Saturday, 25 April 2015 10:57

ሁለት ፅንፎች

Written by  መሐመድ ነስሩ
Rate this item
(22 votes)

 አያት፡፡ አየችው፡፡
ከአዲሱ ገበያ ወደ ቄራ በምትሄደው 6 ቁጥር አውቶብስ ውስጥ ናቸው፡፡ መጀመሪያ እሱ ነው ያያት፡፡ የቀይ ዳማ ናት፡፡ ውብ የሆኑ ትልልቅ ዓይኖች ታድላለች፡፡ ረዘም ያለ ፀጉር አላት፡፡ ጸጉርዋ የተፈጥሮ ይመስላል፡፡ ግን አርቴፊሻል ነው፡፡ ሂውማን ሄይር! … ቢሆንም አስውቧታል፡፡ ቅንድብዋና ሽፋሽፍትዋ “እኔ ነኝ ጥቁር … እኔ ነኝ ጥቁር” እያሉ ከፀጉርዋ ጋር ይፎካከራሉ፡፡ አንገትዋ ረዘም ያለ ነው፡፡ ብርሌ  አንገት! እሱ የሚወደው ዓይነት!... አንገቷ ላይ ያንጠለጠለችው የአንገት ሐብል የብር መስቀል ነው። በጡቶችዋ መሀል ይጫወታሉ፡፡
ከአንድ ቦታ ነው የተሳፈሩት፡፡ ካያት በኋላ ቲኬት ለሁለቱም ቆረጠ፡፡ ቲኬቱን እንቺ አላት፡፡
“ምንድን ነው?”
“ቲኬት!”
“የምን ቲኬት?” አለች ግራ ገብቷት፡፡
“የአውቶብስ መጓጓዣ ቲኬት ነው … ያዢው!”
ተቀበለችው፡፡ እና በሙሉ ዓይንዋ አየችው። ጠይም ነው፡፡ እሷ ደግሞ ጥሎባት ጠይም ወንድ ትወዳለች፡፡ እንደ ዘንግ ቀጥ ያለ አፍንጫ አለው። ፀጉሩን አሳድጎታል፡፡ አሳድጎ ፈርዞታል፡፡ ያምርበታል፡፡ ያምራልም፡፡ አጠገብ ለአጠገብ ነው የቆሙት፡፡
መካከለኛ ኑሮ የሚኖር ቤተሰብ ልጅ ነች፡፡ ስልክ ይዛለች፡፡ ሳምሰንግ፣ ጋላክሲ፡፡ ኤርፎን ጆሮዋ ላይ ሰክታ ሙዚቃ እየሰማች ነው፡፡ እሱም ስልኩን ላውድ ላይ አድርጎ ሙዚቃ እያዳመጠ ነው፡፡
“ይቅርታ ረበሽኩሽ?” አላት
“በምኑ?”
“በሙዚቃው”
“ኧረ ችግር የለውም”
“ምንድነው የምታዳምጪው?” አለ የኤርፎንዋን ገመድ በእጁ ነካ እያደረገ፡፡
“ሙዚቃ …”
“የምን ሙዚቃ … ማለቴ … አማርኛ ነው እንግሊዝኛ?”
“እንግሊዝኛ”
“የኔ እህት፤ እኔ እንኳን እንግሊዝኛ አማርኛ እራሱ እንደፓንት ነው ያጠረኝ”
“ምን አልከኝ?”
“አይ…ጥሩ ነው፡፡ ደስ ይላል!”
“ሙዚቃ አትወድም?”
“እወዳለሁ … በተለይ ደሀ የሚል ቃል ያለበት ዘፈን በጣም እወዳለሁ!”
“ለምን?”
“ደሀ ስለሆንኩ”
ፈገግ አለች፡፡
“አሁን ለምሳሌ ነዋይ ደበበ የኔ ደሀ ሲል እኔን የሚጠራኝ እየመሰለኝ ብዙ ጊዜ ‹አቤት!› እላለሁ”
“እኔ ግን የሰው ደሀ አለ ብዬ አላስብም!”
“እንዴት?”
“ሙሉ አካልና ሙሉ ጤና ያለው ሰው ቀርቶ የሌለው እንኳን አዕምሮ በመታደሉ ብቻ ሀብታም ነው ብዬ አምናለሁ!”
“እኔ ደግሞ ድህነቴን አምኜና ተቀብዬ የምኖር ሰው ነኝ! አይገርምሽም?”
“እስኪ ስለድህነት ንገረኝ” አለችው ፈገግ እንዳለች፡፡
“ከሚታየው ልጀምርልሽ?”
“እሺ”
“አሁን ለምሳሌ ይሄን ስልክ የገዛሁት ከሰፈር ልጆች ጋ ከመኪና ዕቃ ስናወርድ የማገኘውን ገንዘብ አጠራቅሜ ነው፡፡ ወላጆቼ ደሀ ናቸው፡፡ ያደግሁት በድህነት ውስጥ ነው፡፡ ወጪ ለመቀነስ በቀን ሁለቴ የሚበሉትን ሰዎች በዕውቀቱ ስዩም ቁምሳ ነው የሚበሉት ይላል፡፡ አምስት ሰዓት ላይ ቁርስ፤ አስራ አንድ ሰዓት ላይ ምሳ፡፡ እኛ ቤት ግን እንኳን ምሳ ወይም እራት ብቻ ሊዘለል ይቅርና ቀኑን ሙሉ እህል ሳንቀምስ ውለን የምናድርባቸው ብዙ ቀናት ነበሩ፡፡”
አዘነች፡፡ እውነቱን ሳይደብቅ ስለነገራት ደስ አላት፡፡ አደነቀችው፡፡ በራስ መተመኑና ምንም ሳይሸማቀቅ ይህን መናገሩ ብስለቱን ያሳያል አለች። ብዙ ወንዶች እንደዚህ አይደሉም፡፡ እንደውም ይዋሻሉ፡፡ ያላቸው መስለው ለመታየት ይጥራሉ፡፡ እሷ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ የምትጠላው፤ ውሸት ነው፡፡ በተለይ ወንድ ሲዋሻት ቅጥል ትላለች፡፡ ደግሞ ታሪክም አላት፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚሽከረከር ታሪክ፡፡
የቀድሞ ጓደኛዋ ብዙዓለም ይባላል፡፡
መንገድ ላይ ነው የተገናኙት፡፡ ከመሳለሚያ ወደ አውቶብስ ተራ እየተጓዘች ነበር፡፡ ዝናብ እያካፋ ነው፡፡ ጃንጥላ መያዝዋን ያስተዋለ ወጣት ተጠጋት፡፡
“ይቅርታ ጃንጥላው ለሁለት ይበቃናል?” አላት በጥላዋ እየተጠለለ፡፡
ዝም አለችው፡፡
ዝምታዋን እንደ እሺታ ወሰደው፡፡ ማውራት ጀመሩ፡፡
“መኪናዬን እኮ አሁን ጋራጅ አስገብቼ መምጣቴ ነው … ለዚህ ነው የተቸገርኩት፤ ተቸግሬ ያስቸገርኩሻ” አለ ብዙዓለም፡፡
“ኧረ ችግር የለውም” አለችው፡፡
“ቦሌ አካባቢ አንድ የቢዝነስ ቀጠሮ አለኝ… ለዚያ እየቸኮልኩ ነው … ታክሲ የሚባል ደግሞ የለም፡፡
“አውቶብስ ተራ ጋር ታገኝ ይሆናል”
“አዎ! እኔም እሱን ነው ተስፋ ያደረኩት”
ስታየው ጠይም ነው፡፡ ቆንጆ አይደለም፡፡ ግን እንደክዋክብት የሚያበሩ ዓይኖች አሉት፡፡ ጠይም ነው፡፡ ጠይምነቱ ልቧ ላይ ጠብ፣ ነፍሷ ላይ ጥብቅ ብሏል፡፡ ሲያወራም ደስ ይላል፡፡
አድራሻ ተለዋወጡ፡፡ እና ተለያዩ፡፡
በቀጠሮዋቸው ዕለት ሲገናኙ ለመዘነጥ ሞክሮ ነበር የመጣው፡፡
እንደተገናኙ “ህሊናዬ!” ብሎ ተጠመጠመባት፡፡
“እንዴት ነህ ብዙዓለም?”
ተቀመጡ፡፡
በጫወታ መሀል፤ “ስራህ ግን ምንድን ነው?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“ፋርማሲስት ነኝ … ቦሌ አካባቢ ትልቅ ፋርማሲ አለኝ .. ገብቶሻል አይደል አባባሌ … መድኀኒት መደብር አለኝ”
“ራስህን ችለኃላ?”
“እግዚአብሔር ይመስገን ለቤተሰቦቼ ተርፌያለሁ”
“ቤተሰቦችህ ችግረኞች ነበሩ?”
“ኧረ በጭራሽ … አባቴ የአየር መንገድ ሜካኒክ ነው፤ እናቴ ነርስ ናት .. አንቀባረው ነው ያሳደጉን!”
“ደስ ይላል” አለችው፡፡
ብዙዓለምና ህሊና ተላመዱ፡፡ ተዋደዱ፡፡ ፍቅር ተጀመረ፡፡ ለወራት ያህል አብረው እንደቆዩ ህሊና ሌላ ታሪክ ሰማች፡፡ እውነቱን ማወቁዋ ደስ አላት፡፡ የነገራት ሁሉ ውሸት መሆኑን መረዳትዋ አቃጠላት፡፡ ብዙዓለም ደሀ ነው፡፡
ብዙዓለም የደሀ ልጅ ነው፡፡
ደሀ በመሆኑ ሳይሆን ውሸታም በመሆኑ ጠላችው፡፡ አውቶብስ ተራ አካባቢ በሚገኝ አንድ ካፌ ውስጥ አስተናጋጅ ነው፡፡ ስራው ሳይሆን ማንነቱ (የውሸት ማንነቱ) እንድትጠላው አደረጋት። እንደሞኝ ስላታለላትና እንደተራ ዕቃ በገንዘብ ሊሸውዳትና ሊገዛት የሚሞክር መሆኑን ስታውቅ በዓይኔም አልየው አለች፡፡
ቤተሰቦቹ በጨረቃ ቤት የሚኖሩ ደሀ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ስታውቅ ይህን ሁሉ ውሸት ምን አመጣው በሚል ተንገሸገሸች፡፡ ቀጠረችው፡፡ የሆድ የሆድዋን አውርታ ልክ ልኩን ነግራው (እሷ እንደምትለው) ተለየችው፡፡
ይኸው እዚህ ደግሞ ድህነቱን በነፃ ሳይሸማቀቅ የሚያወራ፣ በራስ መተማመን ያለው ወንድ ገጠማት። ወንድ ሁሉ በውሸት ‘ራሱን የሚክብ፣ በሴት ለመወደድ አለሁ አለሁ የሚል ይመስላት ነበር፡፡ አሁን እዚህ ግን የድህነቱን ጥልቀት በተባ አንደበት የሚያብራራላት ወንድ ገጠማት፡፡ ታሪክዋና እውነቱ ተላተሙ፡፡ ከብዙዓለም በኋላ ወንድ አላምንም ብላ ነበር፤ ወንዶች ሴትን እንደዕቃ ነው የሚያዩዋት፤ በብር ኃይል ሊገዟት የሚችሉ፤ በገንዘብ ተጎትታ የምትመጣ ጠቦት ናት ብለው የሚያምኑ ይመስላት ነበር አልሆነም፡፡
እነሆ እዚህ አሁን የተለየ ወንድ ተገኘ፡፡
“አሁን ለምሳሌ እዚህ ስልክ ላይ ያስጫንኩትን ዘፈን ለምን እንደዚህ ከፍቼ የማዳምጥ ይመስልሻል?”
“ለምንድነው?”
“ሄድፎን መግዣ የሌለኝ ደሀ ስለሆንኩ ነው፤ እንጂ እንዳንቺ ሰው ሳልረብሽ ለ‘ራሴ ብቻ ማድመጥ የማልፈልግ ይመስልሻል?”
“ለየት ያልክ ሰው ነህ!” አለችው
“እንዴት?”
“እኔ‘ጃ … እንዲሁ”
ድንገት ተጠራች፡፡ እዛ ማዶ ከተቀመጡ እናት አጠገብ አንድ ሰው ሊወርድ ሲነሳ “ህሉ ነይ እዚህ” ብለው ተጣሩ፤ እናትየው፡፡ “እናቴ ናት” ብላው ወደዚያው አመራች፡፡ የሚሄዱበት ደርሰው ሲወርዱ፣ ያለመውረጃ ቦታው ተከትሏቸው ወረደ፡፡
ከኋላ ኋላ እየሄደ ስልኩን ወረቀት ላይ ፅፎ አንድ ህፃን አስይዞ ወደ እሷ ላከው፤ ዞር ብላ አየችው፡፡ ተጠቃቀሱ፡፡
የዚያኑ ቀን ደወለችለት፡፡
ስልኩን አንስቶ “ማን ልበል?” አለ፡፡
“ቅድም የተዋወቅኩህ ልጅ ነኝ፤ አውቶብስ ውስጥ …”
“እእ… እንዴት ነሽ?”
“ደህና ነኝ…. ስም እንኳን ሳንለዋወጥ አይደል?” አለችው እንደማፈር እያለች፡፡
“ዮናታን እባላለሁ!” አላት፡፡
“ህሊና እባላለሁ!” አለችው፡፡
“ስለደወልሽልኝ በጣም ደስ ብሎኛል … ይኼ ስልክ ያንቺ ነው?”
“አዎ ሱቭ አድርገው!”
መገናኘት ጀመሩ፡፡ ተግባቡ፡፡ ተዋደዱ፡፡ ተጣመሩ፡፡
ውሸት እንደምትጠላው አውቆ ነው መሰል፤ አድብቶ ይከታተላታል፡፡ የዮናታንም ታሪው ውሸት ሆነ፡፡ ግራ ገባት፡፡ አዘነች፡፡ ዮናታን እንዳላት ደሀ አይደለም፡፡ ቱጃር፤ የቱጃር ልጅ ነው፡፡ ራሱን ደሀ አድርጎ የተዋወቃት አውቆ ነው፡፡
ሴቶች ይመጣሉ፡፡ ግን አያምናቸውም፡፡ እሱን ፈልገው ሳይሆን ገንዘቡን ፈልገው የሚጠጉት ይመስለዋል፡፡ ደግሞ እውነቱን ነው፤ ብዙዎች በእሱ ማንነት ተማርከው ሳይሆን በሀብቱ ተደልለው ነው የሚያናግሩት፣ የሚቀጥሩት፣ እወድሃለሁ የሚሉት፡፡
“እኔ ተሳቢዬንና ተለጣፊዬን (ገንዘብ፣ ሀብት) አይታና ፈልጋ ሳይሆን ማንነቴን ወዳና ፈቅዳ የምትመጣ ሴት ነው የምፈልገው” ይላል፡፡
አልሙኒየም የመግጠም ስራ ላይ የተሰማራ “ዮናታን አልሙኒየም” የተሰኘ ድርጅት አለው። የቤት መኪና አለው፡፡ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ነው ከሚባል ነገር ውስጥ አንድም የጎደለበት ነገር የለም። እሱ የጎደለ የሚለው “ሀብቴን ሳይሆን እኔን ፈልጋ የምትመጣ ሴት ማግኘት” ነበር፡፡
እንደ ዕድል ሆኖ ህሊናን አገኘ፡፡ ደሀ ሆኖ ተዋወቃት። ድህነቱን ተቀብላ፤ በማንነቱ ብቻ ወደደችው፡፡ “ያሰብኩት ተሳካ፣ ያለምኩት ደረሰ” አለ ዮናታን፡፡ አብዝቶም ወደዳት፡፡
ዮናታን ሀብታም ነው፡፡ የሚኖረው ግን እንደ ደሀ ነው፡፡ ድህነት ውስጥ የሆነ የሚስበው ነገር አለ። ምን እንደሆነ ‘ራሱ ለይቶ አያውቀውም፡፡ ግን ደሀ ይወዳል። በድህነት ይማረካል፡፡ መኪናውን ለጓደኞቹ እየሰጠ በታክሲ ይጠቀማል፡፡ አንዳንዴም የከተማ አውቶብስ ይሳፈራል፡፡ የከተማ አውቶብስ መሳፈር የሚወደው ልጅነቱን ስለሚያስታውሰው ነው፡፡
በልጅነቱ አንዳንዴ አባቱ ተቻኩለው ት/ቤት ሳያደርሱት በሚሄዱ ቀን፤ ለታክሲ ተብሎ የሚሰጠውን ብር ከጓደኞቹ ጋር በአውቶብስ እየተሳፈረ … የቀረውን ሳንቲም ብስኩት፣ ሳምቡሳ ይበላበት፤ ጀላቲ ይልስበት ነበር፡፡ ከጓደኞቹ ጋር እየተጫወቱ ይጓዙበት ስለነበር - የከተማ አውቶብስ ይወዳል፡፡ ልጅነቱን ስለሚጠራለት።
ህሊናን የተዋወቃት ዕለትም አውቶብስዋ መቆምዋን ሲያይ በቅርብ ርቀት ስለነበር ጥልቅ ብሎ ገባ፡፡ እና ተዋወቁ፡፡
ህሊና ውሸት አትወድም፡፡ ስለማትወድ እንደዋሻት ስታውቅ ተናደደች፡፡ እውነተኛ ማንነቱን ለምን አልነገረኝም ስትል በሸቀች፡፡
“እሱንም ልለየው ወይስ አልለየው?”
ግራ ገባት፡፡
ቀጥራው ስታበቃ የምትነግረውን እያብሰለሰለች የቀጠሮ ሰዓቱን መጠበቅ ጀመረች፡፡

Read 4193 times