Tuesday, 14 April 2015 07:52

በፋሲካ ገበያ የሸቀጦች ዋጋ ጨምሯል

Written by 
Rate this item
(8 votes)

     በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መቀነሱን ተከትሎ በትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ላይ ቅናሽ ቢደረግም በፋሲካ ገበያ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ሸማቾችና ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡
የአዲስ አድማስ ሪፖርተሮች በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ የገበያ ስፍራዎች ተዘዋውረው ባደረጉት ቅኝት፤ ሠንጋ በሬዎች ከ8ሺህ እስከ 17 ሺህ ብር ሲሸጡ፣ የፍየል ዋጋ ከዓምናው የፋሲካ በአል የ300 ብር ጭማሪ በማሳየት ከ2ሺ 4500 ብር እየተሸጠ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የበግ ዋጋ በሾላ ገበያ ትንሹ 1500 ብር፣ መካከለኛው እስከ 1800ብር እንዲሁም ትልቁ  እስከ 3500 ብር ሲሸጥ፣ በሣሪስና ጐተራ አካባቢ ትንሹ እስከ 1800 ብር፣ መካከለኛው 2500 ብር፣ ትላልቅ የሚባሉት ደግሞ እስከ 4000 ብር የሚገኙ ሲሆን መሲና የሰቡ ሴት በጐች ከ2200 እስከ 3ሺህ ብር እየተሸጡ ነው፡፡
በሾላ ገበያ የሚገኘው የከብቶች መሸጫ ቦታ በመንግስት በመውሰዱ፣ ሰሞኑን ነጋዴዎች ከደንብ አስከባሪዎች ጋር እየተሳደዱ በየመንገዱ ሲሸጡ የነበረ ሲሆን ከከተማው ርቆ በሚገኘው የካራ ገበያ እንዲጠቀሙ ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡ የካራ የገበያ ቦታ ግን ደንበኞቻቸውን ለማግኘት ምቹ ባለመሆኑ በየመንገዱ ለመሸጥ መገደዳቸውን ነጋዴዎቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በከተማዋ ያሉ አንዳንድ እንቁላል አቅራቢ ድርጅቶች አንዱን እንቁላል በ2.50 ብር ሂሳብ ሲሸጡ፣ በየአካባቢው ያሉ ሱቆችና መደብሮች ደግሞ ከ3.00 ብር እስከ 3.50 እየሸጡ ይገኛሉ፡፡ የእንቁላል ዋጋ ከዓምናው የትንሳኤ በዓል ከ1.00 ብር እስከ 1.75 ብር ድረስ ጭማሪ ማሳየቱንም ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናግረዋል፡፡
ሽንኩርት በኪሎ ከ12.00 ብር እስከ 12.50 ብር እየተሸጠ ሲሆን ከወትሮው ገበያ እምብዛም የዋጋ ለውጥ እንዳልታየበትና ካለፈው ዓመት ጋርም ተመሳሳይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የቅቤ ዋጋ በአሉን ተከትሎ የጨመረ ሲሆን በአብዛኞቹ ገበያዎች 1ኛ ደረጃ የሚባለው ቅቤ 185 ብር በኪሎ ሲሸጥ፣ ከዚያ በታች የሆኑት ከ165 እስከ 175 ብር በኪሎ እየተሸጡ ነው፡፡
ሳሪስ አካባቢ የበዓል ሸቀጦች ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወ/ሮ ፀዳለ ይልማ፤ የትራንስፖርት ዋጋ መቀነሱን ተከትሎ የበዓል ሸቀጦች ዋጋ ቅናሽ እንደሚያሳይ ገምተው እንደነበር ጠቁመው ሆኖም እንደገመቱት ሳይሆን መቅረቱን ተናግረዋል፡፡
ጎተራ መስቀል ፍላወር አካባቢ በጎች ሲሸጥ ያገኘነው ጉልማ ዳዲ፤የበግ ዋጋ ከወትሮው የጨመረው ገበሬው ዋጋ በመጨመሩ ነው ብሏል። ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው ፍቼ በጎቹን እንደሚያመጣ የጠቆመው ነጋዴው፤ ገበሬው ካለፈው የገና በዓል በኋላ እንኳ በአንድ በግ ከ150 እስከ 200 ብር ጭማሪ ማድረጉን ገልጿል፡፡
በሾላ ገበያ አስፓልት ዳር በጎቹን ሲሸጥ ያገኘነው ነጋዴም ከደብረ ብርሃንና ለአዲስ አበባ ቅርብ ከሆኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች በጎች እያመጣ እንደሚሸጥ ጠቁሞ፤ ገበሬው ከ200 እስከ 300 መቶ ብር የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን ተናግሯል፡፡ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የበሬ ነጋዴዎች በበኩላቸው፤ በበሬ ዋጋ ላይ ካለፉት በአላት እምብዛም የዋጋ ጭማሪ አለመስተዋሉን ገልፀዋል፡፡
በበአላት ወቅት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚዘጋጁ የጐዳና ላይ የንግድ ባዛሮች  እንደ አንድ የገበያ አማራጭ የሚታዩ ቢሆንም በዋጋ አንፃር ከመደበኛ የገበያ ስፍራዎች ብዙም ለውጥ እንደሌላቸው ሸማቾች ይናገራሉ። ኢንተርፕራይዞቹ ከመንግስት ነፃ የንግድ ቦታ የተመቻቸላቸው እንደመሆኑ ዋጋቸው ከፍተኛ ግብር ከሚከፍሉት ነጋዴዎች እኩል መሆን አልነበረበትም የሚሉት ሸማቾች፤ ለመንግስት ግብር ሣይከፍሉ ህብረተሰቡን በዋጋ መበዝበዛቸው ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
በለገሃር አካባቢ በተዘጋጀው የንግድ ባዛር ላይ ጫማ ሲገዙ ያገኘናቸው አንድ ሸማች፤ በመደበኛ ቡቲኮች ከ250 እስከ 400 ብር የሚሸጡ ጫማዎች በባዛሮቹም ላይ በተመሳሳይ ዋጋ ሲሸጡ መታዘባቸውን ጠቁመዋል፡፡ የአልኮል መጠጦችም በተመሳሳይ በግሮሰሪዎች ከሚሸጡበት ዋጋ ምንም ለውጥ እንደሌላቸው ሸማቾች ጠቅሰው፤ ባዛሮቹ በመንግስት ድጋፍ የሚዘጋጁ እንደመሆናቸው ዋጋቸው ቅናሽ ማሳየት ነበረበት ብለዋል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ነጋዴዎች በበኩላቸው፣ እንዲህ ያለውን ዕድል የምናገኘው በዓመት ውስጥ ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ በመሆኑ ቅናሽ ማድረግ አያዋጣንም ብለዋል፡፡

Read 3608 times