Monday, 20 April 2015 14:06

በኢቦላ ወደተጠቁ አገራት ለስራ የሄዱ ኢትዮጵያውያን እየተመለሱ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ተመላሽ ኢትዮጵውያኑ በማቆያ ውስጥ ተቀምጠው ክትትል እየተደረገባቸው ነው
የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች ወደ አገር ውስጥ አይገቡም ተብሏል፡፡
በሽታው ወደ አገር ውስጥ ቢገባ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡

በምዕራብ አፍሪካ አገራት በድንገት ተከስቶ ለሺዎች ሞት ምክንያት የሆነውና ዓለምን ስጋት ላይ የጣለው የኢቦላ በሽታ አሁንም ሥጋት መሆኑ አላበቃም። በበሽታው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳት በሽታው ወደተከሰተባቸው አገራት ሄደው ለወራት የቆዩት ኢትዮጵያውያን ኮንትራታቸው በመጠናቀቁ ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው፡፡ ተመላሽ ኢትዮጵያውያኑ ለኢቦላ ክትትልና ቁጥጥር በተዘጋጁት የማቆያ ማዕከላት ውስጥ ሆነው ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ ኢቦላን አስመልክቶ ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ዳዲ ጂማ እንደተናገሩት፤ ኢቦላ የዓለም ስጋትነቱ እንደቀጠለ መሆኑን ጠቁመው የስጋቱ መጠን ቀደም ብሎ ከነበረው የተለየ አለመሆኑንና ኢትዮጵያ እስከአሁን ድረስ ከበሽታው ነፃ መሆኗ መረጋገጡን ገልፀዋል፡፡ በሽታው በአገሪቱ ቢከሰት እንኳን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ በሽታውን በቀላሉና በፍጥነት ለመለየት የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች ግዥ መፈፀሙንም ገልፀዋል፡፡
በኢቦላ ወደተጠቁ አገራት በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት አማካኝነት ለስራ የሄዱ ኢትዮጵያውያን የሥራ ኮንትራታቸውን አጠናቀው ወደአገራቸው እየተመለሱ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዳዲ፤ እነዚህ ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ለሥራ በቆዩባቸው ጊዜያት ለበሽታው ሊጋለጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ ተመላሾቹ በኢቦላ ክትትል ማዕከል ውስጥ እንዲቆዩ በማድረግ ክተትልና ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የበሽታው ምልክት የታየባቸው ደግሞ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ በመግታት እዚያው ባሉበት ቦታ ላይ ክትትልና ምርመራ እንደሚደረግላቸው ጠቁመው በዚህም በሽታው ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በበሽታው ወደተጠቁ አገራት በመንግስት የተላኩ በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎችም በቅርቡ የቆይታ ጊዜያቸውን አጠናቀው እንደሚመለሱና በእነሱም ላይ ተመሳሳይ ክትትል እንደሚደረግ ዶ/ር ዳዲ ጨምረው ገልፀዋል፡፡  

Read 1148 times