Monday, 06 April 2015 07:44

ሚስቱን በተጋቡ በ2ኛ ወር በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ተፈረደበት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

በድሬደዋ ከተማ ጋብቻ በፈፀሙ በሁለተኛው ወር ሚስቱን በእለታዊ ግጭት ተነሳስቶ በአሰቃቂ ሁኔታ በዱላና በድንጋይ ደብድቦ የገደለው ግለሰብ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተፈረደበት፡፡
ረመዳን ዳዊ አህመድ የተባለው የ40 አመት ጐልማሣ፤ የካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ ከአካባቢው በመሠወር አለማያ ከተማ አጐቱ ጋ ተደብቆ እንደነበር የገለፀው ፖሊስ፤ በክትትል ግለሰቡ ተይዞ ምርመራ  ከተደረገበት በኋላ ክስ የተመሰረተበት ሲሆን ፍ/ቤቱ የቀረበለትን ማስረጃ መርምሮ ግለሰቡን በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
የድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዲቪዢን ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ገመቹ ካቻ፤ ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በሰው አካል ላይ ጉዳት በማድረስና ወንጀለኛን በማስመለጥ የወንጀል ድርጊቶች በፍ/ቤት ቅጣት ተወስኖበት የእስር ጊዜውን ጨርሶ ከማረሚያ ቤት የወጣ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የሟች በአሠቃቂ ሁኔታ መገደልን ተከትሎ የድሬደዋ ነዋሪዎች ሠላማዊ ሠልፍ በማድረግ ወንጀለኛው ተመጣጣኝ ፍርድ እንዲሰጠው መጠየቃቸውን ያስታወሱት ኢንስፔክተር ገመቹ፤ ህብረተሰቡ ወንጀለኛው ከተደበቀበት እንዲያዝ በመጠቆምና መረጃ በመስጠት  ከፍተኛ ትብብር ማድረጉን በመጠቆም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ላይ የነበረችው ሟች ከትዳር በፊት ከሌላ የወለደችው የአንድ ልጅ እናት ነበረች ተብሏል፡፡

Read 2625 times