Monday, 06 April 2015 08:03

የሕፃናት ቊርባን የሥነ ምግብ ባለሙያዎችን አከራከረ

Written by 
Rate this item
(10 votes)
  • ‹‹የሥነ ምግብ ጥናቱ የትኛውንም ሃይማኖት በተለየ የሚመለከት አይደለም›› /አስተባባሪው/
  • ‹‹ሥጋወደሙን ከምግብ መቁጠር ሃይማኖታዊ ነጻነትንና ሥርዓትን የሚፃረር ነው›› /ምእመናን/

   ከውልደታቸው እስከ ስድስት ወራት ዕድሜአቸው ድረስ ያሉ የአገሪቱ ሕፃናት፣ ከእናቶቻቸው ጡት ወተት ውጭ ተጨማሪ ነገር ስለመውሰዳቸው የዳሰሳ ጥናት ለማካሔድ በሚል ለመረጃ ሰብሳቢዎች የተሰጠው ሥልጠና፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሕፃናት ከሚፈጸመው ሥርዐተ ቊርባን አኳያ የሥነ ምግብ ባለሞያዎችን ማከራከሩ ተገለጸ፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥነ ምግብ ዲፓርትመንት ባለፈው የካቲት ወር፣ የሕፃናት ጥቃቅን ንጥረ ምግብ(micro nutrients) እና ተያያዥ የጤና ችግሮችን አስመልክቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ስለሚሰበሰቡ መረጃዎች ለሦስት ሳምንት የዘለቀ ሥልጠና በሰጠበት ወቅት፣ ‹‹አንድ ሕፃን እስከ ስድስት ወር ዕድሜው ድረስ ሥጋወደሙን ወይም ቁርባን ከተቀበለ  የእናቱን ጡት ወተት ብቻ እንደተመገበ (exclusive breast feeding) አንቆጥረውም፤ እንደ ተጨማሪ ምግብ ነው የምናየው፤›› በሚል በጥናቱ አስተባባሪ የተነሣው ሐሳብ ብዙዎቹን አጥኚዎች ክፉኛ እንዳከራከረ የሥልጠናው ተሳታፊዎች ይናገራሉ፡፡
አንድ ሕፃን ከልደቱ እስከ ስድስት ወር ድረስ መመገብ ያለበት በበቂ ንጥረ ነገሮች የበለጸገውንና በተስማሚነቱ መተኪያ የሌለውን የእናት ጡት ብቻ እንደኾነ በሕክምና ሳይንሱ ይመከራል፤ ይህም ተጨማሪ ምግብና ፈሳሽ ለመውሰድ የሕፃኑ ጨጓራና አንጀት ዝግጁ ባለመኾኑና ለጤና እክልም እንዳይጋለጥ በሚል እንደኾነ የሚያስረዱት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ተከታይ ባለሞያዎቹ፣ በሥርዓተ እምነታቸው ዕድሜ እና ጾታ ሳይለይ የአምላክ አማናዊ ሥጋ እና አማናዊ ደም እንደኾነ አምነው የሚቀበሉት ቅዱስ ቊርባን፤ ‹‹ተጨማሪ›› በሚል በሚሰበሰበው መረጃ ለማካተት መታሰቡንና ከሥነ ምግብ አንጻር መታየቱን በጥብቅ እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡
በሕክምናው ስድስት ወራት ያልሞላቸው ሕፃናት ሲታመሙ ሽሮፕ ወይም ክኒን እንዲሟሟ ተደርጎ ለተወሰነ ጊዜ መድኃኒት እንደሚሰጣቸውና ይህም ለመዋዕለ ዘመናቸው የተወሰነውን የእናት ጡት ወተት ብቻ የመመገብ ሥርዓት ያፈርሰው እንደኾነ ለአስተባባሪው ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ባለሞያዎቹ፣ ‹‹በሐኪም ትእዛዝ ከኾነ ችግር የለውም፤ ሥርዐተ ምግቡን አያፈርሰውም ተብሎ ነው የሚታሰበው፤ ቁርባን ከወሰደ ግን ያፈርሰዋል›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ ይህም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚታመንበት የሥርዐተ አመጋገቡ መግለጫ እንደኾነ ተነግሮናል የሚሉት ባለሞያዎቹ፣ ከሚመለከታቸው የሚኒስቴሩ አካላት ለማረጋገጥ ሲጠይቁ ግን ‹‹በዚኽ ጉዳይ መልስ መስጠት አልፈልግም›› እንደተባሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሕፃናት ጤና አጠባበቅ ከአህጉሩ በቀዳሚነት ለምትጠቀስበት ስኬቷ፣ በሥርዓተ ሃይማኖቱ በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሕፃናት የሚፈጸመው ቊርባን ዕንቅፋት ይኾናል ብለው እንደማያምኑ ባለሞያዎቹ ይናገራሉ፡፡ በእምነቱ የተቀደሰ ትውፊት ከስድስት ወራት በፊት ያሉ ሕፃናትንም ቢኾን ማቁረብ ለመንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ ዕድገታቸው የመጨነቅ የጥሩ እናትነት ምልክት መኾኑን የሚያስረዱት ባለሞያዎቹ፣ በብዙ ሚልዮን የሚገመቱት ክርስቲያን ሕፃናት እስከ ስድስት ወራቸው ድረስ የእናት ጡት ወተት ብቻ የማይመገቡበት አንዱ ምክንያት ‹‹ስለሚቆርቡ ነው›› የሚል ድምዳሜ በዳሰሳ ጥናቱ እንደ አንድ ነጥብ ቢቀመጥ ለአገር የሚያሰጠው ገጽታ ከወዲኹ መጤን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ሥርዓተ ቊርባን፣ ሕፃናት በተወለዱ ከ40 እና ከ80 ቀናቸው ጀምሮ የሚቀበሉትና ከአምላካቸው ጋር ያላቸውን አንድነት የሚያረጋግጡበት የእምነታቸው አክሊልና ፍጻሜ ነው ያሉት ባለሞያዎቹ፣ ከስድስት ወራት በፊት ያሉ ሕፃናትን አመጋገብ ያፈርሳል የሚለው የጥናቱ ውጤት በሒደት የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት መርሐ ግብር አካል ተደርጎ ሊሠራበት ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አልሸሸጉም፡፡ ይህም የሃይማኖት ነጻነትን የሚጋፋ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፣ የምእመናኑን መንፈሳዊ ሕይወት የሚያጠፋና የሚደመስስ፣ እንዲኹም ለባዕድ አስተሳሰብም አሳልፎ የሚሰጥ በመኾኑ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደማይኖረውና በጽኑ እንደሚያወግዙት ገልጸዋል፡፡
‹‹መረጃውን ለእናንተ ከነገሯችኹ ሰዎች በላይ ለምንሠራው ሥራ ሓላፊነት ይሰማናል›› ያሉት በኢንስቲትዩቱ የሥነ ምግብ ዲፓርትመንት የሥልጠናው አስተባባሪ ለአዲስ አድማስ በስልክ እንደተናገሩት፣ ጥናቱ የተወሰነ ሃይማኖትን የሚመለከት አይደለም፤ ዓላማውም ምን ያኽል ሕፃናት እስከ ስድስት ወር ድረስ የእናት ጡት ብቻ ወስደዋል የሚለውን ለማወቅ ብቻ በመኾኑ ከሃይማኖት ጋራ የሚያያዝ ትንታኔ የሚሰጠበት አይደለም፡፡
‹‹ለሕፃኑ ከውልደቱ ጀምሮ እስከ ስድስት ወሩ ድረስ ከእናት ጡት ውጭ የተሰጠው ማንኛውም ነገር አለ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ‹‹በሃይማኖት ሥርዓትም ቢኾን›› በመረጃ ሰብሳቢዎቹ መጠየቅ እንዳለበት በሥልጠናው ላይ በአጽንዖት መነገሩን የሚጠቁሙት አስተባባሪው፤ በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ለሕፃናት ከሚፈጸመው ቁርባን አንጻር ከአንድ ተሳታፊ ጥያቄ መነሣቱን አረጋግጠዋል፡፡
‹‹በሃይማኖት ሥርዓትም ቢኾን ብለን ጥያቄ ስንጠይቅ ኦርቶዶክስ ሊኾን ይችላል፤ ሙስሊም ሊኾን ይችላል፤ ባዕድ አምልኮ የሚከተል ሊኾን ይችላል፤ እኛ እርሱ አይደለም የሚያሳስበን፤ በሃይማኖታዊ ሥርዓትኮ ሥጋወደሙ ብቻ አይደለም፤ ልጆች ሲታመሙ ጠበልም ምንም በተከታታይ አብዝቶ ይሰጣል፤ ይህም ኾኖ ወላጆች የእናት ጡት ብቻ ነው የመገብነው ይላሉ፤ ጤና አዳም ውኃ ውስጥ አድርገው ይሰጡና ምንም አልሰጠንም ይላሉ፡፡ በዚኽ ኹኔታ የጤና ችግር የሚያጋጥማቸው ሕፃናት ይኖራሉ፤ ከኦርቶዶክስ እምነት ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፤ ነገሩ ተገቢው ግምት ስለማይሰጠው በየትኛውም ሃይማኖት የሰጣችኹት ነገር አለ ወይ? ብለን እንጠይቃለን፡፡ ጥያቄው እንዲኽ ያሉ ነገሮችን ለማስተካከል ነው፤ ምክንያቱም አገሪቱ የሕፃናት ሕመምና ሞት መጠንን ማሻሻል ብትችልም የሚፈለገውን ያኽል መሔድ አልተቻለም፡፡ ስለዚኽ በሃይማኖታዊ ሥርዓትስ የሰጣችኹት ነገር የለም ወይ? ምን? የሚል ጥያቄ በመጠይቁ ተካትቷል፤›› ሲሉ አስተባባሪው አስረድተዋል፡፡  

Read 8463 times