Monday, 06 April 2015 09:02

አሜሪካ ለግብጽ ወታደራዊ ድጋፍ መስጠቷን ልትቀጥል ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   አሜሪካ ለግብጽ ስትሰጥ የቆየችውንና ለሁለት አመታት ያህል አቋርጣው የነበረውን ወታደራዊ ድጋፍ እንደገና ሙሉ ለሙሉ መስጠት ልትጀምር እንደሆነ ማስታወቋን ዋሽንግተን ፖስት ዘገበ፡፡ የኦባማ አስተዳደር ለግብጽ ሲሰጠው የቆየውንና ከ2013 ጥቅምት ወር ወዲህ አቋርጦት የነበረውን 1.3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት አመታዊ የወታደራዊ መሳሪያዎች ድጋፍ እንደገና ለመጀመር ውሳኔ ላይ መድረሱን ባለፈው ክሰኞ አስታውቋል፡፡የግብጹ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሙርሲ ከስልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ፣ አገሪቱ እስከምትረጋጋና ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ተጨባጭ ለውጥ እስኪታይ ድረስ፣ አሜሪካ ለግብጽ የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ አቋርጣ መቆየቷን ዘገባው አስታውሷል፡፡ የአሜሪካ መንግስት ወታደራዊ ድጋፉን እንደገና ለመስጠት መወሰኑ፣ ግብጽን ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ አሜሪካ ሰራሽ የወታደራዊ መሳሪያዎች ባለቤት ያደርጋታል ያለው ዘገባው፣ ላለፉት ሁለት አመታት በአሜሪካ እጅ የቆዩ 12 ኤፍ-16 ተዋጊ ጀቶችን፣ 20 ቦይንግ ሃርፖን ሚሳየሎችን፣125 አሜሪካ ሰራሽ አብራምስ ኤምዋንኤዋን ታንኮችንና ሌሎች መሳሪያዎችን ማግኘት እንደሚያስችላት የአሜሪካ ብሄራዊ የደህንነት ካውንስል ቃል አቀባይ በርናዴት ሜሃን መናገራቸውን ጠቁሟል፡፡  አሜሪካ ወታደራዊ ድጋፉን እንደገና ለመቀጠል የወሰነችው፣ የራሷን የብሄራዊ ደህንነት ፍላጎት መሰረት በማድረግ ነው ያሉት ቃል አቀባይዋ፣ ለግብጽ የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ በተለይ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት፤ የድንበርና የባህር ደህንነቶችን ለማስጠበቅና አይሲሲ የተባለው ታጣቂ ቡድን በሲናይ አካባቢ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲውሉ በሚያስችል መልኩ ማሻሻሏንም አስታውቀዋል፡፡ ኦባማ ክግብጹ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ 1.3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን ወታደራዊ ድጋፍ በዘላቂነት ለማስቀጠል ለአሜሪካ ምክር ቤት ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ቃል ገብተዋል፡፡ ግብጽ ከ2018 ጀምሮ የጦር መሳሪያዎችን በብድር መግዛቷን ማቆም እንደሚገባት አሳስበዋቸዋል፡፡አልጀዚራ በበኩሉ፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት አሜሪካ ለግብጽ ሙሉ ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት መወሰኗ እንደሚያሳስባቸው መግለጻቸውን ጠቅሶ፣ ሂውማን ራይትስ ፈርስት የተባለው ተቋም ዳይሬክተር ኔል ሂክስ “አሜሪካ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለሚታዩባት ግብጽ ድጋፏን ለመቀጠል መወሰኗ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቅድሚያ አትሰጥም የሚል አደገኛ መልዕክት ሊያስተላልፍ ይችላል” ማለታቸውን ዘግቧል፡፡አሜሪካ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወር ለግብጽ የምትሰጠውን ድጋፍ በከፊል እንደምትጀምር ማስታወቋን ያስታወሰው ዘገባው፣ ግብጽ ከአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ በማግኘት ከእስራኤል ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም ጠቁሟል፡፡

Read 2429 times