Saturday, 25 April 2015 11:08

የአይሲስ የግድያ ቪዲዮዎች የቡድኑ “የስነ-ልቦና ጦርነት” አካል ናቸው ተባለ

Written by 
Rate this item
(50 votes)

 የግድያ ቪድዮዎቹ አለማቀፍ ስነ-ልቦናዊ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ነው
      አይሲስ የተባለው አሸባሪ ቡድን እያሰራጫቸው የሚገኙና በተለያዩ አገራት ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን አሰቃቂ ግድያዎች የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች፣ ቡድኑ በአለማቀፍ ደረጃ የከፈተው የስነልቦና ጦርነት አካል ናቸው መባሉን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የጀርመን የአገር ውስጥ የስለላ ተቋም ሃላፊ ሃንስ ጆርጅ ማሰን እንዳሉት፣ አገራት እነዚህ አሰቃቂ የግድያ ቪዲዮዎች በወጣት ዜጎቻቸው ላይ የሚያሳድሩትን የስነልቦና ተጽዕኖ ለመቅረፍ የራሳቸውን እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል፡፡
የቪዲዮ ምስሎቹ የአሸባሪውን ቡድን የጥፋት ፕሮፓጋንዳ በወጣቱ ትውልድ ልቦና ውስጥ የሚያሰርጹ ናቸው ያሉት ጆርጅ ማሰን፤ ምስሎቹ ለእይታ ሲበቁ የቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ አሰቃቂነት የሚያሳዩ መልዕክቶችን አብሮ ማቅረብ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ በቅርቡ በጀርመን ለሚገኙ ደጋፊዎቹ ባሰራጨው የቪዲዮ መልዕክት፣ ባለፈው ጥር ወር በፈረንሳይ የተፈጸመውን ዓይነት ጥቃት እንዲፈጽሙ ጥሪ አቅርቧል ያለው ዘገባው፣ የጀርመን የደህንነት ባለስልጣናትም መልዕክቱን ያስተላለፈው ትውልደ ጀርመናዊው አለማቀፍ አሸባሪ ዴኒስ ኩስፐርት መሆኑን ማረጋገጣቸውን አስታውሷል፡፡
ሲኤንኤን በበኩሉ፤አይሲስ እያሰራጫቸው ያሉት የግድያ ቪዲዮዎች በአለማቀፍ ደረጃ ፍርሃትን እያነገሰ እንደሚገኝና የቡድኑ ቪዲዮዎች ሌሎችም ለመሰል ጥፋቶች እንዲነሳሱ ተጽዕኖ እንደሚያደርግ ዘግቧል፡፡
በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና መምህር ፕሮፌሰር አሪ ክሩግላንስኪ እንዳሉት፤ የአይሲስ የአሰቃቂ ግድያ ቪዲዮዎች፣ ግለሰቦች በግጭት ወቅት  ተመሳሳይ ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ የሚያነሳሳ ስነልቦናዊ ጫና የመፍጠር ሃይል አላቸው፡፡
የጀሃዲስቶች አሰቃቂ ግድያዎች በቪዲዮ ምስሎች በስፋት መሰራጨታቸው፣ ግለሰቦች ከዚህ ቀደም የማያስቡትን አንገት ቀልቶ መግደል የሚል የጭካኔ ሃሳብ ትኩረት ሰጥተው ማሰብ እንዲጀምሩ በማድረግ ረገድ በአለማቀፍ ደረጃ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው ብለዋል ፕሮፌሰሩ፡፡

Read 6757 times