Tuesday, 14 April 2015 09:03

መቃብር ቆፋሪው

Written by  በደረጀ ይመር
Rate this item
(8 votes)

ጉዳጓድ የሚምስበትን መዳፉን አፈፍ አደረገው። መቃብር ቆፋሪው እየተርበተበተ ቀና ሲል በጭስ ቅርጽ የተሠራ ሰው ከሚመስል አንዳች ፍጡር ጋር ፊት ለፊት ተላተመ፡፡
“እነኝህ መዳፎች ለስንቱ ንጹሃን ጉዳጓድ ሲምሱ ኖሩ” አለ ጭሳዊው ፍጡር
“ማነህ አንተ”  መቃብር ቆፋሪው ቆፍጠን ብሎ ወደ ጭሱ አፈጠጠ
“መላአከ ሞት ….ስሜን በከንቱ የምታነሳው …መላአከ.ሞት ነኝ”
“መላአከ ሞት…..እዚህ ምን ዶለህ፤ እኔ አገልጋይህ ታዛዥህ እያለሁ” አለ ከወገቡ ሸብረክ ብሎ ሰላምታ እየሰጠው፡፡
“አሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃ…እርግጥ ነው ንጉስህ ነኝ፤ እፍታ ነፍስን የሸለቆዬ ጥሪት የማደርግ ንጉስ፤ ይልቅ በደንብ ጆሮ ሰጥተኽ አድምጠኝ፤ ዛሬ በማስከው ጉድጓድ ልዶልህ ነው አመጣጤ”
“ምን በድዬ ጌታዬ!” “የመቃብር ቆፋሪው እጆች መንቀጥቀጥ ጀመሩ
“ለበድን ዘብ ቆመሃል፤ሀገር አሳድምሃል፤በድን ላይ ሽር ጉድ እንዲበራከት ተዋናይ ሆነሃል፤ቆይ እኔ የምለው እስትንፋስ ለሌለው በድን ይኽ ሁሉ ጎበስ ቀና ማለታችሁ በሸለቆዬ ያደላደልኳቸውን ነፍሶች ልታሸፈቱ መሻታችሁ ይሆን ?”
“ምን ፍጠር ይሉኛል ጌታው፤እኔ ወድጄ ነው? የዕለት ጉርስ ሆኖብኝ እንጂ”
“ሀገሬው በድን እየሞሸረ ከሸለቆዬ ያኖርኳቸው ነፍሶች እየተቀናቀነ ነው፡፡ ለበድኑ ሻማ ያዥ ደግሞ አንተ ነኽ፡፡ ለማንኛውም አንድ ዕድል ….አንድ ዕድል እሰጥሃለሁ፡፡ ይሄን ጉድጓድ የመማስ ግብርህን ፊት ንሳ፡፡ ፊት ካልነሳህ ግብሬ ይከፋል። ጥንቅሹንም፣ ጎበዛዝቱንም፣ የአልጋ ቁራኛውንም  ከጎታዬ ለመክተት እንጥፍጣፊ ምህረት አይኖረኝም።”
“ታዲያ ሀገሬው በድኑን የት ያኑረው ጌታው”
“ያቃጥለው፡፡ ዓመድ ያድርገው….ሲያሻው ዓሙዱን እንደእህል ይውቃው ”
“በቁሙ ተቀጥሎ፤በድኑ ተቃጥሎ እንዴት ይዘለቃል …እሺ  የእኔስ የዕለት ጉርስ ነገር? ”
“ከጎጆህ ፊት ለፊት ያለችውን ጉብታ  ስፍራ አቅና፤ ሳይውል ሳያደር ሀብት በሀብት ትሆናለህ…ቃሌ …ከሚያልፍ…… ”
የጋሽ ጎንፋ ጥሩንባ፤ መቃብር ቆፋሪው  ከመላአከ ሞት ጋር የነበረው የህልም አለም ግብግብ መሃል ገብቶ ገላገለው፡፡
“ማንም ከመጤፉ የማይቆጥራት ቆሻሻ መጣያ ጉበታ ሥፍራን አቅንቼ ምን አይነት የፍሰሃ ሕይወት ነው ልኖር የምችለው? ይህንን ህልም ችላ ማለት መቼም በራስ ላይ መፍረድ ነው፡፡” ለራሱ አጎተመተመ፡፡
ደጋግሞ አማተበ እና በድን የለመዱ፣ ቋጥኝ የታከኩ መዳፎቹን ወደ ደረቱ አስጠግቶ በፍቅር ሙጭሙጭ አድርጎ ሳማቸው፡፡ እንደ ጻዲቅ ለእርሱ ብቻ ተገልጦ ተዓምር ስላሰማው መላአከ ሞት ሲያወጣ ሲያወርድ ህልም ፈቺው ደብተራ ይሰሃቅ ከእነ ክንብንባቸው ድቅን አሉበት፡፡ ደብተራ ይስሃቅ የተናገሩት መሬት ጠብ አይልም፡፡ ሃገሬው የደብተራ ይሰሃቅን ነብያዊ ግልጋሎት ለማግኘት ማልዶ ነው የሚገሰግሰው፡፡ ደሳሳ ጎጆውን ወደኋላ ጥሎ ወደ ደብተራ ይሰሃቅ ቤት ለመብረር ተነሳሳ፡፡ በጎዳናው ላይ ትንሽ እንዳዘገመ ፍጥነቱን የሚገታ የጣር ድምጽ ከጆሮው የዘለቀ መሰለው፡፡ በጉጉት ወደ ጣር ድምጹ ጆሮውን ጣል ሲያደርግ፣ ጣሩ ከአጋፋሪ ቢትወደድ ቤት ነው የሚያስተጋባው፡፡ የአጋፋሪን ቢትወደድ መዝጊያ ገፉ አድርጎ ወደ ወስጥ ዘለቀ፡፡
“አንተ የሞት ታናሽ ወንድም፤ ገና ክንዴን ሳልንተራስ ምን አጣደፈኽ” አሉት አጋፋሪ የበኩር ልጃቸውን እጅ እንደተደገፉ፡፡
“እርግጥ ነው አጋፋሪ… ከመላአከ ሞት ጋር ያለን ዝምድና በርትቷል”
“እህህ..እህህ..አህህ..አህህህ………ይህንን ሞት ጠሪ...አባሩልኝ…እህህ.. አባሩልኝ…አህህ..” የአጋፋሪ መቃሰት ተባባሰ፡፡
“እርሱ ይሁኖት…መቼስ ሌላ ምን ይባላል” የተከሰከሰውን የመንትያ የልጅ ልጆቻቸውን ፊት ገርመም አድርጎ በመጣበት ፍጥነት ተፈተለከ፡፡
ስለራዕዩ የሚወጣበት የሚወርድበት ምናቡ የሰነፈ መሰለው፡፡ ይመኙሻል የዶሮ ዓይን የመሰለ ጠላ ድንገት ውል አለበት፡፡ የለገመውን ንቃቱን መልሶ ለማበርታት ወደ ይመኙሻል ጠላ ቤት የምትወስደውን ከሲታ የኮብል ስቶን መንገድ ተያያዘው፡፡ ይመኙሻል ጥሩ ጠላ የምትጥል ባለሟል ነች፡፡ በቤቷ የመንደሯ ሲሶ አባወራ ይታደምባታል። የከተማው ጮማ ረዕሰ ወሬ ለእርድ የሚቀርበው እዚች ኩርማን በምታክለው ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ነው። ፍትህ የፈለጉ ባለሶስት ጉልቻ ተጣማጆች ግራ እና ቀኝ ቆመው ብይን ያገኙባታል፡፡
ከቤቷ ፈጥኖ እንደደረሰ ይመኝሻል እንደወትሮው በመዳፍ ልክ የተከረከመውን የጠላ ቤቷን ወለል ጋራ በሚያክለው ዳሌዋ ግልብጥብጡን እያወጣች አገኛት፡፡ ለባሻ ወልዴ ጠላ በአንኮላ ትቀዳለች። “ኖር ኖር” አሉት ባሻ ወልዴ፤ የይመኙሻል ዳሌን በብትራቸው ጎንተል እያደረጉ
“እኚኽ…ደግሞ….የማይሸመግሉ ሰው” አለችና እየተቆናጠራች ወደ ውስጥ ዘለቀች፡፡
“ወሬያችን ቆረፈደ አይደል፤እስቲ የወሬውን ጠርዝ አመላክተኝ ጃል” አሉ ባሻ ከጎናቸው ያሉትን ጠና ያሉ ባልንጀራቸውን፡፡
“ሰውዬው ሊሞት እያጣጣረ ያልከኝ መሰለኝ”መቃብር ቆፋሪው ይበልጡኑ ጆሮውን ቀሰረ፡፡
“አዎ ሰውየው ሊሞት እያጣጣረ ነው። አራቱ ልጆቹ ከበውት መላ ያወጣሉ ያወርዳሉ። የበኽር ልጁ ለአባቱ ክብር ጭንቅ ጥበብ ይላል። “አባታችን በቁሙ እያለ በሽሙንሙን አውቶሞቢል ፍስስ እያለ መሄድ ይመኝ ነበረ፤ያለንን ጥሪት አሟጠንም ቢሆን ሬሳው ወግ ማዕረግ ሊያይ ይገባል” አለ
ሁለተኛው ልጅ የወንድሙን ሃሳብ በጽኑ ተቃወመ፡፡
“ጥሪት ማሟጠጥን እዚሀ ምን አመጣው። ደግሞ ለበድን ሬሳ….የጋሽ ጠና ጋሪ አለ አይደል እንዴ?” ብሎ አወገዘው፡፡
“መቼም በበኽርልጁ የማይቀና የለም። ሞቴን አሳምርልኝ። ቀብሬን አድምቅልኝ ይሉሃል እንዲህ ነው።” ውኃ የጠገበውን የአፈር ወለል በብትራቸው እየቆረቆሩ በስሜት መናጋራቸውን ቀጠሉ፡፡
ሶስተኛው ልጅ አስታራቂ ብሎ ያሰበውን ሀሳብ አቀረበ፤
“የዘየዳችሁት መላ አልገባኝም፡፡ ለሞተ በድን ይሄ ሁሉ ሽርጉድ ምን ይፈይዳል? አባታችን ልክ ነፍሱ ሲወጣ ሬሳውን አንስተን ከአውራ ጎዳና ላይ እናኖረዋለን:: ከእዛም የመዘጋጃ ቤቱ አውቶሞቢል ሬሳውን ያነሳ እና ቀብሩን በራሱ ወጪ ይፈጽማል” አለ፡፡
“ጉድ ጉድ አበስኩ ገበርኩ፤የጉድ ቀን ቶሎ አይመሽም” አዛውንቱ ሰውነታችው እየተርገፈገፈ አማተቡ፡፡
“ይህ ይደንቀሃል? የማሟጠጫው ልጅ ተብየው የባሰ ጉድ አመጣ፤ሬሳው መቃጠል አለበት አለ፡፡ ይህን ጊዜ ብርታቱ ከየት እንደመጣለት እንጃ የወላድ መካን የሆነው አባት ድንገት ከመኝታው እምር ብሎ ተነሳና ጫማውን እንዲያቀብሉት ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡”
“አይያዙ እንጂ..ከተያዙ በኋላ…ከአብራክ የወጣም እንዲህ ይጨክናል” የወሬው መቋጫ እየናፈቃቸው አዛውንቱ አጉተመተሙ፡፡
“ሁላችሁም ለበድን አካሌ የሚፈይድ መላ አላበጃችሁም፡፡ ወጪ ቆጣቢው መፍትሄ በእኔው እጅ ላይ ነው ያለው፡፡ እኔው እራሴ አዝግሜ እዛው ከመቃብሩ ሥፍራ ክንዴን እንተራሳለሁ።” ባሻ የታሪኩን ሰም እና ወርቅ ፍቺ ለአዛውንቱ ትተው አንኮላው ላይ የቀረውን ጠላ በአንድ ትንፋሽ ጨለጡት፡፡
መቃብር ቆፋሪው ህልሙ እና የእነ ባሻ ጨዋታ የሚገጥሙበትን ፈር እያሰሰ ባለበት ሁናቴ ከሌላኛው ጥግ ድምጻቸውን ዘለግ አድርገው የሚያወጉት ጠጪዎች እነ ባሻ ላይ ያኖረውን ትኩረት ነጠቁት። የመላአከ ሞት ቃልኪዳንን የሚቀናቀን ወሬ ስለሆነ ጆሮውን  የበለጠ አነቃ፡፡
“በቀይ ሽብር ይፋፋም ሰበብ የአንድ ፍሬ ወጣቶችን ደም የበላች ሥፍራን፣እንዴት ዘነጋሃት?” አለ አናቱ ላይ የነተበ የሹራብ ቆብ ያጠለቀው ጎልማሳ!
“ምን ዙሪያ ጥምጥሙን አስክሄደህ ጉብታዋን አትለኝም…እርሷ ስፍራ እኮ ታሪከ ብዙ ነች ፤ጥሊያን አንድ እንስራ ሙሉ ጠገራ ብር ቀብሮባታልም ይባላል” አለ ሌላኛው የገጠር ዘይቤ በተጫነው አማርኛ፡፡
“ሰሞኑን የሆነ ኤፍም ራዲዮ ላይ የሥፍራዋ ማሕጸን ተመርምሮ ተዝቆ የማያልቅ የኮብል ድንጋይ ሀብት ተገኘሲሉ ሰማሁ”
“እንዴት ነው ነገሩ፡፡ ማርትሬዛ ሲውል ሲያድር ከድንጋይ ጎራ መቀየጥ ጀመረ? አይ 8ኛው ሺ??? ለነገሩ ቸር ወሬ ነው፡፡ የዘንድሮው ድንጋይ እንደሆነ ቆብ የደፋ ካላየ ወይ ፍንክች ብሏል ”ወሬ ተቀባዩ በዜናው ላይ ተዘባበተ፡፡
“መጪው ዘመን ከጉብታዋ ጋር ብሩህ ነው” መቃብር ቆፋሪው ድምጹን ድንገት አሰማ፡፡
“አብሾ አለበት…ትንሽ ከቀማመደ መለፍለፍ አመሉ ነው” ባሻ እንግዳ የሆነባቸውን ጠጪዎች አረጓጓቸው፡፡
“ይህ ሁሉ ወፈሰማይ የመንደሯ ነዋሪ…………. አንኮላውን እያንደቀደቀ ከሚቃዥ… እንደ እኔ ጎኑን አሳርፎ ጥሩ ህልም አያልምም?…እኔ ባለራዕይ…ህልመኛ ነኝ…ህልመኛ ደግሞ ባልንጀራው፤ መሸታ ቤት ሳይሆን ደብተራ ፣ምትሐት ነው፡፡” እየለፈለፈ የይመኙሻልን ጠላ ቤት ጥሎ በረረ፡፡
“አጅሬ ዛሬ ያለነገር ደብተራ ደብተራ አላለም….የፈረደበትን ሕልም ከደብተራ ይሰሓቅ ዘንድ ሊያስፈታ ነው…. ደሃ በሕልሙ ቅቤ ባይጣጣ……አሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃ.”  ባሻ በትራቸውን እየወዘወዘ ፈገግታቸውን ከፊታቸው ላይ እንደ ችቦ ለኮሱት፡፡

Read 4822 times