Monday, 20 April 2015 14:04

“የኛ” ፊልም ከዛሬ ጀምሮ ለእይታ ይበቃል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“የኛ” የሬዲዮ ፕሮግራም አምስተኛ ሲዝን ጀምሯል

ታዋቂ ድምጻውያን ለመሆን በሚጥሩ አምስት ወጣት ሴቶች የህይወት ውጣውረድ ዙሪያ የሚያጠነጥነው “የኛ” ፊልም ከዛሬ ጀምሮ በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች ለእይታ እንደሚበቃ ፕሮዲውሰሮቹ አስታወቁ፡፡
ፊልሙ በክልሉ በሚገኙ 26 ከተሞች በትምህርት ቤቶችና የማህበረሰብ አዳራሾች ውስጥ በነጻ እንደሚታይና 40ሺህ ያህል ተመልካቾች ያዩታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሯል፡፡
የኛ በተባለው የሬዲዮ ድራማ ላይ የሚታወቁት ሚሚ፣ ሜላት፣ እሙየ፣ ሳራ እና ለምለም የተባሉት ገጸባህሪያት የሚሳተፉበት ይህ ፊልም፤ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ በኢቢኤስ እና በአማራ ክልል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ልዩ ፕሮግራሞች ለእይታ እንደሚበቃም ተገልጧል፡፡
የናይኪ ፋውንዴሽንና የእንግሊዝ መንግስት አለማቀፍ የልማት ድርጅት (ዲፊድ) ጥምረት በሆነው ገርል ሃብ ኢትዮጵያ የሚከናወነው የኛ ፕሮጀክት በሸገር ኤፍ ኤም እና በአማራ ክልል ሬዲዮ ጣቢያዎች፤ ሲያስተላልፈው የቆየውን የኛ የሬዲዮ ፕሮግራም አምስተኛ ሲዝን መጀመሩንም የኛ ቤት የተባለው የ3 ተቋማት ጥምረት አስታውቋል፡፡
የኛ የሬዲዮ ድራማ በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችና እና በአዲስ አበባ ከ1 ሚሊዮን በላይ አድማጮች እየተከታተሉት እንደሚገኙና፣ ድራማውን ከሚከታተሉት ልጃገረዶች 84 በመቶው በህይወታቸው ስኬታማ ለመሆን የራስ መተማመናቸው እንዳደገና፣ 76 በመቶ የሚሆኑትም ድራማው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲቀጥሉ እንዳነሳሳቸው በጥናት መረጋገጡም ተገልጧል፡፡
የኛዎች በለቀቋቸው ነጠላ ዜማዎችና የቪዲዮ ክሊፖች እንዲሁም በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ በሚያቀርቧቸው የሙዚቃ ዝግጅቶች ተወዳጅነትን ማትረፍ መቻላቸው ይታወቃል፡፡

Read 4129 times