Tuesday, 14 April 2015 11:27

በ1 ደቂቃ ሙሉ ለሙሉ ቻርጅ የሚደረግ የሞባይል ባትሪ ተሰራ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

   የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በአንድ ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ቻርጅ መደረግ የሚችልና የረጅም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥ አዲስ የአልሙኒየም የሞባይል ስልክና የላፕቶፕ ኮምፒውተር ባትሪ መስራታቸውን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
አዲሱ የሞባይል ስልክና የላፕቶፕ ባትሪ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኘው መደበኛው የሊቲየም ባትሪ ጋር ሲነጻጸር፣ በከፍተኛ ፍጥነት ቻርጅ ከመደረጉ በተጨማሪ ለአደጋ የመጋለጥ ዕድሉም እጅግ አነስተኛ ነው ተብሏል፡፡
“ፈጠራችን በባትሪው ቴክኖሎጂ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው፡፡ እኛ የሰራነው ባትሪ በእሳት የማይቃጠል ነው፡፡ ለአጠቃቀምም ምቹ በሆነ መልኩ ነው የተሰራው፡፡ ሊቲየም አዮን ባትሪን ከመሳሰሉ ሌሎች ነባር የባትሪ አይነቶች ጋር ሲነጻጸር፣ ሳይደክም ለብዙ ጊዜያት ቻርጅ የመደረግ አቅሙ እጅግ ከፍተኛ መሆኑም ተመራጭ ያደርገዋል” ብለዋል፤ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት የተመራማሪ ቡድኑ መሪ ሆንጊ ዳይ፡፡
ፕሮፌሰሩ እንዳሉት፣ ከዚህ በፊት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የአልሙኒየም ባትሪዎች፣ በሙሉ አቅማቸው መስራት የሚችሉት እስከ መቶ ጊዜ ያህል ተደጋግመው ቻርጅ እስኪደረጉ ነበር፡፡ ይሄኛው ባትሪ ግን 7ሺህ 500 ጊዜ ያህል ቻርጅ እስኪደረግ አቅሙ የማይቀንስ በመሆኑ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡
ተመራማሪዎቹ የፈጠራ ውጤታቸውን ሰርተው ማጠናቀቃቸውን ሰሞኑን ለህትመት በበቃ መጽሄት ላይ ይፋ ቢያደርጉም፣ ባትሪው በብዛት ተመርቶ ለገበያ የሚቀርብበትን ጊዜ በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡

Read 4423 times