Tuesday, 14 April 2015 07:50

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓመቱ ምርጥ ሽልማትን አገኘ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

     የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቻይና በየአመቱ በሚካሄደው “ኢንደስትሪ ጎልደን ቼር አዋርድስ” በተሰኘ አለማቀፍ ሽልማት የዓመቱ ምርጥ አየር መንገድ ተብሎ ለሁለተኛ ጊዜ መሸለሙን አስታወቀ፡፡
አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ ለስምንተኛ ጊዜ በተካሄደውና በአለማቀፍ ደረጃ የላቀ አፈጻጸም ያሳዩ አየር መንገዶች፣ ሆቴሎች፣ የጉዞ ወኪሎችና የቱሪዝም መዳረሻዎች በሚሸለሙበት በዚህ ዝግጅት ተሸላሚ መሆኑ እንደሚያኮራቸው ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ተናግረዋል፡፡
ሽልማቱን ለሚያዘጋጀው ኤምአይሲኢ የተባለ መጽሄት፣ እንዲሁም ለአየር መንገዱ ድምጻቸውን በመስጠት ለተሸላሚነት ላበቁት የቻይና ደንበኞችም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዘመናዊዎቹና በምቹዎቹ 787 እና 777 አውሮፕላኖቹ ቻይና ውስጥ ወደሚገኙት የቤጂንግ፣ የሻንጋይ፣ ጉዋንግዡና ሆንግ ኮንግ መዳረሻዎች በየሳምንቱ በድምሩ 28 በረራዎችን በማድረግ ምርጥና ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው የፈረንጆች አመት ኤር ትራንስፖርት ወርልድ በተባለው ታዋቂ የአቪየሽን ዘርፍ መጽሄት “ቤስት ሪጅናል ኤርላይን” የተሰኘ ሽልማት የተሰጠው አየር መንገዱ፣ ባለፈው አመትም ከአሜሪካ ታዋቂ የጉዞ መጽሄቶች አንዱ በሆነው ፕሪሚየር ትራቭለር “የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ” ተብሎ መሸለሙንም መግለጫው አስታውሷል፡፡ በ “ፓሴንጀር ቾይዝ” እና በአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበርም፣ “ቤስት ኤርላይን ኢን አፍሪካ” እና “አፍሪካን ኤርላይን ኦፍ ዘ ይር” ሽልማቶችን መሸለሙንም አክሎ ገልጿል፡፡

Read 2397 times