Saturday, 25 April 2015 10:50

ሳይንስ፤ “ውሃ በጣም አስታዋሽ እና ታሪክ ዘጋቢ ነው” ይላል

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

 ውሃ ፍቅርና ጥላቻንም ይለያል
     
    ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝን፤ ‹‹የሕፃናት ቊርባን የሥነ ምግብ ባለሙያዎችን አከራከረ›› በሚል የቀረበው ዜና ነው፡፡ በአንድ በኩል፤‹‹ሥጋ ወደሙን ከምግብ መቁጠር ሃይማኖታዊ ነጻነትን እና ሥርዓትን የሚፃረር ነው›› በሚል የቀረበ ሐሳብ አለ፡፡ በሌላ በኩል፤ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ‹‹እንደ ተጨማሪ ምግብ ነው የምናየው›› ያሉ መሰለኝ፡፡ እንግዲህ ይህ ፅሑፍ፤ ይህን ክርክር ዳራ አድርጎ የተፃፈ መሆኑ ነው፡፡ እዚህ የማጫውታችሁ፤ ሳይንስ በውሃ ባህርይ መቸገሩን ነው፡፡ ሳይንስ፤ ‹‹ውሃ ያስታውሳል›› ይላል፡፡
ውሃ ቅርብ - ውሃ ሩቅ
ውሃ በየትም ቦታ ይገኛል፡፡ ለምሣሌ፤ ድንች 80 በመቶ ውሃ ነው፡፡ አንዲት ላም፤ 74 በመቶ ውሃ ነች። ባክቴሪያም 75 በመቶ ውሃ ሲሆን፤ የቲማቲምን ነገር ተውት፡፡ ቲማቲም 95 በመቶ ውሃ ነው፡፡ ቲማቲም ሙሉ በሙሉ ውሃ ከመባል የተረፈው ለጥቂት ነው። የሰው ልጅ ራሱ 70 በመቶ ውሃ ነው፡፡ ከጠጣርነቱ ይልቅ ውሃነቱ ያመዝናል፡፡ የሰውን ልጅ ‹‹የውሃ - ጠጣር›› ምጣኔ ሲታይ፤ አንድ እጅ ጠጣር፣ ለሁለት እጅ ውሃ ነው፡፡ ውሃ በጣም እንግዳ ነገር ነው፡፡ ቅርፅ የለውም፣ ሽታ የለውም፣ ‹‹ትራንስፓረንት›› ነው፡፡
የሰው ልጅ፤ ከአጠገቡ እንዲጠፋበት የማይፈልገው ነገር ውሃ ነው፡፡ ውሃ በዙሪያው ከሌለ ድራሹ ይጠፋል። ውሃ ጣዕም የለውም፡፡ ግን የውሃን ጣዕም አብዝተን እንፈልገዋለን፡፡ ውሃ ሽታ የለውም፡፡ ግን የውሃን ሽታ አብዝተን እንወደዋለን፡፡ ውሃ በጣም የሚፈለግ፤ ነገር ግን እጅግ አደገኛ ነገር ነው፡፡ ውሃ በየዓመቱ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት የሚቀጥፍ ነው፡፡ ሰሞኑን እንኳን በሜድትራኒያን ባህር ያለቀው ስደተኛ ቁጥር ዘጠኝ መቶ የደረሰ መሰለኝ፡፡ ውሃ ይገድለናል። ግን ከእርሱ ጉያ መራቅ አንፈልግም፡፡ ውሃን ዘወትር ስለምናየው፤ አስገራሚ ነገር መሆኑን እንዘነጋለን፡፡ ውሃ የተለየ ነገር ነው፡፡ ስለ ውሃ በማወቅ ስለሌሎች ፈሳሾች ለማወቅ አንችልም፡፡ ስለ ሌሎች ፈሳሾች ያለን ዕውቀት፤ ፈሳሽ የሆነውን ውሃን ለማወቅ ምንም አይጠቅመንም፡፡ ምክንያቱም ውሃ ልዩ ንጥረ ነገር ነው፡፡ ስለ ውሃ ስናውቅ፤ ከውሃ ጋር ዝምድና ስላላቸው ኬሚካሎች ማለትም ስለ <<hydrogen Selenide or hydrogen Sulphide>> ዕውቀት ቢኖረን፤ ውሃ 135 ድግሪፋናይት ሊፈላ የሚችል ወይም በ Room temperature ወደ ጋዝነት ሊቀየር የሚችል ነገር አድርገን ልናስበው እንችላለን፡፡
በሌላ በኩል፤ አብዛኞቹ ፈሳሾች ሲቀዘቅዙ በ10 በመቶ ይኮማተራሉ፡፡ ውሃም በረዶ ከመሆን ደረጃ ሳይደርስ በሚኖረው ቅዝቃዜ ለዓመል ያክል ትንሽ የመኮማተር አዝማሚያ ያሳያል፡፡ ግን ወደ ነጥበ-በረድ (freezing Point) ሲቃረብ በአስገራሚ ሁኔታ መንሰራፋት ይይዛል። ጠጣር ከመሆን ደረጃ ሲደርስ፤ ምግደቱ (volume) በ10 በመቶ ጨምሮ ይንሰራፋል፡፡ ስለዚህ በረዶ በውሃ ላይ ይንሳፈፋል፡፡ በረዶ እንዲህ ዓይነት ባህርይ ባይኖረው ኖሮ፤ በውሃ ገፅ ላይ መንሳፈፉ ቀርቶ ይሰጥም ነበር፡፡ በረዶው እየሰረገ እና እታች ወርዶ እየተቆለለ፤ ውቂያኖሶች ወይም ሐይቆች ከስር ጀምረው በረዶ እየሆኑ ሲመጡ እናይ ነበር። ሆኖም ነገሩ እንደዚያ አይደለም፡፡ በባህር ገፅ ላይ እንደ ቂጣ ተጠፍጥፎ የሚንሳፈፈው በረዶ፤ እንደ ጋቢ ባህሩን ጀቡኖ፤ ሙቀት ከባህሩ እንዳይወጣ አምቆ በመያዝ፤ የባህሩ ውሃ ወደ በረዶነት እንዳይቀየር ያደርጋል፡፡ በዚህ ዓይነት የባህሩን ሙቀት በማቀብ፤ ውሃው ወደ በረዶነት እንዳይቀየር እገዛ ያደርጋል፡፡ በረዶው ባይንሳፈፍ ኖሮ፤ ሙቀት እያፈተለከ፤ የባህሩ ውሃ በቶሎ ነጥበ - በረድ (freezing Point) ላይ ደርሶ፤ ያ የባህር ውሃ ለረጅም ጊዜ ምናልባትም ለዘላለም በረዶ ሆኖ በቀረ ነበር፡፡ ይህም ለህይወት መቀጠል የማያመች ሁኔታን ያስከትል ነበር፡፡
ውሃ፤ የኬሚስትሪን ደንብ እና የፊዚክስን ህግ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው፤ የውሃ ኬሚካላዊ ቀመር H2O ነው፡፡ ይህ ማለት አንድ ትልቅ የኦክስጅን አተም እና ሁለት አነስ-አነስ ያሉ የሐይድሮጅን አተሞችን የያዘ ውህድ ነው፡፡ እነዚህ የሃይድሮጅን አተሞች ከኦክስጅን አተም ጋር በጥብቅ ተያይዘዋል፡፡ ግን ውሃ ጠላቂ ዘሎ ሲገባ ለመከልከል በሚያስችል ኃይል እርስ በእርስ የተጣበቁ አይደሉም፡፡ ሆኖም ውሃ ቱቦ ሆኖ ሽቅብ ሊረጭ የሚችለው ወይም በመኪና መስተዋት ላይ የተንጠባጠበው የዝናብ ውሃ ከሌላ የውሃ እንክብል ጋር እንደ ዛጎል ሲጣመር የምናየው የመተሳሰር ባህርይ ስላለው ነው፡፡ በውሃ ገፅ ላይ ያለው ከፍተኛ የመሳሳብ ዝንባሌ (Surface tension) የተፈጠረው በዚሁ የትስስር ተፈጥሮ የተነሳ ነው፡፡ በውሃ ገፅ ላይ የሚገኙ ሞለኪሎች፤ ከበላያቸው ካሉ የአየር ሞለኪሎች ይልቅ፤ ከእነሱ በታች እና ከጎናቸው ካሉ ሌሎች የውሃ ሞለኪሎች ጋር በከፍተኛ ሁኔታ የመሳሳብ ባሕርይ አላቸው፡፡ ይህም አንዳንድ ጥቃቅን ነገሮችን ለማንሳፈፍ የሚያስችል የኃይል ድርን ይፈጥራል፡፡
ታዲያ የሃይድሮጅን አተሞች ከኦክስጅን አተም ጋር በጥብቅ ቢያያዙም፤ አንዳንዴ ከሌሎች የውሃ ሞለኪሎች ጋር ይተሳሰራሉ፡፡ የውሃ ሞለኪሎች በባህርያቸው ዳንስ የሚወዱ ይመስላሉ፡፡ ለአንድ አፍታ ከአንዱ ጋር ይጣመሩና መልሰው ያን ለቅቀው ከሌላው ጋር ይጣመራሉ፡፡ ሁል ጊዜ የዳንስ ጓደኞቻቸውን ይቀይራሉ፡፡ በብርጭቆ የተሞላ ውሃ ሲታይ እንዲህ ያለ ዓመል ያለው አይመስልም፡፡ ሆኖም በውሃ ውስጥ ያሉ ሞለኪሎች በሰከንድ ውስጥ በቢሊየን ለሚቆጠር ጊዜ የዳንስ አጣማጃቸውን ይቀያይራሉ፡፡ በዚህ መንገድ የውሃ ሞለኪሎች፤ ባህር እና ውቂያኖሶችን ይፈጥራሉ፡፡ ይሁንና ከውሃ ሞለኪሎች በአንድ ጊዜ ተያይዘው የሚገኙት 15 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው፡፡
ውሃ ያስታውሳል
ከሰሞኑ የተመለከትኩት አንድ ዶኩመንታሪ ‹‹ውሃ በዙሪያችን ያለ ነገር ነው፡፡ ግን ስለዚህ አስደናቂ የተፈጥሮ ክስተት ምስጢር በውል እናውቃለን?›› በማለት ይጀምራል፡፡ አያይዞም፤ ‹‹ውሃ ከየት መጣ? ለዚህ ፕላኔታችን ይህን ልዩ የተፈጥሮ ሐብት ያደላት ማን ይሆን?” ሲል ይጤቃል፡፡
‹‹በዚህ በእኛ ዩኒቨርስ ውስጥ ውሃ ያላት ፕላኔት የእኛይቱ መሬት ብቻ ነች፡፡ ግን ይህን ሐብት ማን ሰጣት? ለምን ሰጣት?›› የሚለው የዶኩመንታሪው ተራኪ፤‹‹ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጠን የሚችለው ራሱ ውሃ ብቻ ነው›› ይላል፡፡
ዛሬ በምድር ላይ ያለው ውሃ፤ ገና ከፍጥረት ማለዳ የነበረው ውሃ ነው፡፡ የውሃ ስርዓት ዝግ በመሆኑ፤ የውሃው መጠን አይጨምርም አይቀንስም፡፡ በመሬት ላይ 320 ሚሊየን ኪዩቢክ ማይል ውሃ አለ፡፡ ዝንተ ዓለም መጠኑ ይኸው ነው፡፡  የሚጨመር የሚቀነስ ነገር የለም፡፡ ዛሬ በብርጭቆ ሞልተን ብድግ አድርገን የምንጠጣው ውሃ፤ ‹‹የተሰጠውን ሥራ›› እየሰራ፤ ከጥንት እስከ ዛሬ የኖረ ነው፡፡ የነበረ እና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፤ ከ3.8 ቢሊየን ዓመታት ጀምሮ ውቂያኖሶች ከሞላ ጎደል ዛሬ ያላቸውን የውሃ መጠን አግኝተዋል፡፡ ባለሙያዎች፤ ነገረ-ውሃን ‹‹ሃይድሮስፌር›› (Hydrosphere) ይሉታል፡፡
የነገረ-ውሃ ጥናት ውቂያኖስ ነው፡፡ 97 በመቶ የሚሆነው የምድራችን ውሃ የሚገኘው በውቂያኖሶች ሲሆን፤ ከውቂያኖሶችም ግማሽ የሚሆነው ውሃ የሚገኘው (51.6 በመቶው) በሰላማዊ ውቂያኖስ (Pacific Ocean) ነው፡፡ የሰላማዊ ውቂያኖስ ስፋት ከዓለማችን የየብስ ስፋት ይበልጣል፡፡ አትላንቲክ ውቂያኖስ 23.6 በመቶ፣ ህንድ ውቂያኖስ 21.2 በመቶ፣ ሌሎች የዓለማችን ባህሮች በአንድነት 3.6 በመቶውን የምድር ውሃ ይዘዋል፡፡
ለመጠጥ ሊውል የሚችለው የዓለማች የውሃ መጠን፤ ከዓለማችን የውሃ ሐብት 3 በመቶው ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የሚበዛው የበረዶ ቂጣ ሆኖ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህ የበረዶ ቂጣ 90 በመቶው የሚገኘው በአንታርቲካ ነው፡፡ ቀሪው ደግሞ በግሪንላንድ፡፡ ከ3 በመቶው ውስጥ እጅግ በጣም ትንሽ መጠን የሚሸፍነው (0.036 በመቶ) በሐይቅ፣ በወንዞች፣ በግድቦች ሲገኝ፤ 0.001 ተን ሆኖ በደመና ውስጥ ይገኛል፡፡
ሩስተም ሮይ (Rustum Roy) በአሜሪካ፤ ‹‹ስቴት ዩኒቨርስቲ ኦቭ ፔንሲልቫኒያ›› ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ የዓለምአቀፍ የሳይንስ አካዳሚ አባል የሆኑት ሩስተም ሮይ፤ ‹‹እኛ ሁልጊዜም ጠበብ ያለ የጥናት መስክ መርጠን፤ ትኩረታችንን ወስነን፤ በጣም ጥንቃቄ አድርገን ነው ጥናት የምናካሂደው፡፡ እናም አሁን ውሃን በመውሰድ ለማጥናት ወስነን ምርምር ስናካሂድ፤ የውሃን ነገር ከብዙ አቅጣጫዎች እናየዋለን›› ይላሉ፡፡
ኪሪል (Kirill) የተባሉ በሩሲያ የስሞለንስኪ እና የካሊንግራድስኪ (Smolensky and Kaliningradsky) ሐገረ-ስብከት ሊቀ ጳጳስ ውሃ ስለ ውሃ ሲናገሩ፤ ‹‹በብዙ ሐይማኖታዊ መፃህፍት፤ ውሃ ከተራ ግዑዝ ነገር ላቅ ያለ ተደርጎ ይቀርባል፡፡ ውሃ ተራ ግዑዝ ነገር ሳይሆን ላቅ ያለ ፅንሰ-ሐሳብ ሆኖ ሲቀርብ እናስተውላለን፡፡ ይህም ፅንሰ-ሐሳብ ለየት ባለ መንገድ ከህይወት ጋር ትስስር ያለው ነገር ሆኖ ሲገለጥ እናስተውላለን›› ይላሉ፡፡
ከምድር የተፈጥሮ ክስተቶች ውስጥ እንደ ውሃ ለስላሳ እና ገራም ነገር የለም፡፡ ሆኖም፤ ይህ ገራም እና ለስላሳ ነገር፤ እንደ ዓለት ፅኑ እና ጠንካራ የሆነን ነገር ያፍረከርከዋል። አልሞ ይበላዋል፡፡ ውሃን ማንም ሊቆጣጠረው ይችል ይሆናል፡፡ ግን ውሃን የሚያሸንፍ ነገር በምድር ላይ አይገኝም፡፡ በጣም ገራም እና ለስላሳ የሆነው ውሃ፤ በጣም ፅኑ እና ጠንካራ የሆነውን ነገር ሁሉ ያሸንፋል፡፡ ገራሙ ጠንካራውን፤ ለስላሳው ፅኑዕ እና ድርድር የሆነውን ነገር ያንበረክከዋል፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ይህን እውነት ሁሉም ሰው ያውቀዋል፡፡ ግን ከዚህ እውነት የሚገኘውን ትምህርት መመሪያው አድርጎ ህይወቱን ለመምራት የሞከረ ሰው ብዙ አይገኝም፡፡ ይህን እውነት የሕይወት መመሪያ ሊያደርግ የሞከረ ላኦትዙ የተሰኘ የቻይና ሊቅ ነው፡፡ ‹‹በድካም ኃይል ይገኛል›› የሚል ሐሳብ ያለው ላኦትዙ፤ ከሁለት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በፊት ስለ ውሃ ፅፏል፡፡ ላኦትዙ ነገረ-ውሃ ገብቶታል፡፡
የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ዶ/ር ከርት ውትሪች (Kurt Wuthrich)፤ ‹‹ውሃ በእጀጉ ጥናት የተደረገበት ነገር ነው። ሆኖም ውሃ ሁሌም እንግዳ ነው፡፡ ከሌሎች ፈሳሽ ንጥረ ነገሮች ጋር ሲተያይ ከተለመደው ነገር ወጣ ያለ ፊዚካላዊ እና ኬሚካላዊ ጠባይ የሚያሳይ ንጥረ ነገር ነው›› ይላሉ፡፡
አሎይስ ግሩበር (Allois Gruber) የተባሉ የኦስትሪያ ተመራማሪ በበኩላቸው፤ ‹‹ውሃ ከነጥበ-በረድ (freezing point) ሳይደርስ በፊት፤ እፍጋቱ (Density) ለምን እንደሚጨምር፤ በተቃራኒው ከነጥበ-በረድ አለፍ ሲል ለምን እንደሚቀንስ እስከ ዛሬ ድረስ ለማወቅ የቻለ ሳይንቲስት አልተገኘም›› ይላሉ፡፡
ቅዝቃዜው ከነጥበ-በረድ በታች ሲሆን እፍጋቱ ለምን እንደሚጨምር፤ በተቃራኒው ከነጥበ-በረድ በላይ ሲሆን እፍጋቱ ለምን እንደሚቀንስ ምክንያቱን አውቆ ሊያብራራልን የሞከረ ጠቢብ አላገኘንም፡፡ ማንኛውም ንጥረ ቁስ (substance) ሲቀዘቅዝ ይኮማተራል ወይም contract ያደርጋል፡፡ ሆኖም ውሃ በጣም ሲቀዘቅዝ በጣም ይንሰራፋል ወይም expand ያደርጋል፡፡
ሰው እና ውሃ
ሰው ያለ ውሃ ሊኖር አይችልም የሚል ነገር መናገር ከንቱ ነው፡፡ የሰው ልጅ ውሃ ካጣ፤ ሰውነቱ በፍጥነት ይፈራርሳል፡፡ በቀናት ውስጥ ከንፈራችን በቢላ ቆርጠው እንዳነሱት እልም ብሎ ይጠፋል፡፡ ድዳችን እንደ ከሰል ይጠቁራል፡፡ አፍንጫችን አንደ ቅጠል ክሽልል ብሎ የተፎነነ ይመስላል፡፡ ቁመቱ በግማሽ ይቀንሳል፡፡ በዓይናች ዙሪያ ያለው ቆዳ ተሸብሽቦ ዓይናችንን ለማርገብገብ ያዳግተናል፡፡
ታዲያ በምድር ላይ ካለው ውሃ ለጤና ተስማሚ ሆኖ ጥማችንን ሊቆርጥልን የሚችለው እጅግ በጣም ጥቂቱ ነው፡፡ የሚበዛው ገዳይ ነው፡፡ ወይም ጨዋማ ነው፡፡ የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር ጨው ያስፈልገዋል፡፡ ግን፤ ሰውነታችን የሚፈልገው በመጠኑ በጣም ትንሽ ጨው ብቻ ነው፡፡ በባህር ውሃ ውስጥ የሚገኘው ጨው ግን በጣም ብዙ ነው፡፡
የባህር ውሃ ከሰውነታችን እንደሚወጣው ላብ እና እንባችን ያለ ይዘት ያለው ነው፡፡ በአንድ ሊትር የባህር ውሃ ውስጥ በሻይ ማንኪያ፤ ሁለት ከግማሽ የሚሆን ጨው ይገኛል፡፡ ከሚገባው በላይ ጨው ብንወስድ፤ ወዲያው የምግብ ልመት ስርዓታችን ይቃወሳል፡፡ የውሃ ሞለኪሎች፤ እንደ እሳት አደጋ ሰራተኛ በፍጥነት አደጋውን ለመከላከል ይራወጣሉ፡፡ በድንገት ወደ ሰውነታችን የገባውን ውሃ ‹‹ዳልዩት›› ለማድረግ እና ከሰውነታችን ለማስወጣት ይረባረባሉ፡፡ በዚህ የተነሳ፤ ሰውነታችን ተገቢውን ሥራ ለመስራት የሚያስፈልገው ውሃ በእጅግ ይቀንስበታል፡፡ ሰውነታችን በውሃ እጥረት ይቸገራል፡፡ ወይም Dehydrated ይሆናል፡፡ በጣም የከፋ ‹‹ዲሐይድሬሽን›› ሲከሰት፤ ራስን የመሳት ችግር ይፈጠራል፡፡ አዕምሮ ለጉዳት ይዳረጋል፡፡ በዚህ ጊዜ አደጋውን ለመከላከል የተራወጡት እና በከባድ ሥራ የዛሉት የደም ሴሎች፤ ጨውን ወደ ኩላሊት ያጓጉዛሉ። ኩላሊት ፋታ የማይሰጥ ሥራ ይሸከማል፡፡ የሚመጣው ጨው ከአቅሙ በላይ ሲሆን በሩን ይዘጋል፡፡ ኩላሊት ሥራ ሲያቆም ያ ሰው ይሞታል፡፡ ለዚህ ነው የባህር ውሃ የማንጠጣው፡፡  
እንደተጠቀሰው የውሃ ባህርይ ልዩ ነው፡፡ ምነው ቢሉ፤ በፊዚክስ ውስጥ ተቀባይነት ካላቸው አጠቃላይ ህግጋት ጋር የሚጣጣም ባህርይ አያሳይም፡፡ ግን ይህ የውሃ ልዩ ባህርይ፤ ህይወት በምድር ላይ እንዲኖር ለማድረግ ያስቻለ ነው ይላሉ፡፡ ከቁሳዊ ነገሮች ውስጥ በሦስት ኩነት (ጠጣር፣ ፈሳሽ እና ጋዝ) ሊገኝ የሚችል ውሃ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ሳይንስ፤ ይህ ለምን እና እንዴት እንደሆነ ገና አላወቀም፡፡ ከፈሳሽ ነገሮች ውስጥ ውሃ ለምን ከፍተኛ ‹‹ሰርፌስ ቴንሽ›› ያለው ፈሳሽ ሆነ ለሚለው ጥያቄም ምላሽ አላገኘም። ውሃ በምድራችን ላይ ከፍተኛ የአሟሚነት ባህርይ ሊይዝ የቻለው እንዴት ነው? ለሚለው ጥያቄም መልስ የለውም። ውሃ፤ በአስር ሺዎች የሚለካ ‹‹አትሞስፌሪክ ግፊት›› ያለበትን ሁኔታ ተቋቁሞ፤ በትላልቅ ዛፎች  ግንድ ውስጥ በሚገኙ ‹‹ቀጫጭን ቱቦዎች›› (thin tubes) ውስጥ ሽቅብ መውጣት የቻለው እንዴት ነው? ለሚለው ጥያቄም ሳይንስ ገና መልስ አላገኘም፡፡ ስለዚህ፤ በሩሲያ ‹‹የሞስኮ ስቴት ዩኒቨርስቲ›› የባዮሎጂ ፋካልቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ቭላድሚር ቮይኮቭ (Vladimir Voeikov) ስለ ውሃ ብዙ የምናውቀው ነገር የለንም ይላሉ፡፡
የውሃ ትንግርት
በደቡብ ምሥራቅ እስያ በ1956 ዓ.ም የተከሰተ አንድ አስደናቂ ነገር አለ፡፡ ቦታው፤ ዚግት (?) እየተባለ የሚጠራ ወታደራዊ ላቦራቶሪ ነው፡፡ በዚህ ላቦራቶሪ አውዳሚ የጦር መሣሪያ ለመፍጠር እና ለመፈብረክ ለዓመታት ጥናት እየተደረገ ቆይቷል፡፡ አውዳሚ የጦር መሣሪያ ለመፍጠር በውሃ ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡ እኒያ የሳይንስ ጠቢባን በአንድ ክፍል ውስጥ ለረጅም ሰዓታት በምስጢር ውይይት ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ፤ ውይይቱ ድንገት ተቋረጠ፡፡ በስብሰባው የነበሩት ሳይንቲስቶች በሙሉ በድንገት ታመሙና ወደ ሆስፒታል ተወሰዱ፡፡ በሁሉም ላይ የምግብ መበከል ከሚያስከትለው የጤና መታወክ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ችግር ይታይባቸው ነበር። ወዲያው የችግሩን መንስዔ ለመረዳት ጥረት አደረጉ፡፡ ሆኖም ሳይቲስቶቹ ከውሃ በስተቀር ሌላ የወሰዱት ምግብ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ውሃው ተመረመረ፡፡ በጠጡት ውሃ ውስጥ ምንም ዓይነት መርዛማ ነገር አልተገኘም። የጠጡት ውሃ ኬሚካላዊ ይዘት፤ ያው የታወቀውና የተለመደው H2O ነበር፡፡ ምርመራ ከተካሄደ በኋላ የተጠናቀረው ሪፖርት ያመለክተው፤ ሰዎቹ የቀመሱት መርዝ አለመኖሩን ነበር፡፡ ሰዎቹ የተመረዙት በጠጡት ውሃ ነበር፡፡
ይህ ችግር ከተከሰተ ከ20 ዓመታት በኋላ አንድ አስደናቂ መላምት ቀረበ፡፡ ይህ መላምት የውሃን ተገማች ያልሆነ ባህርይ ፍንትው አድርጎ የሚገልጥ ነበር፡፡ አጥኚዎቹ፤ ያቀረቡት መላምት፤ ‹‹ውሃ እንደ ሰው አዕምሮ ሁኔታን የመመዝገብ ባህርይ አለው›› የሚል ነበር፡፡ ስለዚህ ሰውን አጥፊ የሆነ ነገር ለመስራት ለሚያስቡት ሳይቲስቶች ውሃ መርዝ ሆነባቸው፡፡
በዓለም ዙሪያ በተደረጉ በርካታ ጥናቶች እንደተረጋገጠው፤ ውሃ በዙሪያው የሚከናወኑ ነገሮችን ሁሉ መዝግቦ ይይዛል፡፡ በውሃ ዙሪያ የሚከናወኑ ነገሮች ሁሉ፤ በውሃ ላይ ተፅዕኖ ያሳድሩበታል፡፡ እርሱም፤ በዙሪያው ባሉ ቦታዎች የሚከናወኑ ነገሮችን መዝግቦ ይይዛል፡፡ ውሃ ሁሉንም ነገሮች ያስታውሳል፡፡ ከውሃ ጋር የተገናኘ ማንኛውም ነገር (ለምሣሌ፤ መርከብ በላዩ ላይ ቢሄድ ወይም ዳክዬ ብትዋኝበት) ውሃው የእነዚህን ክስተቶች አሻራ መዝግቦ ያኖራል፡፡
በነገራችን ላይ፤ ተራ ውሃን በነሐስ ውሃ ማቅረቢያ ውስጥ በማኖር፤ ፈዋሽ ይዘት እንዲኖረው የማድረግ ጥበብ አለ፡፡ ታዲያ ከዚህ ጋር በተያያዘ ፕሮፌሰር ሩስተም ሮይ የሚሉት ነገር አለ፡፡ ‹‹የአሜሪካ ጦር ለቁስል ማከሚያ የሚጠቀምበት፤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በእጃቸው የሚገኝን ጀርም (Infectious bugs) ለማጥፋት በማሰብ የሚታጠቡበት ወይም እጅግ ምርጥ ‹አንቲባዮቲክ› ሆኖ የሚያገለግለው ውሃ መሆኑን ታውቃላችሁ›› ይላሉ፤ ፕሮፌሰር ሮይ፡፡ ‹‹ታዲያ ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?›› ሲሉ ይጠይቃሉ ፕሮፌሰሩ፤ ጠርሙሱን በእጃቸው ይዘው እያገላበጡ፡፡ ‹‹ታዲያ ይህን ነገር እንዴት ውሃ ልንለው እንችላለን›› በማለት ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡
ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፤ የውሃው ኬሚካላዊ ባህርይ አይቀየርም፡፡ ያው የተለመደው H2O ነው፡፡ ‹‹የውሃ ሞሎኪላዊ መዋቅር (Molecular Structure) በእጅጉ ይቀያየራል፡፡ በዚህ ጉዳይ እጅግ ወሳኙ ነገር፤ የውሃው ኬሚካላዊ ባህርይ ሳይሆን የውሃው ሞሎኪላዊ መዋቅር (Molecular Structure) ነው›› የሚሉት እኒሁ ፕሮፌሰር፤ የውሃ ሞሎኪላዊ መዋቅር (Molecular Structure) ስንል፤ ሞሎኪሎቹ እርስ በእርስ ሲያያዙ የሚፈጥሩት መዋቅራዊ ቅርፅ (ስርዓት) ነው፡፡ ይህ ሞሎኪላዊ መዋቅር ቅርፅ የሚፈጠረውም፤ የተወሰኑ የውሃ ሞሎኪዩል ቡድን ወይም ክለስተር በሚፈጥሩት ቅርፅ ነው፡፡ ቅርፁን በአጉሊ መነፅር ስንመለከተው፤ ልዩ ልዩ ውብ ወይም አስቀያሚ ምስል እንመለከታለን፡፡
ስለዚህ፤ ውሃ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ እየተከተለ፤ የውሃ ክለስተሮች የሚሰሩት ቅርፅ የተለያየ ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ፤ ውሃ ልክ እንደ ‹‹ማግኔቲክ ቴፕ›› በዙሪያው ያለውን ነገር ይመዘግባል። ለምሣሌ፤ መብራት ሲበራ ወይም ሲጠፋ የውሃው ሞሎኪላዊ መዋቅር (Molecular Structure) ይቀየራል፡፡ ከኬሚካላዊ ይዘት አንፃር፤ ውሃ - ውሃነቱ አይቀየርም፡፡ ሆኖም ሞሎኪላዊ መዋቅሩ (Molecular Structure)፤ ከውጭ (በአካባቢው) እንዳለው ነገር ሁኔታ ይቀያየራል፡፡ እንደ አንድ ሰው የነርቭ ስርዓት፤ ከውጭ ለሚያጋጥመው ነገር ምላሽ ይሰጣል ወይም react ያደርጋል፡፡
በእያንዳንዱ የውሃ ‹‹አስታዋሽ ሴል›› ውስጥ (memory cells) 440 ሺህ የመረጃ ቧንቧዎች አሉ፡፡ እያንዳንዱ ባንቧም የየራሱን የመረጃ ዓይነት የመመዝገብ ሚና ይጫወታል፡፡ እናም በዚህ ሞሎኪላዊ መዋቅር ያሉ ሞሎኪሎች ትስስር በየቅፅበቱ ይቀያየራል። ሆኖም መዋቅሩ የተለያዩ ሞሎኪሎችን እየተቀበለ እና እየሸኘ ለረጅም ጊዜ ይዘልቃል፡፡ የዚህ ዘላቂ  ሞሎኪላዊ መዋቅር መኖር፤ መረጃው ተመዝግቦ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡ ነገሩን ከፍተኛ የሜሞሪ አቅም ካለው ኮምፒውተር ጋር ያነፃፅሩታል፡፡ እናም ‹‹የውሃ ሞሎኪላዊ መዋቅር የውሃ ፊደል ወይም አልፋቤት ነው›› የሚሉት ፕሮፌሰር ሩስተም ሮይ፤ ‹‹እነዚህን ፊደሎች በመጠቀም ውሃ አረፍተ ነገር ይሰራል፡፡ ይህን አረፍተ ነገርም መቀያየር ይቻላል›› ይላሉ፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በዶኩመንታሪው የተጠቀሰ አንድ ነገር አለ፡፡ ጉዳዩ በጊዜው በ‹‹ኒዮርክ ታይምስ›› ጋዜጣ ተዘግቦ ነበር፡፡ ‹‹ላራ›› የተሰኘች አንዲት መርከብ በ1881 ዓ.ም (እኤአ) ከሊቨርፑል ወደ ሳንፍራንሲስኮ ጉዞ ጀመረች፡፡ ጉዞ በጀመረች በሦስተኛው ቀን፤ የእሳት ቃጠሎ ተፈጠረና ተጓዦቹ መርከቧን ለቅቀው በመውረድ የነፍስ አድን ጀልባ ላይ በመሳፈር ህይወታቸውን አተረፉ፡፡ የነፍስ አድን ጀልባ በመጠቀም ከተጓዙት ሰዎች መካከል፤ የመርከቧ ካፒቴን አንዱ ነበሩ፡፡ የተወሰኑ ሰዎችን የያዘችው እና የመርከቧ ካፒቴን የተሳፈሩባት ጀልባ የያዘችው ውሃ አለቀ፡፡ የሚጓዙበት የውቂያኖሱ ውሃ ሊጠጣ የሚችል አልነበረም፡፡
ሆኖም ከሦስት ሳምንታት የባህር ላይ ቆይታ በኋላ መሬት ረገጡ፡፡ እናም፤ ‹‹ካፒቴኑ ውሃ ጥሙን ተቋቁማችሁ እንዴት በህይወት ልትተርፉ ቻላችሁ?›› ተብለው ሲጠየቁ፤ ‹‹የአዕምሮ ኃይላችንን በማሰባሰብ፤ የውቂያኖሱን ውሃ እንደ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እናስበዋለን። ከጀልባችን ሥር ያለው ሰማያዊው የውቂያኖስ ውሃ፤አረንጓዴ ቀለም ወዳለው የመጠጥ ውሃ ይቀየርልን ነበር›› ብለዋል፡፡ በፍፁም እምነት የውሃን ዐረፍተ ነገር ቀየሩት ማለት ነው፡፡ የባህሩ ውሃ የሚጣፍጥ የመጠጥ ውሃ ይሆንላቸው ነበር፡፡
የሩሲያ የተፈጥሮ ሳይንስ አካዳሚ ፕሮፌሰር የሆኑት ኮንስታንቲን ካርትኮቭ (Konstantin Korotkov)፤ ‹‹አንድ በጣም የታወቀ ምሣሌ እናንሳ›› ይላሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፡፡ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ውሃውን ወደ ወይን የቀየረው ስኳር ወይም ላክቶስ ውሃው ውስጥ ጨምሮ አልነበረም፡፡ እኛ የተለያዩ ነገሮች በውሃ ናሙናችን ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ለመመርመር ሞክረናል›› ይላሉ፡፡ ማግኔቲክ ፊልድ፣ ኤሌክትሪካል ፊልድ፣ ሌሎች ቁሳቁሶች፣ የሰው በውሃ አጠገብ መገኘት፣ እንዲሁም የሰዎች በጎ እና መጥፎ ስሜቶች በውሃ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ለማጥናት ሞክረናል›› ካሉ በኋላ፤ ‹‹ከሁሉም ነገሮች በበለጠ በውሃ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድረው የሰዎች ስሜት መሆኑን ተረድተናል›› ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር ካርትኮቭ በላብራቶሪያቸው በርካታ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ሙከራዎች መካከል፤ ሰዎች የተለያየ ስሜት ይዘው ከውሃው አጠገብ እንዲቀመጡ ማድረግ ነው፡፡ ከተለያዩ ሰዎች ፊት ለፊት በብርጭቆ ውሃ አስቀምጠው፤ ውሃን ፍቅር፣ ርህራሄ እና መሳሳትን የመሳሰሉ አዎንታዊ ስሜቶች ይዘው ውሃውን እንዲመለከቱ አደረጉ፡፡ ከዚያም በሌሎች ብርጭቆዎች ውሃ ሞልተው፤ ጥላቻ እና ቁጣ የመሳሰሉ አሉታዊ ስሜቶች ይዘው እንዲቀመጡ አደረጉ፡፡ ከዚያም ናሙናዎቹን ሲመረምሩ፤ የታየው ሁኔታ ፍፁም የተለያየ ነበር፡፡ ፍቅር የውሃውን የኃይል መጠን (energy level) ከፍ እንዳደረገው እና የተረጋጋ ባህርይ እንደታየበት አረጋግጠዋል፡፡ በተቃራኒው፤ መጥፎው ስሜት የውሃውን የኃይል መጠን በእጅጉ እንደቀየረው አስታውቀዋል፡፡
የጃፓን ተመራማሪዎች ባደረጉት ምርምር፤ ውሃ ለጥሩ እና ለመጥፎ ስሜት እንዲጋለጥ ካደረጉ በኋላ በውሃው ላይ የተፈጠረውን ለውጥ ፎቶ ለማንሳት ሞክረዋል፡፡ ልዩነቱ አስገራሚ ነው፡፡ ‹‹ታስጠላኛለህ›› የተባለው የብርጭቆ ውሃ በጣም አስፈሪ ወይም አስቀያሚ የተዘበራረቀ መልክ አለው፡፡ ‹‹እወድሃለሁ›› የተባለው ውሃ ደግሞ በጣም የሚያምር እና የአልማዝ ጌጥ መስሎ ይታያል፡፡
በቦታ ጥበት ሳቢያ፤ ከዚህ በላይ ላጫውታችሁ አልቻልኩም፡፡ መነሻ ካደረግሁት ጉዳይ ጋር የተያያዘ አንድ ነገር አንስቼ ፅሁፌን ልቋጭ፡፡ ተመራማሪዎች፤ በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ፀሎት የተደረገበትን ውሃ፤ ከፀሎት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር በማነፃፀር ፍፁም የተለያየ ባህርይ እንዳላቸው አረጋግጠዋል፡፡ የቤትሆቭን እና የሮክ ሙዚቃ እንዲሰሙ በተደረጉ ውሃዎች መካከል ያለው ልዩነት እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ የሰው ልጅ 70 በመቶ ውሃ ነው፡፡ ይቆየን፡፡


Read 4999 times