Saturday, 25 April 2015 11:00

3ኛው አገር አቀፍ የቴአትር ፌስቲቫል ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ቴአትሮች ተወዳድረው ይሸለማሉ
በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ከ10 ዓመት በላይ የሰራው ተስፋ ኢንተርቴይንመንት፣ ከህይወት ፕሮሞሽንና ኮሚዩኒኬሽን ጋር በመተባበር 3ኛውን አገር አቀፍ የቴአትር ፌስቲቫል በአዳማ ከተማ ኦሊያድ ሲኒማ ያካሂዳል፡፡ በፌስቲቫሉ ለእይታ ቀርበው በዳኞች የሚወዳደሩ ስምንት ቴአትሮች የተመረጡ ሲሆን ከብሔራዊ ቴአትር “ባቢሎን በሳሎን” እና “ቅጥልጥል “ኮከቦች”፣ ከሀገር ፍቅር “የበዓል እንግዶች”፣ “ትዳር ሲታጠን” እና “የጉድ ቀን” እንዲሁም ከግል የቴአትር ኢንተርፕራይዞች “የፍቅር ካቴና”፣ “ብር አምባር” እና “ወንድ አይገባም” የተሰኙት ቴአትሮች መመረጣቸውን የተስፋ ኢንተርቴይንመንት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ወርቁ ገልፀዋል፡፡ ፌስቲቫሉ ከሚያዚያ 24 እስከ ግንቦት 1 ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ሲሆን በሊቢያ በኢትዮጵያዊያን ወገኖች ላይ በተፈፀመው ግድያ ሃዘን ምክንያት ፌስቲቫሉ ለአንድ ሳምንት መራዘሙንና ከግንቦት 1-9 እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ብዙ ተዋንያን ያላቸው እንደነ “የቴዎድሮስ ራዕይ”፣ “ቶፓዝ” እና “ግይድ” የመሳሰሉ ቴአትሮች በበጀት እጥረት ሳቢያ አዳማ ሄደው መታየት ባይችሉም እዚሁ አዲስ አበባ በዳኞች ታይተው እንደሚወዳደሩ ተገልጿል፡፡
አንደኛውና ሁለተኛው አገር አቀፍ የቴአትር ፌስቲቫል በአዲስ አበባ መካሄዱን ያስታወሱት አቶ ተፈራ፤ የአሁኑ አዳማ የሚካሄደው ፕሮግራሙን ለየት ለማድረግና ለአዳማ ህዝብ ቴአትሮቹን ለማሳየት ታስቦ ነው ብለዋል፡፡ ወደፊት በሌሎች ክልሎችም ፌስቲቫሉ እንደሚካሄድ አክለው ገልጸል፡፡ ቴአትሮቹ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተውጣጡ የቴአትር ምሁራን የሚዳኙ ሲሆን አሸናፊ ቴአትሮች፣ ተዋንያን፣ ደራሲና አዘጋጆች በየዘርፉ ይሸለማሉ ተብሏል፡፡

Read 1360 times