Tuesday, 14 April 2015 08:31

ሰሙነ ሕማማትና ምስጢሩ

Written by  ተመስገን ዘገየ (ከአዲስ አበባ)
Rate this item
(9 votes)

     ከትንሣኤ በፊት ያለው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ ይኸውም በነቢዩ ኢሳይያስ፤ “ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማምነ፤” በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንም ተሸከመ፤ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን። (ኢሳ.5፤34-36) ተብሎ በመንፈስ ቅዱስ ትንቢት የተነገረው ቃል ተፈጸመ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ሳምንት ውስጥ ለድኅነት ዓለም ሲል በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ ለማስታወስ የወጣ ስያሜ ነው፡፡  
በሰሙነ ሕማማት መስቀል መሳለምና እርስ በእርስ መሳሳም የለም፡፡ ይህም ይሁዳ ጌታን በመሳም አሳልፎ እንደሰጠው ለማሰብ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ውስጥ ያሉት ዕለታት ስያሜያቸውና በየእያንዳንዳቸው ዕለታት የተፈፀሙትን ድርጊቶች እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡
ሰኞ፡- አንጽሖተ ቤተ መቅደስና መርገመ በለስ የተፈፀመበት ዕለት ነው፡፡ የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ ያድራል፡፡ በማግስቱም ከቢታንያ ሲመጣ ተራበ “ወበሳኒታ ወፂኦ እምቢታንያ ርኅበ ወርእየ በለሰ እምርሑቅ ወባቲ ቁጽለ ወሖረ ይርአይ እመቦ ዘይረክብ ፍሬ በውስቴታ ፀበጺሖ ኅቤሃ አልቦ ዘረከበ ዘእንበለ ቁጽል ባሕቲቱ እስውመ ኢኮነ ጊዜሁ ለበለስ” ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ ዓይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳችም ፍሬ አላገኘባትም፤ “ወአውሥኦ ወይቤላ ለዓለም አልቦ ዘይበልዕ ፍሬ እምኔኪ እንከ” ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረግማት፡፡ (ማር. 11፤11-12)
በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፡፡ ፍሬ የተባለች ሃይማኖት ምግባር ናት፡፡ ከእስራኤል ፍቅርን ሃይማኖትን ምግባርን ፈለገ አላገኘም፡፡ እስራኤል ሕዝበ እስራኤል መባል እንጂ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡ በመርገም ምክንያት እርሱ ከላያቸው በስተቀር ደግ ሰው ጠፋባት፡፡
አንድም በለስ ኦሪት ናት፡፡ በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፡፡ ሕገ ኦሪትን ከመፈፀም በእሷ ድኅነት አላደረገባትምና ፍሬ በአንቺ አይሁን አላት፡፡ ድኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደ መድረቅ አለች፡፡
አንድም በለስ ኃጢአት ናት፡፡ የበለስ ቅጠል ሠፊ እንደሆነች ኃጢአትም በዚህ ዓለም ስፍራ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፡፡ ኃጢአትም ሲሠሩት ደስ ያሰኛል፡፡ ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ ወደ እርሷ ሄደ ማለትም ከኃጥአን ጋር ዋለ፤ ኃጥአ ከመባል በቀር በመዋዕሉ ኃጢአት አለመሥራቱን ለመመልከት ፍሬ አላገኘባትም አለ። በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም በኃጢአት በፍዳ ተይዞ የሚቀር  አይኑር ለማለት ነው፡፡ ስትረገም ፈጥና መድረቋም በአዳም በደል ያገኛትን እዳ በደል በእርሱ እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡
በመቀጠልም ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፡፡ ቤተ መቅደስ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምሲያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው “ቤትየሰ ቤተ ጸሎት፣ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች።
እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት” ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው፤ ገርፎም አስወጣቸው፡፡ /ማር 11፤17-19/ ይህም የሚያሳየው ማደሪያ ቤቱ የነበርን የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን፣ ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን ነው፡፡
በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፣ በሠለስት፣ በስድስት ሰዓትና በተሰዓቱ ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱና ሲፀልዩ ይሰነብታሉ፡፡ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፡፡ ምክንያቱም የደረሰበትን መከራ፣ ኅዘኑንና 5500 ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ሕይወት ይኖር እንደነበር ለማዘከር ነው፡፡
ማክሰኞ፡- የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ሰኞ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት በዚህ ዕለት ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና፡፡
ጥያቄውም “ከምድራውያን ነገሥታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታት በማን ሥልጣን ታደርጋለህ?” የሚል ነበር፡፡ “ይህንስ ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ወይስ ከሰው?” አላቸው፡፡ እነርሱም ከሰማይ ነው ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም? ይለናል፡፡ ከሰው ነው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል፤ እንደ መምህርነቱም ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን ተባብለው “ወዴት እንደሆነ አናውቅም” ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም “በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ እኔም አልነገራችሁም” አላቸው፡፡ ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም። ልቡናቸው በክፋትና በጥርጣሬ ስለተሞላ ነው እንጂ። ከዚህ የምንማረው የእነሱን ክፉ ጠባይና ግብር መከተል እንደማይገባን ነው፡፡ በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስም ረጅም ትምህርት ስላስተማረ የትምህርት ቀንም ይባላል፡፡ ይኸውም ከሃይማኖት የራቁትን፤ ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን አስተምሮ ማቅረብ፣ መክሮ መመለስ እንደሚገባ ሲያስተምር ነው፡፡
ረቡዕ፡- ይህ ዕለት የምክር ቀን ይባላል፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር የጀመሩበት ወይም የያዙበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት በመሆኑ፣ ብዙው ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ፣ ተአምራቱን የሚያደንቁ ስለነበር ሁከት እንዳይፈጥር ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀመዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ /ማቴ.26፤1-5፣ ማር.14፤1-2/
የሐዲስ ኪዳን ካህናት ምእመናን በዚህ ዕለት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ከእህልና ውኃ ተለይተው፣ መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው፣ የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ፣ ስለዚህ የሚያወሳውንም በማንበብ፣ እስከ ኮከብ መውጫ በጾም፣ በፀሎትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡
ይሁዳ ማለት ታማኝ ማለት ቢሆንም እንደስሙ ግብሩ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ስምና ግብሩ አልተባበረለትም፡፡ እኛስ እንደ ስማችን ይሆን ግብራችን?
መልካም መዓዛ ያለው ቀንም ይባላል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት “ከእንግዲህ በኃጢአት ተጐድቶ ይኖረ የነበረውን ሕይወቴን እንደዚሁ መልካም ሽቶ የሚያጣፍጥ፣ ኃጢአትን ይቅር የሚል አምላክ መጣ” ስትል ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የሞላ ሽቱ ይዛ በመሄድ በጠጉሩ /በራሱ/ ላይ በማርከፍከፍ ስላቀረበች ነው፡፡
የእንባ ቀንም ይባላል፡፡ ይህም ይህችው ሴት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና፡፡ /ማቴ.26፤6-13፣ ማር.14፤3-9፣ዮሐ.12፤1/ ከዚህም እያንዳንዳችን ልንማር የሚገባን ነገር አለ፡፡ ይኸውም የራስን ኃጢአት በማሰብ ማልቀስና የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ ለእግዚአብሔር ማቅረብን ነው። ሐሙስ፡- ከስቅለትና ከትንሣኤ በፊት ያለው ሐሙስ በቤተክርስቲያናችን የተለያዩ ስያሜዎች አሉት፡፡
ሕጽበተ እግር ይባላል፡፡ ይህ ስያሜ የተሰጠው ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ለማስታወስ ዛሬ ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳት፤ “በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝቡን ኃጢአት እጠብ” ሲሉ በቤተ ክርስቲያናችን የተገኙትን ምእመናን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ሲያጥቡ ያረፍዳሉ፡፡ /ዮሐ.13፤4-15/
የጸሎት ሐሙስ ይባላል፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚደክም ሥጋን የተዋሐደ አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን ለመግለጽና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ በጌቴ ሴማኒ ሲፀልይ በማደሩ ምክንያት ነው፡፡ /ማቴ.26፤36፣ ዮሐ.17፤1/
የምስጢር ቀንም ይባላል፡፡ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷል። ይኸውም “ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፤ እንካችሁ ብሉ፡፡”ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ “ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ፡፡” በማለት እኛ ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበትን መንገድ ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ የሚቀደሰውም በለሆሳስ ሲሆን እንደ ቃጭል በመሆን የሚያገለግለውም ጽናጽል ነው፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ ሲመጡ ድምጻቸውን ዝግ አድርገው በለሆሳስ እየተነጋገሩ መምጣታቸውን ለማሰብ ነው። በቅዳሴውም ኑዛዜ አይደረግም፡፡ ሥርዓተ ቁርባን ግን ይፈጸምበታል፡፡ ይህም ጌታችን የሰጠውን ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ለማሰብ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ተዘጋጅቶ፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይኖርበታል፡፡
የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡ ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳ ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው።                 /ሉቃ.22፤18-20/ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚሆን የአዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱም ጠጡ” በማለቱ ይታወቃል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት መሆኑን በማሰብ፣ የቃል ኪዳኑ ፈጻሚዎች ጠባቂዎች መሆን እንደሚገባን እንማራለን፡፡
የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡፡ ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ራሱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር፤ “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆቼ ግን ብያችኋለሁ” በማለቱ /ዮሐ.15፤15/ ከባርነት ነጻ የወጣንበት ቀን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከኃጢአት ባርነት በመራቅ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት፣ ሕይወቱን በቅድስና መምራት ይኖርበታል፡፡ እርሱ ጠላቶቹ ስንሆን ወዳጆቹ አድርጐናል፡፡ /ማቴ 24፤17-19/
6. አረንጓዴው ሐሙስም ይባላል፡፡ ይህም ጌታችን
  መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአትክልት ቦታ
   ስለጸለየ ነው፡፡
ዕለተ ዓርብ፡- /የስቅለት ቀን/ ስቅለት፣ መስቀል፣ መሰቀል፣ አሰቃቀል ማለት ነው፡፡ መስቀል በቁሙ መስቀያ፣ መመዘኛ፣ መሰቀያ፣ መንጠልጠያ፣ ለሞት የሚያበቃ መከራ፡፡ በማር 8፤34፤ “ወደውፆሙ ለሕዝብ ምስለ አርዳኢሁ ወይቤሎሙ ዘይፈቅድ ይፀመደኒ ይድልአ ለነፍሱ ወያጥብዕ ወይፀር መስቀል ሞቱ ወይትልወኒ” ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ሕዝቡን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ” ይላል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በ1ኛ ቆሮ፣ 1፡17 ላይ፤ “ወኢኮነ በጥበበ ነገር ከመ ኢንሰዐር መስቀሎ ለክርስቶስ” የክርስቶስን መስቀሉን ከንቱ እንዳናደርግ ነገርን በማራቀቅ አይደለም… ይላል፡፡
ጌታችን በተሰቀለ ዕለት ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፡፡ /ፀሐይ ጨለመ/፣ እነሆም የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ ተኝተውም ከነበሩት ቅዱሳን ብዙ ሥራዎችን ተነሱ፤ ከትንሳኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ለብዙዎች ታዩ፡፡ /ማቴ.27፤51/
ጌታችን ለዓለሙ ያሰበውን ቤዛነት ሊፈጽም በመስቀል ላይ መሰቀሉ የሚታሰብበት ነውና ለስቅለቱ መታሰቢያ የሚሆን አጎበር ተዘጋጅቶ፣ ከርቤ እየታጠነ፣ ስቅለቱን የሚመለከቱ ምንባባት በወርድ ሲነበቡና ሲሰገድ ይዋላል፡፡ የሰው ልጅ በሙሉ በእግረ አጋንንት ረግጦ፣ ከፈጣሪው ተጣልቶ ለ5500 ዘመን በጨለማ መኖሩን ለማስታወስም መንበሩ ታቦቱ በዚህ ቀን በጥቁር ልበስ ይሸፈናሉ፡፡ /ወያለብሱ ታቦተ ልብሰ ጸሊመ/ ዲያቆኑም በቤተ ክርስቲያን በመዞር የሚያሰማው የቃጭል ድምጽ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅሶ፣ አንድም ዋና ዋና እያሉ የተከተሉት የኢየሩሳሌም ሴቶችን መሾም ምሳሌ ነው፡፡ /ሉቃ. 23፡31/
ቀዳም ሹር፡- የስቅለት ማግስት የሚውለው ቅዳሜ ወፍጮ ስለሚፈጭበትና ሌላም ለፋሲካ የሚኾን ሥራ ስለሚሰራበት ቅዳሜ ሹር /የተሻረ ቅዳሜ/ ተባለ፡፡ ምስጢሩ ግን ክርስቲያኖች በዘመነ ሐዲስ በቅዳሜ ፈንታ እሑድን ማክበራቸውን ያሳያል፡፡ ይኸውም የተጀመረው በታላቁ ቆስጠንጢኖስ ዘመን ነው፡፡
ቀዳም ሥዑር በጾም፡- የተሻረ ጾም ውሎ የሚያድርበት የአክፍሎት ቀን ማለት ነው። /መዝ. 88፤44/ “ወሠዐርኮ እምንጽሑ፣ ከንጽሕናውም ሻርከው እንዲል ቅዱስ ዳዊት”
ቅዳም ሥዑር፡- የለመለመ ዕለት ቄጤማና ግጫ የሚታደልበት /መዝ. 22፡2  “ውስተ ብሔር ሥዑር ሕየ የኅድረኒ፣ በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፡፡ ቄጤማ በረግረግ ቦታ ላይ የሚበቅል ለምለም ሣር ነው፡፡ “በውኑ ደንገል ረግረግ በሌለበት መሬት ይበቅላልን? ወይስ ቄጤማ ውኃ በሌለበት ቦታ ይለመልማል?” /ኢዮብ 8፡11/ ግጫ እንግጫ የእንቁጣጣሽ ሣር ወይም በበዓል ጊዜ ቤት ውስት የሚጎዘጎዝ፡፡ /ኢሳ.19፡5/
በዕለተ ዓርብ ነፍሳት ከሲኦል ወጡ፡፡ አንቀጸ ገነት ተከፈተልን፣ ርስተ መንግስተ ሰማያት ተመለሰችልን፤ አባታችን አዳምም ከፈጣሪው ጋር ታረቀልን በማለት “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃዶ” እያልን የተድላ፣ የደስታ ምልክት ወይም መገለጫ የሆነ ልምላሜ ያለውን ቆጽለ ሆሣዕና ወይም ቄጤማ ግጫ ይዘን የምስራች እንባባላለን፡፡ /ኤፌ.2፡14-15/ “ወዘእንበለ ምሳሌሰ ኢተናግሮሙ፣ ያለ ምሳሌ አልተናገረምና እንዳለ /ማቴ 13፡34-35/ በኖኅ ጊዜም ርግብ “ሐጸ ማየ አይኅ፣ ይትባ ማየ አይኅ፣ የጥፋት ውኃ ጎደለ፣ አለቀ እያለች     ቆጽላ ዕፀ ዘይት ይዛ ለኖኅ አብስራዋለች፡፡ /ዘፍ. 8፡8-11/
ርግብ የካህናት፣ ኖኅ የምእመናን፣ ኖኅ እጁን ዘርግቶ ርግብን እንደተቀበላት ካህናትም በየመንደሩ እየዞሩ “ክርስቶስ ተመረመረ፤ ዲያብሎስ ታሰረ” በማለት ቄጤማ ሲያድሉ፤ ምእመናንም እጃቸውን ዘርግተው መቀበላቸው የዚህ ምሳሌ ነው፡፡
ስለዚህ አሁንም ቢገኝ የወይራ ልምላሜ ቢታጣ ግጫን እየታደልን የምሥራች መባባላችን ነፍሳት ከሲኦል ለመውጣታቸው መታሰቢያ ነው፡፡ ይህን ቆጽላ ልምላሜ ይዞ ተድላ፣ ደስታ መግለጽ ከጥንት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣ ነው እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ለዚህ በመጀመሪያዪቱ ቀን ከበጎ እንጨት ፍሬን፣ የሰሌንና የተምር ዛፍ ልምላሜ ይዛችሁ በየዓመቱ ሰባት ቀን ተድላ፣ ደስታ ታደርጋለችሁ ብሏል፡፡ /ዘሌ. 23፡40-44/
በሰሙነ ሕማማት ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችን የምታደርገው ትውፊት የሐዋ. ሥራ 1፤3
ከሆሣዕና እስከ ቅዳም ሥዑር ያሉት ዕለታት የዓመተ ፍዳ መታሰቢያ ናቸው፡፡ የሆሣዕና ዕለት ካህናት ቅዳሴ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ መግባታቸው ከአዳም ጀምሮ እስከ ስቅለት ያሉ ነፍሳት ወደ ሲኦል መውረዳቸው አምሳል ነው፡፡ ጸሎተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ በዚህ ሳምንት ውስጥ ለሚሞቱ ምእመናን እግዚኦ ሕያዋን ይደገማልና፡፡ በሰሙነ ሕማማት መስቀል የለም። ሳምንቱ የዘመነ ኦሪት ምሳሌ ስለሆነ እርስ በእርስ በመሳሳም፣ ሰላም መባባልና መልክዐ መድገም የለም። ይኸውም ይሁዳ ክርስቶስን በሰላምታ ስላስያዘው እርሱን ላለመምሰል፡፡ /ማቴ. 26/
በዚህ ሳምንት ብሉያትና ሐዲሳት መጻሕፍት ከጥዋት እስከ ማታ ይነበባሉ፡፡ የአምልኮ ስግደት ይሰገዳል፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሲል መስቀልን ተሸክሞ ሲወድቅ ሲነሣ የዋለበትን፣ ይልቁንም ሥርዓተ ስግደትን ራሱ ሰግዶ እኛን ያስተማረንን በማሰብ ነው፡፡ /ሉቃ. 22፡41-45፣ ዩሐ፣ 4፡22-24/
ስለዚህም በዚህ ሣምንት ወርኃዊ፣ ዓመታዊ በዓል ቢሆን እንኳ ስግደት አይቋረጥም፡፡ የአምልኮ ስግደት ሳምንት ስለሆነ፡፡ ዲያቆኑ ጥቁር ለብሶ መስቀል ይዞ ቃጭል እያቃጨለ ቤተ ክርስቲያንን ሦስት ጊዜ መዞሩ፣ ዲያቆኑ በዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፣ ቃጭል የእመቤታችን ምሳሌ ሲሆኑ፤ ዮሐንስና እመቤታችን ጌታችን የተሰቀለበትን እግረ መስቀሉን እየዞሩ አልቅሰው ነበርና፡፡
በዕለተ ዓርብ ሰርክ ሲሆን ምእመናን ወደ ቄሱ እየቀረቡ ስግደት እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡ ቄሱም በወይራ ቅጠል እየጠበጠበ ተጨማሪ ቀን ሲሰግዱ ከዋሉት ሌላ ስግደት ይሰጣቸዋል፡፡ ጥብጣብ የጌታችን ግርፋት ምሳሌ ነው፡፡ አንድም  የተግሣፅ ምሳሌ ነው፡፡ /ማቴ. 26፡27/
አክፍሎት
አክፈለ፣ አካፈለ፣ ደረበ እያሳገሩ መብላትን ግብረ ሕማማትም ያዛል፡፡ አክፍሎት ማለት ማካፈል፣ ማጠፍ፣ መደረብ፣ ሁለቱን ቀን አንድ ቀን አድርጎ መጾም፣ ጌታ ከተያዘበት እስከተነሳበት ድረስ ይህ ሥርዓት የመጣው በቤተ ክርስቲያናችን ልማድ እመቤታችን፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የጌታን ትንሳኤ ሳናይ እህልና ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤ በመቆየታቸው ምክንያት ነው። በሀገራችን ብዙ ሰዎች ሐሙስ ማታ የቀመሱ እሁድ የትንሳኤ ዕለት ብቻ እህልና ውኃ የሚቀምሱ ሲሆን ያልተቻላቸው ግን ዓርብ ማታ ትንሽ ቀምሰው እስከ ትንሳኤ ይሰነብታሉ፡፡ የሁለቱ ቀን ማክፈሉ እንኳ ቢከብድ ቅዳሜን ማክፈል ሥርዓት ነው፡፡ ቅዳሴው በመንፈቀ ሌሊት ስለሆነ በልቶ ማስቀደስና መቁረብ እንዳይሆን፡፡

Read 3749 times