Saturday, 25 April 2015 10:38

እግዜር ያተረፋት ነፍስ ምስክርነት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከማልታ ባገኘሁት መረጃ፤ በቀደም ከተሰውት ወንድሞቻችን ጋር የነበረ፣ በእግዚአብሔር ቸርነት አምልጦ ትሪፖሊ የገባ ወንድም አግኝቼ ነበር፡፡ እርሱ እንደነገረኝ፤ “በአጅዛቢያና ቤንጋዚ መንገድ ላይ የአይሲስ አራጆች የሊቢያ መንግሥት ወታደሮችን ዩኒፎርም ለብሰው በዚያ የሚያልፉትን ለመያዝ ይጠብቃሉ፡፡
በአካባቢው ወደ ትሪፖሊ የሚጓዙ መንገደኞችን ሲያገኙ ይይዛሉ፡፡ ሱዳኖችና ሶማሊያውያን ሙስሊሞች ናቸው ብለው ስለሚያስቡ ወዲያው እንዲሄዱ ይለቋቸዋል። ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያንን ግን ለብቻ ይይዛሉ፡፡ ከዚያም ሙስሊሞችን ለብቻ፣  ክርስቲያኖችን ለብቻ ያሰልፏቸዋል፡፡ በመቀጠልም ክርስቲያኖችን በኮንቴይነር ውስጥ ከትተው ወዳልታወቀ ስፍራ ይወስዷቸዋል። ምግብ የሚሰጧቸው በየሦስት ቀን ነው፡፡ ሙስሊሞችን ደግሞ ይለቋቸዋል፡፡
በቀደም እለት አይሲስ በባህር ዳርቻ የሰዋቸው ክርስቲያኖች የመስቀል ማህተብ የነበረባቸውን መርጦ ነው፡፡ እነርሱን በተለየ ኮንቴይነር አስቀምጧቸው ነበር።” ይሄንን መረጃ የነገረኝ ሰው ሊገደሉ ተመርጠው ከተለዩት ወገን ነበረ፡፡ ሌሎች በኮንቴይነር ያስቀመጣቸው ክርስቲያኖችም አሉ። ምናልባት ከዚህ የከፋ ዜና እንሰማ ይሆናል። አምላክ ይጠብቀን።
አሁንም የአይሲስ አራጆች የመንግሥት ወታደሮችን ልብስ ለብሰው ሌሎች ስደተኞችን እየያዙ ነው፡፡ይሄ መረጃውን ያደረሰኝ ሰው ሊያመልጥ የቻለው ሌሎች ክርስቲያኖችን በጨለማ ወደ ኮንቴይነሩ ለማስገባት ኮንቴይነሩን በከፈቱበት ጊዜ ነው፡፡ የተወሰኑ ተያዦች አምልጠው ነበር። አንዳንዶች ተያዙ፡፡ ሦስቱ ግን አመለጡ። ሁለቱ የት እንደደረሱ አያውቅም፤ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ቸርነት አምልጦ ትሪፖሊ ገብቷል፡፡
እባካችሁ ሰሞኑን ለመጓዝ የተነሱት ቢያንስ ለጊዜው ይታገሱ፡፡ ሱዳን ያሉትም ከሱዳን አይውጡ። መንገዱ በአይሲስ አራጆች ተይዟል። ለማታለልም የመንግሥት ወታደሮችን ልብስ ለብሰው ድንበር ጠባቂ ይመስላሉ፡፡
እግዚአብሔር በእጃቸው የተያዙትን እንዲታደግ እንፀልይ!!
 (ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ከፌስ ቡክ የተገኘ)

Read 2843 times