Saturday, 25 April 2015 10:10

ወደ ሳውዲ የተላከችው ወጣት ደብዛ መጥፋት እያወዛገበ ነው

Written by 
Rate this item
(6 votes)
  • ከ2 ዓመት በላይ ወጣቷ የት እንደገባች አልታወቀም
  • ኤጀንሲው የተጣለበት የፈቃድ እገዳ ተግባራዊ አልሆነም

    ከሁለት ዓመት በፊት አል-ኢስማኤል በተባለ የውጪ አገር የግል ሥራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ በኩል በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኮንትራት ውሏ ፀድቆ ወደ ሳውዲ አረቢያ የተላከችው ወጣት ደብዛ መጥፋት እያወዛገበ ነው፡፡ ወጣቷ ላለፉት 27 ወራት የት እንደገባች የሚያመለክት አንዳችም ፍንጭ አልተገኘም፡፡ ሀያት አሊ መሐመድ በሚል ስም የካቲት 27 ቀን 2005 ዓ.ም ወደ ሳውዲ የተጓዘችው ወጣቷ፤
ከአገር ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ከቤተሰቦችዋ ጋር አንዳችም ግንኙነት  ባለማድረግዋ ቤተሰቦችዋ የትና በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ሊያውቁ እንዳልቻሉ ይገልፃሉ። ወደ ሳውዲ የላካት ኤጀንሲ ሀያት አሊ ያለችበትን ሁኔታና የት እንደምትገኝ እንዲያሳውቃቸው ቤተሰቦቿ ኤጀንሲውን ቢጠይቁም ኤጀንሲው ምላሽ ባለመስጠቱ ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ማመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ኤጀንሲው ወጣቷ ያለችበትን ሁኔታ በአፋጣኝ ተከታትሎ እንዲያሳውቅ ያሳስባል፡፡ ኤጀንሲውም ሳውዲ ድረስ ሄዶ ወጣቷን ለማግኘት ቢሞክርም እንዳልተሳካለት ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳውቋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ሀያት አሊ መሐመድ የተባለችው ወጣት በምን ሁኔታና የት እንደምትገኝ ተጣርቶ ምላሽ እንዲሰጠው ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቆንስላዎች ጉዳይ ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ጥያቄ ያቀርባል፡፡
የቆንስላ ጉዳይ ክትትል ቢሮው በበኩሉ፤ ወጣቷ የምትገኝበት ሁኔታ ተጣርቶ እንዲገለፅለት ሪያድ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥያቄ ቢያቀርብም ከኤምባሲው ምላሽ ሊገኝ ባለመቻሉ የሃያት ቤተሰቦች እጅግ በከፋ ሃዘንና ሰቆቃ ውስጥ እንደሚገኙ  የወጣቷ እህት የኔነሽ አያሌው ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ የወጣቷ ደብዛ መጥፋት በእጅጉ ያሳሰባቸው ቤተሰቦች፤ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በተደጋጋሚ የአፋልጉን ጥሪ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን የጠቆመችው የኔነሽ፤ ኤጀንሲው ተግባሩን በአግባቡ ባለመውጣቱ የሥራ ፈቃዱ እንዲታገድ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐምሌ 24 ቀን 2006 ዓ.ም ትዕዛዝ ቢተላለፍበትም ኤጀንሲው አሁንም በስራ ላይ እንደሚገኝ ገልፃለች፡፡ ‹መንግስት ህገ ወጥ ስደትን እቃወማለሁ፤ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደሚፈልጉበት አገር ለስራ መሄድ ይችላሉ› ባለው መሰረት፣ ዕድሉን ተጠቅማ በህጋዊ መንገድ የሄደችው እህቴ፤ ያለችበት ሳይታወቅ ሁለት ዓመት ከሶስት ወራት ማለፉ እጅግ የሚያሳዝንና ስጋት የሚፈጥር ነው ያለችው የኔነሽ፤
“የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተረባርበው እህቴ ያለችበትን ሁኔታ እንዲያሳውቁንና ከስጋት እንዲያወጡን እማፀናለሁ” ብላለች፡፡ ስለጉዳዩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለመጠየቅ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡

Read 5620 times