Tuesday, 21 April 2015 07:59

የአያቴ ኩርፊያ

Written by  ሙሉጌታ አለባቸው
Rate this item
(7 votes)

የሰፈራችንን ትልቁን ነጋዴ መረተን ያሳደገችው አያቴ ነች። ምንም እንኳ የሥጋ ዝምድና ባይኖረንም ከልጆቿ እኩል ነው ያሳደገችው፡፡ ጎልማሳ ሆኖ ወደ ራሱ ሥራ ከመግባቱና ከእኛ ቤት ዝቅ ብሎ ቤት ተከራይቶ መኖር ከመጀመሩ በፊት፤ ብቸኛ እናቱ ሞሳ እያለ ከሞቱበት ጊዜ ጀምሮ አያቴ ቤት ይኖር ነበር። ለስሙ ቤት ተከራየ እንጂ ቤት እየመጣ ቁርሱን፣ ምሳውንና ራቱን መብላቱን አላቋረጠም፡፡ በቅርቡ የገዛቸውን ቴኒሱንና ጆተኒውን እንኳ ከቤታችን በር ላይ አላነሳም፡፡ ከሆነ ጊዜ በኋላ ግን ከአያቴ ጋር ተቆራረጠ፡፡ ዋናው ምክንያታቸው መረተ  ኃይማኖቱን መቀየሩ ነበር፡፡ መረተ ሰለመ፡፡
አያቴ አጥባቂ ኃይማኖተኛ ስለነበረች ለእንደዚህ ዓይነቱ የአቋም ለውጥ ፊት የምትሰጥ አልነበረችም፡፡ በዚያ ላይ በደርግ፣ በኢህአፓ፣ በተስቦ፣ በሳንባ ነቀርሳና በመጠጥ ከሞቱ አምስት ወንድ ልጆቿ ለቁምነገር የበቃው እሱ ነበርና እንደ ዓይኗ ብሌን ምናምን ነው የምታየው፡፡
በአያቴ ዓይኖች መረተ በጎም ሠራ ክፉ በጥቂቱ ተጋንኖ ነው የሚታየው፡፡ ስለዚህም ለጥቂት ጊዜ ያክል እኔም ሆንኩ እህቴና ወንድሜ መረተ አዲስ ቤት ‹‹ድርሽ እንዳንል›› ተነገረን። ሆኖም ከታናሽ ወንድሜ ጋር በድብቅ መሄዳችንን ልናቋርጥ አልቻልንም፡፡ ለሄኖክ መረተ ከትንሿ ሱቁ እያወጣ የሚሰጠው ከረሜላና ማስቲካ ለምን ይቅርበት! ለእኔ ደግሞ ታላቅ ወንድምነቱ!
አያቴ መረተ ጋ በድብቅ እንደምሄድ ብትሰማ በሳማ ባትገርፈኝ እንኳ ጠንከር ያለ ግሳጼ እንደምትሰጠኝ አልጠራጠርም፡፡ ቢሆንም መረተ ቤት እሄዳለሁ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሄድ አስታውሳለሁ፡፡ ብቻዬን ነበርኩ፤ታናሽ ወንድሜ ቴዎድሮስ ኩፍኝ ታሞ ተኝቷል፡፡ ድብርቴ እየገፋኝ፤ የማወቅ ፍላጎቴ እየጎተተኝ መረተ ቤት ሄድኩኝ፡፡ ክፍሉ ጨለምላማ ነው፡፡ ከበሩ የሚገባው ብርሃን እንደ ምንጣፍ ነገር ወለሉ ላይ እየተሳበ ወደ ውስጥ ይዘልቃል፡፡ ብርሃኑ እየደከመ ሄዶ የሚያልቅበት ጫፍ ላይ የጣዖስ ምስል ያለበት ሰፋ ያለ ምንጣፍ ተዘርግቷል፡፡ ምንጣፉ ላይ መረተ አለ፡፡ እያሰለሰ ደፋ ቀና ይላል፡፡ ደግሞ እጁን በደረቱ ላይ አድርጎ የሆነ ነገር ያጉተመትማል፡፡ ከውጭ ስሙን እየጠራሁ ስገባ ዝም ማለቱና አሁን ያለበት ኮስተር ባለ ተመስጦ እየተደረገ ያለው ነገር መረበሽ እንደሌለብኝ ነገረኝ፡፡ የበሩን መቃን በግራ ጎኔ ተደግፌ በአትኩሮት ማየቴን ቀጠልኩ፡፡ ከመረተ ጀርባ አልጋ ተዘርግቷል፡፡ ራቅ ብሎ ደግሞ ኩርቱ የሚል ጥቁር ጽሑፍ ያለበት ቢጫ ፌስታል በዕቃ ተሞልቶ ተቀምጧል፡፡ ፌስታሉ አጠገብ ደግሞ ዱቄት የተነሰነሰበት የመሰለ አረንጓዴ ቀለም ያለው ቡታጋዝ አለ፡፡ መምጣቴን ሁሉ ያወቀ አይመስልም፡፡
የሆነ የሚያስፈራ እንግዳ ነገር አለው፡፡ እስልምና ባይተዋር ሆኖብኝ አይደለም፡፡ ከቅርብ ጓደኞቼ ሁለቱ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ መስገድ አዲሴ አይደለም፡፡ ከመስጊድ የአዛን ድምፅ ሲጮህ ሁሉ ልብ ሳልለው የሚከናወን ድርጊት ነው፡፡ ብቻ አጋጣሚ ሆኖ በአዛን ሰዓት በመስጊድ አጠገብ እያለፍኩ ከሆነ አዛን ባዩ ‹‹የእስላም ቄስ›› ቅዳሴቸውን ለመጀመር ጉሮሯቸውን ጠርገው፣ ድምጻቸው በጣም በሚጮኸው የድምፅ ማጉያ ሲወጣ ሰምቼ አንድ ሁለቴ እንደ መደንገጥ አድርጎኛል፡፡  
መረተ ብቻውን መኖር ሊጀምር እንዳሰበ ለአያቴ የተናገረ ሰሞን አንድ ከሰዓት ቤተ መጻሕፍት ቆይቼ ወደ ቤት ስመለስ በመስጊዱ አጠገብ ማለፍ ነበረብኝ፡፡ መስጊዱን ከበስተቀኝ በኩል በቅርብ ርቀት አየዋለሁ፡፡ የግንቦትን ወበቅ ሽሽት ሕብረተሰቡ በየቤቱ መሽጎ ጎዳናው ላይ በርቀት ሰከም ሰከም ሲሉ ከማያቸው ሰዎች በቀር ማንም አይታይም፡፡ በአንድ ከባድ ድምጽ ‹‹እህህህም!›› ሲል ሰማሁ፡፡ ጥርት ካለው የበጋ ሰማይ የመጣ ሁሉ ይመስላል፡፡ በአጠገቤ አንድ ሰው ጭኖ ካለፈው ጋሪ በቀር ምንም አልነበረም፡፡ ቆይቶ መስጊዱ አጠገብ መሆኔን አውቄና ጉሮሮ ጠረጋ መሆኑን ተረድቼ ሳልጨርስ አዛኑ በጩኸት አሀዱ አለ፡፡ ለአፍታ ያክል እንደ መቆም እና እግሬ እንደመተሳሰር አለ፡፡ ግን አልቆምኩም፡፡ ድምፁ ወደመጣበት ወደ መስጊዱ አቅጣጫ ስዞር የመረተን ሻማ ጃኬት የመሰለ የለበሰ፣ እርምጃው እሱን የሚመስል ሰው የመስጊዱን በር አልፎ ሲገባ አየሁት፡፡ መረተ መሆን አለመሆኑን እርግጠኛ መሆን አልቻልኩም፡፡ ደግሞ መረተ መስጊድ ምን ሊሠራ ይመጣል?
ማታ ደጅ ወጥተን እግራችንን ታጥበን ከመግባታችን መረተ ወደ ቤት መጣ፡፡ አያቴ  ባለችበት ቀን ወደ መስጊድ ሲገባ እንዳየሁትና ምን ይሠራ እንደነበር ጠየቅሁት፡፡ አያቴ መቁጠሪያዋን በጣቶቿ መነካካቷን አቋርጣ ቀና ብላ አየች፡፡
‹‹መስጊድ? የምን መስጊድ?›› ደነገጠ መረተ፡፡
‹‹የእስላም መስጊድ ነዋ››
‹‹አንተ ደግሞ፤ እኔ ምን እሠራለሁ መስጊድ›› አለና ራት ለመብላት ቁጭ አለ፡፡
ከተደገፈው ግድግዳ ላይ አንድ ‹‹ውራንግለር›› የሚል ጽሑፍ ያለበት ጃኬት የለበሰ ኮስታራ ወጣት ፎቶ ተንጠልጥሏል፡፡ ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም፡፡ ጸጉሩ አፍሮ ነው፡፡ ኮስታራው በሕይወት የለም፡፡ አጎቴ ሰለሞን ነው፡፡ ሀያ ዓመት ቢሆነው ነው፡፡ ፊቱ ላይ ምንም ፂም የለም፡፡ ግን ኩስታሬው እንደ ትልቅ ሰው ዓይነት ነው፡፡  
አያቴ ወደ መቁጠሪያዋ ተመለሰች፡፡ መረተ የቀረበለትን ድንች ወጥና ጥቅል ጎመን በጎረምሳ ደንብ ከወደ ጉርሻው እያገዘፈ ይተመትማል፡፡ ቃሪያውን ይጎረድማል፡፡ ታላቅ እህቴ ማርታ የኤዞጵ ወይ የቢልጮ ተረት አፉን ለከፈተው ሄኖክና ብዙም ለማያዳምጣት መረተ ትተርካለች፡፡ እኔ በሆዴ ተንበልብዬ የሳይንስ የቤት ሥራዬን እጭራለሁ፡፡
መረተ የመጨረሻዋን ጉርሻ ውጦ በኒኬል የቀረበለትን ውሃ ሲጨልጥ አያቴ ጸሎታቸውን ጨርሰው መቁጠሪያቸው ላይ ምራቃቸውን በለሆሳስ በትነው ፊታቸውን ቀባቡ፡፡
‹‹እንደው ምን ቢያደርጉህ ይሻላል አንተዬ? ድሮም ሠፈርተኛው ከየትም አምጥቶ አያወራም፡፡ ልጅሽ ሊሰልም ነው ሲሉኝ አያደርገውም የኔ ልጅ እያልኩ እመልስ ነበር፡፡ እውን እንደው መስጊድ ገባህ?››
ማርታ ተረቷን አቆመች፡፡ እኔም የቤት ሥራዬን ተውኩ፡፡ መረተ ኒኬሉን ወደ ትንሿ ጠረጴዛ መለሰ፡፡
‹‹ምን ልሠራ መስጊድ እገባለሁ እማ?›› ኒኬሏ ላይ አፍጥጦ።
‹‹አዬ ጉድ አዬ ጉድ… በቁም አይለቀስ አሉ›› አለች አያቴ ወደ ጓዳ እየገባች፡፡
‹‹በቁም አይለቀስ›› አያቴ በሰው ስታዝን የምታጣቅሳት ተረት ነች፡፡ ‹‹ከዚያች ከሼህ ሱሌይማን ልጅ ጋርስ ከንፈር ወዳጅ ናቸው የሚባለው… እውን ወዳጅህ ናት?›› አያቴ ከጓዳ፡፡
ማርታ የሳቅ ቡፍታ ስታሰማ መረተ ገላመጣት፡፡
‹‹ሰዉ’ኮ ብዙ ነው የሚያወራው እማ›› ጣሪያውን እያየ፤ድምጹን ከፍ አድርጎ፡፡
የሼህ ሱሌይማን ልጅ ሼኪው ከጥንት ዘመን ጀምሮ ያቋቋሙት ‹‹አይዳ ዳቦ ቤት›› ውስጥ የምትሠራው ሐውለት የተባለች ደስ የምትል ልጅ ናት፡፡ ጉንጮችሽ የተከፈሉ ሮማን ይመስላሉ የሚባልላት ዓይነት ሳዱላ፡፡ መረተ እየላከኝ እሷ ዘንድ ስሄድ በደስታ ነው፡፡ ሂጃብ ውስጥ የተጠቀለለው ቀይ ክብ ፊቷ ላይ የተሰኩት ትላልቅ ዐይኖቿ፤ ችፍርግ ቅንድቦቿና ቀጥ ለማለት ጀምሮ በድንገት የተቆረጠው አፍንጫዋ፡፡ ይሄ ሁሉ ተደማምሮ ፍልቅልቅ ፈገግታዋን ይፈጥራል፡፡ በጥቁር ልብሷ ውስጥ ክብ ፊቷን ያየ ተገራሚ፣ የጥቅምት ጽጌ ትመስላለች ቢል ማንም አጋነንክ አይለውም፡፡ ከአባያዋ እንኳ የሆነ የማላውቀው ዓይነት የሰንደል መዓዛ ይፈልቃል፡፡ አንዳንዴ ሐውለት ከሚሏት አበባ ቢሏት እያልኩ አስብ ነበር፡፡           
በማግሥቱ ጓደኛዬ ክፍለ ዮሐንስ ቤት ስጫዎትና የእጅ ሥራ ትምሕርት የቤት ሥራ ሥንሠራ ቆይቼ ቤት ስደርስ አንዋርና ስሜነህ ቴኒስ ይጫወታሉ፡፡ መረተ መሀል ቆሞ ይዳኛል፡፡ ፈቀቅ ብሎ ያሉት ሁለት ጆተኒዎች በወጣቶችና ታዳጊዎች ተከበዋል። ጆተኒዎቹ ሲንገጫገጩ፣ ኳሶች ተጠልዘው ጎል ሲሆኑ ወይ ሲሳቱ፤ ልጆች ሲጯጯሁ ይሰማል፡፡ ልክ ሲያየኝ ነጥቦቻቸውን ነግሮኝ ወደ ቤት ገባ፡፡ አንድ ሁለት ነጥቦች እንደተቆጠሩ መረተ ተመልሶ መጣና የኤፍሬም ታምሩን የዘፈን ካሴት ለሐውለት እንዳደርስለት ላከኝ፡፡
ደብተሬን ሰጥቼው በረርኩ፡፡ ሽፋኑ ላይ ኤፍሬም ዥንጉርጉር ጃኬቱን ደርቦ፣ ወደ ጎን ዘወር ብሎ ቆሟል፡፡ ምንም እንኳ ፎቶው የሚያሳየው ከወገቡ በላይ ቢሆንም ቀኝ እጁን ኪሱ የከተተ ይመስለኛል፡፡
ደረጃው ጋ ስደርስ ዳቦ ቤቱ ውስጥ የመሐመድ አዎል መንዙማ ይሰማል፡፡ የክፍለ ዮሐንስ ታናሽ እህት ሄለን ፌስታል ሙሉ ዳቦ ይዛ ስትወጣ በሩ ላይ ተገናኘን፡፡ ይህቺ ልጅ ቆንጆ ብቻ አይደለችም፡፡ ቁንጅና ነች፡፡ ውበት እንጂ ውብ ብቻ አይደለችም፡፡
ከእኔ በላይ ያለው ደረጃ ላይ ስለቆመች ከእኔ እኩል ልትሆን ምንም አልቀራትም፡፡ በቀኝ በኩል እንድታልፍ አስቤ ወደ ግራ ገለል ስልላት፣ እሷም በዚያው አቅጣጫ መጥታ ልንላተም ጥቂት እስኪቀረን ተቀራረብን፡፡ ከጀርባ ሐውለት ሳንቲሞች ወደ መሳቢያ ስትከት ትታየኛለች፡፡ ፈጠን ብዬ ወደ ቀኝ ስሄድ፣ እሷም እንደ እኔ አስባ መሰለኝ እንደገና ልንጋጭ፡፡ ዓይነ አፋሯ ሄለን አንገቷን ደፍታለች፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ ሁለቴ ከግራ ቀኝ ተመላልሰን ፈገግ እያልኩ ወደ ውስጥ  ገባሁ፡፡
‹‹ምን ያደናብርሃል? ፍቅር ያዘሽ እንዴ?››
‹‹ማ? እኔ? ፍቅር አይደለም የተላጠ ኤሌክትሪክ አይዘኝም›› አልኳት፤በዚያን ሰሞን ተመራጭ ዘይቤ፡፡
‹‹አሂሂ… እኛም እንል ነበር…
ፍቅር ያዘኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር
እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አርጎን ነበር››
ግጥሙን እንደማንጎራጎር እያለች ፊቷን አዙራ መደርደሪያው ላይ የተቀመጠውን የመሐመድ አዎል መንዙማ ድምፁን ቀነስ አደረገችው፡፡ ሆኖም ዝየራውን መስማት ይቻላል፡፡   
ድም ድም ድም ድም ድም……
በሩህ በቀልቡ ሐድራው ሀልገባ
ምንም በመንገር ሚስጥር አይገባ፡፡
በቀበሌው ሳይንጎራደድ
መች ይገባዋል የኛ ጨዋታ
ጠዋት የለከፈው ትልቅ በሽታ
ይቅር ተወው መች ይሆናል ጓድ፡፡
ድም ድም ድም ድም ድም……
መልዕክቱን አድርሼላት ባልኮኒውን ተደግፌ እያዋራችኝ እያለ፣ አንድ ጠይም ጢማም ሰው ወደ ዳቦ ቤቱ በር ተጠግቶ ሰላምታ ሰጠ፡፡
‹‹አሰላም አለይኩም››
‹‹ወአለይኩም ሰላም አህመድ ያሲን›› ካሴቱንና ፍልቅልቅነቷን በምን ፍጥነት እንደደበቀችው አላውቅም፡፡
‹‹ሼክ ሱለይማን የሉም?›› የተናገረው የአማርኛ ቃላትን ቢሆንም አረብኛ የሚያወራ ይመስል ነበር፡፡
‹‹የለም፡፡ አህመድ ሙሳን ጠይቄ ልምጣ ብሎ አሁን ወጣ››
‹‹ነው እንዴ፡፡ እኔማ ሂደን እንጠይቀው ልላቸው ነበር አመጣጤ፡፡ በይ እደርስባቸዋለሁ››
አህመድ የተባለው ሰውዬ ወደመጣበት ከመመለሱ ተረቤን ጀመርኩ፡፡
‹‹ምንድን ነው፤ ኒካ ልሠርላት ምናምን ሊላቸው ነው መሰለኝ ፋዘርሽን››
‹‹ሂድዛ ምን ይመስላል ይሄ፡፡ መርዬ ነው ኒካ የሚያስርልኝ››
*   *   *
መረተ ሰልሟል፡፡ ለአያቴ መንገር ግን ፈርቷል፡፡ አያቴ ማን እንደነገራት አላውቅም ሰምታለች፡፡ አንድ የሰንበት ማለዳ አያቴ ከቤተ ክርስቲያን እስክትመጣ ይጠብቃል፡፡ ክፍሉ ውስጥ ሆኖ ጠራኝ፡፡ ስሄድ አልጋው ላይ ቁጭ ብሎ ካሴት በእስክርቢቶ ያጠነጥናል፡፡
‹‹እማ መጣች እንዴ?››
‹‹ኸረ አልመጣችም››
‹‹እሺ ስትመጣ ንገረኝ››
ተመለስኩ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ እንደጠራኝ ሁሉ ያወቀ አልመስል አለኝ፡፡ ተጨንቋል፡፡ የሆነ ነገር ሸተተኝ፡፡ ድምፅ አወጣጡ ተቀይሯል፡፡ ፊቱ ላይም ፍርሃት የመሰለ ነገር አይቻለሁ፡፡ ሁኔታው ደስ አይልም፡፡
አያቴ ገብታ ትንሽ ቆይቶ መረተ መጣ፡፡ ሳየው ትዕዛዙን አስታውሼ ስደነግጥ አየኝ፡፡ ሊናገረኝ የነበረውን ወዲያው መለሰው፡፡ እንዲህ ነው፡፡ ጥፋታችንን እስካወቅንና ይቅርታ እስከጠየቅን ድረስ ነገሩን ለመተው አይቸገርም፡፡  
‹‹ደህና አደርሽ እማ? ምነው አረፈድሽ ዛሬ?››
አያቴ ከቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ጨርሳ በዚያው ልጇ ሐረግ ቤት ሄዳ አረፋፍዳ መምጣቷ ነው፡፡ ሐረግ አንድ ሌላ ብዙነሽ ከምትባል አክስቴ ጋር መንታ ነበረች፡፡ ያይኔ አበባ (ብዙነሽን ቤት ውስጥ የምንጠራበት ስም) ከሰባት ዓመት በፊት የሠርጓ ቀን በተቆረጠበት ዕለት በድንገት ስትሞት ከባድ ሀዘን ሆኖ ነበር፡፡ አያቴ ደክሟት አልጋዋ ላይ ጋደም ብላለች፡፡ እኔና ሄኖክ ከቤተ ክርስቲያን በመሐረቧ ቋጥራ ያመጣችልንን ‹‹የሰንበት ቂጣ›› እየተሻማን ነው፡፡ መረተ ወደ ጓዳ የሚያስገባው በር አጠገብ ያለች አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀመጠ፡፡ ሄኖክ ቂጣውን ይዞ ወደ ውጭ ወጣ፡፡ ሁሌም እንደሚያደርገው ከውሻው ጋር ተካፍሎ ሊበላ ነው፡፡
‹‹እግዚሃር መስጌን፤ እንዴት አደርክ ደርዬ? ሐረግዬ ጋ ሄጄ ነውኮ፡፡ ልጆቹም ሲናፍቁኝ ልያቸው እስቲ ብዬ… ደሞ ያቺ ሠራተኛዋ ጥላት ሄዳለች… ምነው አሞሃል እንዴ? ቁርስ በላህ?››
‹‹በልቻለሁ እማ፡፡ ሠራተኛዋ ደሞ መቸ ሄደች?››
‹‹አልሰማህም አንዴ? ይሄው ሁለት ሳምንት ሙሉ ሥራ እንኳ መች ትገባለች… መንታ ልጅ ማሳደግ እንዲህ ቀላል ነው? እኔ ጋ እየመጡ ይዋሉ አንቺ ለምን ሳትሠሪ ትውያለሽ ብል እሺ አልል አለች፡፡ በቃ ሰለሞን… ጣ! ማነው መረተ ይፈልግልሻል ብያታለሁ››፡፡ መረተን ስትጠራ ሁሌም ተሳስታ ሟች የበኩር ልጇን ሰለሞንን ትጠራለች፡፡
‹‹ቤት ተከራይቼ ልወጣ ነው እማ››
አያቴ ከተጋደመችበት ክንዷን ተደግፋ ተነሳች፡፡ በትናንሽ አተኳሪ ዓይኖቿ አፈጠጠችበት፡፡ መረተ በተከፈተው በር ወደ ውጭ ያያል፡፡
‹‹አልሰማው ጉድ የለኝም መቸም ዘንድሮ፡፡ ምን ጎሎብህ ነው ኪራይ የምትገባው?››
አያቴ ጎን አልጋው ላይ ቁጭ አልኩ፡፡  
‹‹ያው መቼስ ልጅ እንደሆኑ አይቀር እማ… ዞሮ ዞሮ እኮ መውጣቴ አይቀርም››
‹‹ምን አደረግኩህ ልጄ? ምን ጎሎህ ነው እዚህ ሌላ ቤት የምትከራየው? አገባህ እንዴ? መቸስ ማተብህን ስትበጥስ ካልሰማሁ አግብተህም ይሆናላ፡፡ ምነው ምን ሆንክ የኔ ልጅ? ምን አደረግኩህ?››
የግራ አውራ ጣቷን ጥፍር በጥርሶቿ መቀርጠፍ ጀመረች። አየኋት፡፡ ትናንሽ ዓይኖቿ ውስጥ እንባ አግቷል፡፡ መሬት ላይ አፍጥጣለች፡፡ አዝናለች፡፡
‹‹እንዴ እማ… ምን ማለትሽ ነው? ኸረ እንደዛ አትበይ… እንዴ…››
የሰማችው አትመስልም፡፡ ብትሰማውም የተናገረው ፍሬ ነገርም አልነበረም፡፡ እንዳቀረቀረች ነው፡፡ ከዓይኖቿ እንባ ቀስ እያለ ይወርዳል፡፡ ቀዝቃዛ ይመስላል፡፡ እርጋታው ቀዝቃዛ ያስመስለዋል፡፡ ተደበርኩ፡፡ መረተን በትንሹ ጠላሁት፡፡ አሁን ይቺን ሴት ማን ጤነኛ ሰው ሊያስለቅስ ይነሳል?
ዘላለም ከመሠለ ፀጥታ በኋላ መረተ እየተጎተተ ተነሳ። እምብዛም በማይሰማ ድምጽ ‹‹መጣሁ›› ብሎ ወደ ውጭ ሊወጣ ጀመረና በሩ ጋ ሲደርስ የሆነ ነገር እንደረሳ ሁሉ ቆም አለ፡፡  ፊቱን በመጠኑ ወደ ግራ መለስ አድርጎ በመርዶ ነጋሪ ድምጸት ተናገረ፡፡
‹‹ስለ ሐውለት የሰማሽውም ዕውነት ነው እማ›› ዞር ብሎም ሳያይ በፍጥነት ወጣ፡፡ የሚባባስ ሀዘኗን ለማየት አይችልም፡፡
‹‹መረገም እኮ ነው፤ ተረግሜ ነው፡፡ እንደው ምን በደልኩ እናንተዬ፡፡ ምን አደረኩኝ ወላዲተ አምላክ? ወንድ ልጅ አይውጣልሽ አልከኝ ምነው መድኃኔያለም… ምነው ፈጣሪዬ… ምነው…››
አምርራ አለቀሰች፡፡ አዘንኩላት፡፡ ሐውለትና መረተ አንድ ላይ ደስ ቢሉኝም የእነሱ ጉዳይ የምወዳት አያቴን ሲያስከፋ ግን ደበሩኝ፡፡ እንባዬን አመጣችው፡፡ አያቴ ስታማርር ሰምታ ማርታ ከወደ ጓዳ መጣች፡፡ እኔ አያቴ ጎን ተሸጎጥኩ፡፡ ፊቴን በነጭ ቀሚሷ ከልዬ ዓይኔ ውስጥ ያጋተውን ዕንባ ለመዋጥ ተጣጣርኩ፡፡     
ማርታ ለአያቴ ያላት ፍቅር ከባድ ነው፡፡ እናታችን ከአገር ከወጣች በኋላ ማርታ አክስታችን ሐረግ ጋር ጥቂት ኖራ ነበር፡፡ ግን የአያቴ ነገር አልሆን ብሏት ሳምንት ሳትቆይ ነበር የተመለሰችው፡፡ በአያቴ የግራ ጎን ተቀመጠችና አቀፈቻት። በግራ እጇ ትንሽ ጭልፋ ወይም ትልቅ ማንኪያ የመሰለ ነገር ይዛለች፡፡ የአበሻ ጎመን ውስጥ ተነክሮ እንደነበር ላዩ ላይ የተለጣጠፉት የቅጠል ቁርጥራጮች ይናገራሉ፡፡ ማልቀሴ እያሳፈረኝና የአያቴ ማዘን አንጀቴን እየበላኝ ተንሸራትቼ የአያቴን ታፋ ተንተርሼ ተጋደምኩ፡፡
‹‹ነገረሽ አይደል እማ?››  
‹‹ለሰው እንኳን ክፉ አስቤ አላውቅ… ይሄው ማርያም ምስክሬ ናት አውቄ ሰው ላይ የሠራሁት ተንኮል የለም…. እንደው ሳላውቅ ላጠፋሁት ይሄን ሁሉ… ፍርዱ ግን አልበዛም? አሁን አደጉ፣ አሁን ደረሱ ስል ልጆቼን ሁሉ ከጎኔ የሚያሸሽ እርግማን እንጂ ምን ይሉታል? እንደው ምን ይሉታል? አንቺ ደሞ የመቸ ሚስጥረኛው ነሽ?››
‹‹አይዞሽ እማ እኛ አለን አይደል? ደሞ እዚሁ ሠፈር ነውኮ… የትም ርቆ አይሄድም››
‹‹እህም! ተከራይቶ ጨርሶ ነው የሚነግረኝ?››
‹‹ፈርቶሽ’ኮ ነው እማ፡፡ በጣም ነው የሚያስብልሽ… ጨንቆት ነው››
‹‹ካሰበልኝ ለምን ትቶኝ ይሄዳል? አንድ የቀረኝ ወንድ ልጅ እሱ እንደሆነ እያወቀ እንዴት እንዲህ ያደርጋል? ቢጨነቅልኝ ነው? ተይው እስቲ… እም… በቁም አይለቀስ አሉ››
‹‹እንዴ እማ ሄኖክና ጥላሁን አይቆጠሩም? አንተ እንደ ሴት ስትቆጠር ዝም ትላለህ?›› ራሴን በግራ እጇ መታ አደረገችኝ። አያቴን ለማሳሳቅ እየጣረች ነው፡፡ ማርታ ሁሌም የቤታችን ሳቅ ነች፡፡
‹‹ምን እቴ እነኚህ አንድ ፍሬ ልጆች… ቁመታቸው ተመዘዘ  ብለሽ ነው? ቆይ ልጅትንስ ሊያገባት ነው ምንድን ነው?››
‹‹ይጋባሉ እማ››
‹‹እንደው ሼህ ሱሊማን ሲሰሙ ምን ይሉ? ከሠፈርተኛም ሊያጣላኝ ነው፡፡ ቆይ ግን እንደው የዕውነት ሰለመ? ማተቡን በጠሰ?››
‹‹ዋናው እነሱ መዋደዳቸው ነው፡፡ ደሞ ቆንጅዬ ልጅ ናት… አይደለች እንዴ እማ?›› ማርታ እንደ መሳቅ እያለች፡፡
‹‹ቁንጅናዋስ አይጠየቅም፡፡ አበባ የመሰለች ልጅ ናት››
*   *   *
መረተ ቀስ በቀስ እየራቀ ሄደ፡፡ ቤት መጥቶ ምግብ መብላቱን እየቀነሰ ሄደ፡፡ ሐውለት እንደነገረችኝ ማብሰል ጀምሯል፡፡ አያቴ መረተን በቀጥታ ማናገር ትታለች፡፡ ግን በየቀኑ ትጠይቃለች፡ መጥቶ ምሳውን በላ?
አንድ ሦስት ቀን ጠፍቶ ቆይቶ የአብይ ጾም መያዣ እሁድ ምሽት መረተ ቤት መጣ፡፡ ማርታና አያቴ ከጠዋት ጀምረው የሥጋ ዘር ቤት ውስጥ እንዳይተርፍ አድርገው ሲለፉ ነው የዋሉት፡፡ ሥጋ ተጠብሶ፣ ሥጋ ተቀቅሎ፣ ሥጋ በከፊል ተጠብሶ፤ ሥጋ ጥሬውን፤ ሥጋ አንጀት ውስጥ ተጠቅጥቆና ተጠብሶ (ሥጋ ሥጋ ለብሶ) ብቻ ሊዘጋጅ በሚችለው መልኩ ሁሉ ተሰናድቷል፡፡ በየዓመቱ እንዲህ ሲለፉ ሳይ ሠርግ የሚደግሱ ነው የሚመስለኝ።
በተለይ ቋሊማውን ከጠዋት ጀምሮ ስጠቀጥቅ ውዬ አንጀቴ ውስጥ አንጀት ተከማችቷል፡፡ አልጋዬ ላይ እገላበጣለሁ። እነሳለሁ፡፡ መልሼ ልተኛ እሞክራለሁ፡፡ ቁንጣን አሸኝ፡፡ ራት መብላት ሁሉ አላሰኘኝም፡፡
ከመኝታ ቤት ስመለስ አያቴና መረተ ያወራሉ፡፡ ራት ላይ ሁላችንም አለን፡፡ መረተ መኖሩ ልክ ምንም እንዳልተፈጠረና አብረን እንደምንኖር ዓይነት ስሜት ፈጥሯል፡፡ ማርታ አሁንም አላረፈችም፤ምግብ ታቀራርባለች፡፡ ደስ እንዳላት ከፊቷ ያስታውቃል፡፡ አያቴም መረተን የምታዋራው ቤቱ ውስጥ ባለው ደስ የሚል ድባብ ተነሳስታ መሰለኝ፡፡ ሄኖክ በማስታጠቢያ  ሙቅ ውሃ ይዞ ሁሉንም እየዞረ አስታጠበ፡፡ እኔ ጋ ሲደርስ እንደማልበላ ስነግረው አያቴ ተቆጣች፡፡ ሄኖክ ምን ቸገረኝ በሚል ዓይነት ትከሻውን ሰበቀ፡፡ ተመልሶ ሊሄድ ሲል ጠራሁትና ደስ ይበላት ብዬ ታጠብኩ፡፡
‹‹ባለፈው እንደነገርኩሽ ቶሎ እንድንጋባ ይፈልጋሉ››
‹‹እንደው እኔ ግን ጥድፍ ጥድፍ ማለቱ አላማረኝም››
‹‹አይ እማ… አንቺ ስላልሰማሽ እንጂ ስንት ዓመታቸው’ኮ›› ማርታ ወደ ጓዳ እየተመለሰች፡፡
‹‹ቁም ነገር ነው የያዝነው አንቺ… እንደው ታዲያ እኔም አጉል ጊዜ ሆነብኝ… የሐረግን ያህል ባይሆንልኝ እንኳ ደንበኛ ሠርግ ደግሼ ካልዳርኩህማ ምኑን እናትህ ሆንኩ››
‹‹ነግሬሽ የለ እማ… አንቺ ምንም አታስቢ፡፡ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቷል፡፡ ሼህ ሱለይማን ጥሩ ሰው ናቸው፡፡ አልነገርኩሽም እንጂ ቴኒስና ጆተኒውንም የገዙልኝ እኮ እሳቸው ናቸው››
አያቴ መረተ ላይ ቂም ይዛ በሠርግ ካልዳርኩህ ማለቷ ገረመኝ፡፡ ግን ደግሞ እኛ ፊት አላዋራውም ትላለች እንጂ ለብቻቸው ሲሆኑ እንደሚያወሩ ገባኝ፡፡ ምናልባት እኛ ፊት የማታዋራው እንደ መቀጣጫ እንዲሆን አስባ ይሆናል፡፡ ራት ከተበላም በኋላ ስለ ሠርጉ ብዙ ዝርዝር ነገር ሲያወሩ አመሹ፡፡  
ሠርጉ የሚደገሰው እነ ሐውለት ቤት ቢሆንም እንኳ ሁዳዴ እስኪወጣ መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ ልማዱ እንደዚያ ነው፡፡ ሙስሊምም ይሠርግ ክርስቲያን የአንዳቸው ጾም ወቅት ከሆነ እስኪያልቅ ይጠብቃሉ፡፡ ሠርጉ የዳግማዊ ትንሳዔ ዕለት ዋለ። ሰፊ ሠርግ ነበር፡፡
በማግስቱ የሠርጉ ዳስ ተነስቶ የመልስ ግብዣው የተደረገው ሰፊው ግቢያቸው ውስጥ ነው፡፡ የግቢው በር ወለል ብሎ ተከፍቷል፡፡ በየጥጉ የተንጠለጠሉት ባለ መቶ ሻማ አምፖሎች ከጨለማው ጋር ይታገላሉ፡፡ ከላይ የተደፋው ኢንዲጎ ሰማይ ላይ ከዋክብት ብልጭ ድርግም ይላሉ፡፡ ከታች የሰዎች ድምጽ አናሳ ባቢሎን ፈጥሯል፡፡ ከሠርጉ ቀን በጣም ያነሰ ቢሆንም ሰፊው ግቢ በሰዎች ተሞልቷል፡፡ በሩን እንዳለፉ አንድ ደልደል ያለ ወጣት  (ብዙ ጊዜ እነ ሐውለት ዳቦ ቤት አጠገብ ያለች ዛፍ ሥር ቁጭ ብሎ አየዋለሁ) የሚገቡትን ሰዎች በየኃይማኖታቸው እየለየ፣በግራውና በቀኙ እንዲሄዱ አቅጣጫ ይጠቁማል፡፡ የማያውቃቸው ሰዎች ሲያጋጥሙት ሙስሊም ወይ ክርስቲያ መሆናቸውን ይጠይቃል፡፡
ደብረ ገሊላ የተባለ ሰፈር ውስጥ ለሚኖሩ አንዲት የሩቅ ዘመዳችን ጠላ ላደርስ ተልኬ አምሽቼ ነው የደረስኩት፡፡ በቁጥር አነስ የሚሉት ክርስቲያን ታዳሚዎች የተቀመጡት በቀኝ በኩል ነበር፡፡ ጓደኞቼ ያሉበትን ፈልጌ በሰዎች መሀል እየተሻሸሁ አልፌ ክፍለ ዮሐንስ ጎን ተቀመጥኩኝ፡፡
‹‹የት ጠፋሽ ነፍሴ? ወንድምሽ ሲያገባ ትደበቂያለሽ እንዴ?››
‹‹ሚስትህ ሠፈር ተልኬ ሄጄ ነው’ኮ:: ቆያችሁ?››
‹‹ሃሃሃ… እኛማ ከትናንት ጀምሮ እዚሁ ነበርን››
ፊትለፊት መድረኩ ይታየኛል፡፡ ደማቅ ብርሃን አርፎበታል። ብልጭልጭ ወረቀት ላይ በጉልህ የሚታይ ጽሑፍ ይታያል፡፡ የሚታዩኝ ፊደላት ጥቂቱ ቢሆኑም ‹‹የአቶ መረተ አሰፋ እና የወ/ት ሐውለት ሱለይማን የጋብቻ ስነ ስርዓት›› እንደሚል አውቄአለሁ፡፡ መረተ ነጭ ሱፍ አድርጓል። ልብሱ ከተቀመጠበት ነጭ የሙሽራ ወንበር ጋር ተመሳስሎ የሚታየው ጠይም ፊቱ ብቻ ነው፡፡ ሐውለት እንደ ሁልጊዜው አምሮባት ጎኑ ተቀምጣለች፡፡ መድረክ ላይ ጠይሙ ጢማም ሰው ይታየኛል፡፡ ከሰውየው ጀርባ ሙሽሮቹና ሚዜዎቻቸው። ሰውዬው ምርቃት እየሰጡ ነው፡፡
ክፍለዮሐንስን ጠጋ ብዬ በጆሮው ጠየኩት፡፡
‹‹ስማ.. ማነው ይሄ ሰውዬ?››
‹‹ኡስታዝ አሕመድ ያሲንንን አታቃቸውም?››
ጮክ ብሎ መመለሱ፣ ደግሞም የሆነ የአረብኛ ቃል መናገሩ አስደንግጦኛል፡፡
‹‹እ… አይ… አላውቃቸውም፡፡ ደሞ ኡስታዝ ምንድን ነው?›› ድምፄ ዝቅ እንዳለ ነው፡፡
ክፈለ ዮሐንስ እያፏጨ አጠገቡ ወደተቀመጠው አንዋር ጠቆመኝ፡፡
‹‹መምህር ማለት ነው›› አለ አንዋር፤ ወደ እኔ ለአፍታ አየት አድርጎ፡፡ ግራና ቀኝ ተገላመጠና ደብቆ የያዛትን ኩባያ አውጥቶ ተጎነጨ፡፡ አንዋር ሁሌም ድግስ ላይ ከእኛ ጋር ነው፡፡ ሁሌም በግልጽ ግን ተደብቆ  ጠላ ነው የሚጠጣው፡፡ የሚገርመኝ ጠላ ሲጠጣ እንኳ ኩባያውን በግራ እጁ አይዝም፡፡   
ክፍለ ዮሐንስ ከጀርባችን ከተቀመጡት የቀበሌ ሦስት ልጃገረዶች ጋር ይጎነታተላል፡፡ ኡስታዙ ጉዳያቸውን ጨራርሰው ወደ መቀመጫቸው ሲመለሱ የታዳሚው ጭበጨባ አጀባቸው። ቀድሞ ያላየሁት የክፍለ ዮሐንስ ታላቅ ወንድም በዛብህ ከሙሽራው ጎን ተነሳና መናገር ጀመረ፡፡  
‹‹ቆይ ግን ክፍሌ፤ ብራዘርሽ እኩዮቹን ሁሉ ሲድር እሱ መቼ ነው የሚያገባው?›› አልኩት፡፡
‹‹ምን አውቃለሁ በናትህ…›› ክፍለ ዮሐንስ ሳቀ፡፡ ቀልድ ሊናገር ሲል ቀድሞ ነው የሚስቀው፡፡
‹‹መብራት ሀይል እንኳ አፀድን ጠየቃት’ኮ… በቃ መቆሙ ካልቀረ የኤሌክትሪክ ፖል እናድርገው ፍቀጂልን ምናም አሏት››
አፀድ እናታቸው ነች፡፡ ሙሉ ስሟ አጸደማርያም ይባቤ ነው፡፡ ስሟን ስወደው፡፡ ዝም ብሎ ቤት የሚመታ ምናምን ይመስለኛል፡፡ ከልጆቿ ሰምተን ነው መሰል እኛም አጸድ እያልን ነው የምንጠራት፡፡ አንዳንዴ ስትቃለደን ‹‹የምን አባክ አንጠልጥሎ መጥራት ነው አንተ… ጓደኛህ አደረከኝ አይደል? እትዬ አትልም? ቆይ ባልመዘልግህ›› ብላ እጇን የውሸት ለቁንጥጫ አዘጋጅታ ትጠጋናለች፡፡ እየሳቅን የውሸት እንሸሻለን።  
ርቦኛል፡፡ የሚያስተናግደኝ ሰው በዓይኔ ልፈልግ ወደ ግራ ዞር ስል ሄለን ቁርጥ እንጀራ የሞላው ትሪ ይዛ አጠገቤ ደረሰች፡፡ ሰሀኖች በአፋቸው ተደፍተውበት እንጀራው በከፊል ተከልሏል።
‹‹እንዴ እኔማ በቃ ግብዣው ካለቀ ደረስኩኝ ብዬ ተስፋ ቆርጬ ነበር… ደሞ እንዴት እንደራበኝ››
‹‹ጠላ ትጠጣለህ አይደል?››
‹‹ቡቅሬ የለም?›› ሁለት የእንጀራ ቁርጥ አነሳሁ፡፡
‹‹እሺ አመጣልሃለሁ… ጨምር ከእንጀራው››
‹‹ይብቃኝ ባክሽ››  
በዛብህ ለሙሽራዋ የዳቦ ስም አውጡላት ብሎ ወደ ታዳሚው ሲማትር ወደ መሀል አካባቢ የተቀመጠው የሰፈራችን አንደኛ ሰካራም ብዙአየሁ ጮክ ብሎ፤ ‹‹የዳቦ ስም? ‘አይዳ ዳቦ’ ትባል ሃሃሃ…››፡ አካባቢው የተቀመጡት ሰዎች ሳቁ፡፡ ትላልቆቹ ገላመጡት፡፡ ክፍለ ዮሐንስ እዚያው አብረን የሰማነውን ጨዋታ ለእኛ ደገመልንና ደግመን ሳቅን፡፡    
‹‹እዚህ ጋ የሙሽራው እናት ይታዩኛል፡፡ የሙሽራው እናት ለሙሽሪት የሚያወጡትን ሥም እስቲ እንስማ…››
ፊት አካባቢ የተቀመጠችው አያቴ የሆነ ነገር ተናገረች። ደካማ ድምጿ ከጥቂት ሜትሮች በላይ መሄድ አልቻለም፡፡ አጠገቧ የነበሩ ሁለት ሦስት ሰዎች የተናገረችውን አስተጋቡ፡፡ በዛብህ አያቴን ለመስማት በጥቂቱ ጎንበስ ካለበት ፈገግ ብሎ ተነሳ፡፡
‹‹በዕውነት የሙሽራው እናት ለዚህች አበባ ለመሰለች ሙሽሪት ያወጡት ስም ደስ የሚያሰኝ ነው…››
ሄለን ተመልሳ መጣች፡፡ የዘረጋችልኝን ኩባያ በግራ እጄ ተቀበልኳት፡፡ ኩባያውን ከነእጇ ያዝኩት፡፡ ቀና አልኩኝ። እያየችኝ ነበር፡፡ ከላዩ ሰማዩ እንደ ጃንጥላ ተደፍቶባታል፡፡ ሰማዩ ላይ ከጭንቅላቷ ጎን እሳት አየሁ፡፡ የሆነ ብልጭ ብሎ ወዲያውም እልም ያለ ነበልባል፡፡ በዕይታዬ እንግዳነት ተደምሜ ለአፍታ ማኘኬን አቋረጥኩ፡፡ ፈገግ አለች፡፡  አፌ ውስጥ ያለውን ጉርሻ በፍጥነት ዋጥኩ፡፡
‹‹… ‘ያይኔ አበባ’ እላታለሁ ብለዋል…››
የተጠራው ስም ወዳለሁበት ቦታ መለሰኝ፡፡ ደማቅ እልልታና ጭብጨባ ተሰማ፡፡ መረተና ሐውለት ተያዩ። ሳቅ ብላ አንገቷን ደፋች፡፡ ሐውለት ትክክለኛ ስሟን ያገኘች መሰለኝ። እኔም ስም አውጣላት ብባል ይሄን የመሰለ ስም እንደምሰጣት አልጠራጠርም፡፡ ይሄን እያሰብኩ ሄለን ከአጠገቤ ስትሄድ ልብ አላልኩም፡፡ በድንገት መሰወሯ ቅድም ካየሁት እሳት ጋር ተደማምሮ መሰለኝ የሆነ ምትሃታዊ ስሜት ተሰማኝ። የሠርግ ቤቱ የሞቅሞቅታ ድባብም ቀላል አልነበረም፡፡ በተከፈለ ልብ ሄለን ወደሄደችበት አቅጣጫ አንድ ሁለቴ ተገላምጬ አማተርኩ፡፡    
አያቴ የምትወዳት ልጇን ስም ለወንድ ልጇ አዲስ ሚስት ስትሰጥ በመረተ ላይ ቂም እንዳልያዘች ገባኝ፡፡በሚወዱት ልጅ ላይ ቂም አይዙም፡፡ ቂም አልነበረም፡፡ አዝናበታለች። የሚወዱት ሲያሳዝን ያኮርፉታል እንጂ አይቀየሙትም፡፡ ኩርፊያ ነበር፡፡ ዛሬ ይሄም አልፎላታል፡፡ ታላቅ ወንድማችን መረተም እንደ በፊቱ ቅርባችን ነው፡፡ የመረተ ወንድ ልጅም ቤት ውስጥ ከሄኖክ ጋር ሲጫወት ይውላል፡፡ ሐውለት ሰዓት እየጠበቀች የሚበላውን ይዛለት ትመጣለች፡፡    

Read 4124 times