Tuesday, 14 April 2015 13:33

የቲ-ሸርትና የኮፍያ ወጪ ያናድደኛል !!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

     የአገራችንን የኢኮኖሚ እድገት የሚያበስሩ ዜናዎችን በየግዜው በሚዲያ እንሰማለን፡፡ ሆስፒታሎች፤ ፋብሪካዎች፤ ት/ቤቶች፤ ድልድዮች ወዘተ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች መንግስት መስራቱን በሰማሁ ቁጥር የላቀ ደስታ ይሰማኛል፤ እሰየው! ብራቮ ኢትዮጵያ እላለሁ፡፡ እነዚህ መሰረተ ልማቶች ሰፋ ባለ እቅድ፤ ብዙ ልፋትና የህዝብ ገንዘብ ፈሶባቸው ለህዝብ አገልግሎት በሚበቁበት ግዜ ይሄንን ትልቅ ስኬት ማክበር አግባብ ነው፡፡ ደስም ይላል፤ የሁላችንም ድል ስለሆነ፡፡
እድለኛ ሆኜ አንዳንድ ምርቃቶች ላይ ብገኝም አብዛኞቹን ያየሁት ግን በቴሌቪዥን ነው፡፡ እነዚህን በዐሎች ስመለከት ግን ሁልግዜ የሚከነክነኝ አንድ ነገር አለ፡፡ አስተውላችሁ እንደሆነ ባለስልጣኖችም ሆነ ተጋባዥ እንግዶች ለምርቃቱ የተዘጋጁ ልዩ ካናቴራዎችና ኮፍያዎች ለብሰው እናያለን፡፡ እነዚህን ካናቴራዎችና ኮፍያዎች በብዛት ለማዘጋጀት ብዙ ብር ያስፈልጋል፡፡ ፅሁፍ ያላቸው ኮፍያና ካናቴራዎች  እያንዳንዳቸው በአማካይ 100 ብር ድረስ ያወጣሉ፡፡ ለአንድ ምርቃት በግምት ከ500 እስከ 1000 ሊዘጋጅ ይችል ይሆናል፤ እንግዲህ ሂሳቡን እናንተ አስሉት፡፡
ጥቅምና ፋይዳ ቢኖረው ግድ ባልሰጠኝ ነበር፤ ግን እነዚህ ካናቴራዎችና ኮፍያዎች አገልግሎታቸው ለዚያች ቀን ብቻ ነው፤ በእለቱ የተገኙት ሰዎች ሌላ ቀን ደግመው የሚለብሱትም አይመስለኝም፡፡ ጥቂቶቹ ቢጠቀሙባቸውም እንኳን ለካናቴራውና ለኮፍያዎቹ ከሚወጣው ወጪ ጋር ሲነፃፀር ከጥቅሙ ጉዳቱ  ያይላል፡፡ በየአመቱ፤ በየክልሉ ስንት የምርቃት በዐል እንደሚደረግ እንግዲህ አስቡት፡፡ አንድ ብዙ የምርቃት በዐል የተካፈለ ጓደኛዬ ሴት ልጅ፤ ‹ቤት ያሉትን ኮፍያዎችና ካናቴራዎች ሰብስቤ ቡቲክ ልከፈትበት--› እያለች በአባትዋ ስትቀልድ ሰምቼአለሁ፡፡ የበዐሉ ዋናውና መሰረታዊ አላማው የመሰረተ ልማቱን ስኬት ማክበር እንጂ ተሳታፊዎቹን በኮፍያና ካናቴራ ማንበሽበሽ አይደለም፤ መንግስትም ይሄን ማድረግ አይጠበቅበትም፡፡  
ለበዐሉ ማስታወሻነትም ከተፈለገ፤ ስለስራው የሚገልፁ ብሮሽሮች፤ መፅሄቶች--- ማዘጋጀት የተሻለና ዘላቂ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ሠው ቤቱም ሆነ ቢሮው ስለሚያስቀምጠው በበዐሉ ላይ ላልተገኙ ወይም በሚዲያ ላልተከታተሉ ሰዎች በማስታወሻነትም በመረጃነትም ለረጅም ግዜ ሊያገለግል ይችላል፡፡
በአገራችን እንጭጭ ኢኮኖሚ ከድህነት ጫና ለመውጣት ገና ዳዴ በምንልበት ወቅት፤ ለምርቃት በሚል ኮፍያና ካናቴራ ማሰራት አላስፈላጊ ወጪ ይመስለኛል፡፡ ይሄንና ሌሎች አላስፈላጊ ወጪዎችን ከዚህም ከዚያም መቀናነስና መቆጠብ ከቻልን ትልቅ የገንዘብ ሀይል ይሆኑናል፤ አንዳንድ አንገብጋቢ የልማት ቀዳዳዎችንም ሊደፍኑልን ይችላሉ፡፡ ግብር ከፋይ ነኝና ጉዳዩ ያገባኛል ብዬ ነው ሃሳቤን የሰነዘርኩት፡፡  በእርግጥ ነገሩ የግል ድርጅቶችን ወይም ግለሰቦችን አይመለከትም።
ኃይለማርያም ገ/ሕይወት- ከቀጨኔ

Read 2799 times