያስመርቋቸው የርቀት ተማሪዎች ያለ መውጫ ፈተና ሠርተፊኬታቸውን እየሰጡ መሆኑን በተጨባጭ እናውቃለን፤ ማስረጃም አለን ብለዋል፡፡ “የኛ ከሌላው የሚለየው በምንድን ነው?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ “የህግ መውጫ ፈተና መኖሩን ፈጽሞ አንቃወምም” የሚሉት ተመራቂዎቹ፤ ነገር ግን ፈተናው መዘጋጀትና መሰጠት ያለበት በፍትህ አካላት ነው ሲሉም ሞግተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የርቀት ትምህርት ማስተባበሪያ የፈተና ክፍል ተጠሪ አቶ በለጠ ተክሌን አነጋግረን በሰጡን ምላሽ፤ መመሪያውን መንግስት እንዳወጣውና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ከመንግሥት መመሪያ ውጪ ሊሆን እንደማይችልም ተናግረዋል፡
Read 5061 times