Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 January 2012 11:11

ጎልደን ግሎብ የኦስካር አሸናፊዎችን ፍንጭ ሰጠ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከዘንድሮው ኦስካር በፊት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የጎልደን ግሎብ የሽልማት ስነስርዓት ባለፈው ሳምንት  ለ69ኛ ጊዜ ሲካሄድ ለኦስካር አሸናፊነት የሚበቁ ፊልሞችን ፍንጭ እንደሰጠ  ዘገባዎች አመለከቱ፡፡ “ዘ አርቲስት”  ሶስት እንዲሁም “ዘ ዲሴንዳንት” ሁለት ሽልማቶችን በማግኘት ምሽቱን ደምቀውበታል፡፡ የሽልማት ስነስርዓቱ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከተካሄዱት የአሜሪካ ሙዚቃ አዋርድና ኤሚ ስነስርዓቶች በበለጠ 17 ሚሊዮን የሚደርሱ ተመልካቾች በቲቪ እንደታደሙት ታውቋል፡፡

በጆርጅ ኩለኒ መሪ ተዋናይነት የተሰራው “ዘ ዲሴንዳንትስ” የተሰኘው ፊልም ሁለት ሽልማቶችን ያሸነፈ ሲሆን አንደኛው የዓመቱ “ምርጥ ድራማዊ ፊልም” በሚለው ዘርፍ ያገኘው ሲሆን ሌላው ጆርጅ ኩለኒ የአመቱ ምርጥ የድራማ ተዋናይ” ተብሎ የተሸለመው ነው፡፡ በጎልደን ግሎብ የዓመቱ ምርጥ ተዋናይት ተብላ የተሸለመችው ሜሪል ስትሪፕ ”ዘ አይረን ሌዲ” በሚል ፊልም ላይ ባላየችው ብቃት ሲሆን የአሁኑ ሽልማት ለስምንተኛ ጊዜ የተሸለመችው እንደሆነ ታውቋል፡፡ “ሁጎ” በተባለው ፊልሙ ማርቲን ስኮርሴሲ የዓመቱ ምርጥ ዲያሬክተር ተብሎ ሲሸለም ባለፉት 10 ዓመታት በጎልደን ግሎብ የምርጥ ዲያሬክተርነት ሽልማት ሲወስድ የዘንድሮው ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ በ “ዘ አርቲስት” ፊልም ላይ በምርጥ የኮሜዲ ፊልም ተዋናይነት የተሸለመው ጆርጅ ቫለንቲን ወይም ዱጅርዲን የተባለው ተዋናይ በድምፅ አልባ ፊልም ለታላቁ ሽልማት የበቃ የመጀመርያው ተዋናይ ሆኗል፡፡ በሌሎች የሽልማት ዘርፎች የስቴቨን ስፒልበርግ “ዘ አድቬንቸርስ ኦፍ ቲንቲን› የዓመቱ ምርጥ አኒሜሽን፤ ዉዲ አለን ‹ሚድናይት ኢን ፓሪስ› በተባለው ፊልም የዓመቱ ምርጥ ስክሪን ፕሌይ እንዲሁም በኢራን ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው “ኤ ሰፓሬሽን” የዓመቱ ምርጥ በውጭ ቋንቋ የተሰራ ፊልም በመባል ተሸልመዋል፡፡ አንጋፋው ጥቁር አሜሪካዊ ተዋናይ ሞርጋን ፍሪማንም “ሴሲል ቢ ዴ ማይሌ” የተባለውን የክብር ሽልማት ተቀብሏል፡፡በጎልደን ግሎብ ሽልማት እጩ ሆነው የቀረቡና ተሸላሚ የሆኑ ፊልሞች ብዙዎቹ ከሆሊውድ ውጭ መቀረፃቸውን የጠቀሰው ሎስአንጀለስ ታይምስ፤ የጆርጅ ኩለኒ “ዘ ዲሴንዳንትስ› በሃዋይ፤ የሜሪል ስትሪፕ ‹ዘ አይረን ሌዲ› በለንደን፤ የማርቲን ስኮርሴሲ ‹ሁጎ ›በፓሪስ እንዲሁም የስፒልበርግ ‹ዘ አድቬንቸር ኦፍ ቲን ቲን› በኒውዝላንድ መቀረፃቸውን አመልክቷል፡፡ የጎልደን ግሎብ የሽልማት ስነስርዓትን የሚያዘጋጀው የሆሊውድ ፎሪን ፕሬስ አሶሴሽን ሲሆን አሸናፊዎችን የሚመርጡ 250 አባላት ያሉት ተቋም ነው፡፡

ለዘንድሮ ኦስካር በተለያዩ የሽልማት ዘርፎች የሚቀርቡ እጩዎች ዝርዝር ከ4 ቀናት በኋላ ይፋ እንደሚደረግ ሲጠበቅ የሽልማት ስነስርዓቱ ከወር በኋላ ሎስአንጀለስ በሚገኘው የኮዳክ ቲያትር አዳራሽ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡ በጎልደን ግሎብ ተሸላሚ የሆኑ ፊልሞችና ባለሙያዎች በኦስካርም ሊቀናቸው እንደሚችል የዘገበው ሆሊውድ ሪፖርተር፤ የፊልሞቹ ገበያ ከሽልማቶቻቸው በኋላ መሟሟቁንም ጠቁሟል፡፡

 

 

Read 2647 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 11:13