Saturday, 25 April 2015 11:13

ገንዘቤ በላውረስ ሽልማት የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊ ሆነች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

     በስፖርቱ ዓለም የላቀ ብቃት ላሳዩ እና በስኬታቸው ከፍተኛ አድናቆት ላገኙ አትሌቶች በሚሸለሙበት ዓመታዊው የላውረስ የምርጥ ስፖርተኛ ሽልማት አትሌት ገንዘቤ ዲባባ የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊ ተሸላሚ አትሌት ሆነች፡፡ በአትሌቲክስ የላውሬስ የዓመቱ ምርጥ ሴት ስፖርተኛ ሆና የተመረጠችው ገንዘቤ ባለፈው ዓመት በሁለት ሳምንታት ውስጥ ሶስት ክብረ ወሰን መስበርዋ፤ በ5000 እና በ2000 ሜትር የዓመቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገቧ እና በ3ሺ ሜትር የኢንተርኮንትኔንታል ሻምፒዮና በመሆኗ ነበር፡፡
በ2015 በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ከመጨረሻዎቹ ሶስት እጩዎች አንዷ ለመሆን የበቃችው የመካከለኛ ርቀት ምርጥ ሯጭ ገንዘቤ ዲባባ፤ ለመጀመርያ ጊዜ የላውረስ ሽልማትን የተጎናፀፈች ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆናለች፡፡ በተያያዘ ሰርቢያዊው ሜዳ የቴኒስ ተጫዋች ኖቫክ ጆኮቪች የላውሬስ የዓመቱ ምርጥ ወንድ ስፖርተኛ ሆኗል። ለ27 ዓመቱ ኖቫክ ድጅኮቪች የላውረስ ሽልማት ለሁለተኛ ጊዜ ያገኘው ሲሆን የመጀመርያውን የተሸለመው በ2011 እኤአ ላይ ነበር፡፡ ታዋቂው የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ኖቫክ በ2015 እኤአ ላይ በተለያዩ ውድድሮች ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሽልማት ገቢ ሲያስገባ፤ በ2014 እኤአ ላይ ደግሞ 11.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስመዝገብ ከሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች የመጀመርያ ነበር፡፡  ኖቫክ በፎርብስ መፅሄት የሃብት መጠኑ እስከ 90 ሚሊዮን ዶላር ተተምኖለታል፡፡
ለዓመታዊው የላውረስ ሽልማት በሻንጋይ ከተማ በሚገኘው ግራንድ ቲያር አዳራሽ በተዘጋጀው ስነስርዓት ላይ ትልልቅ የሆሊውድ ዝነኛ ተዋናዮች ተገኝተው ነበር፡፡ ከመካከላቸው በሙላቱ አስታጥቄ የማጀቢያ ሙዚቃ በተሰራለት ብሮከን ፍላወርስ ፊልም ላይ የተወነው እውቅ ተዋናይ ቢል ሙራይ እንዲሁም ሱፕር ማን የተባለውን ገፀባህርይ የሚተውነው ሄነሪ ካቪል ይጠቀሳሉ፡፡ የሽልማት ስነስርዓቱ በ100 አገራት የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት ሲኖረው ከመሰል የሽልማት ስነስርዓቶች በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ተከታታይ በማግኘት እስከ 2 ቢሊዮን ተመልካች እንደታደመው ተወስቷል፡፡ በላውረስ ሽልማት ከሚጠቀሱ ሌሎቹ አሸናፊዎች መካከል የዓመቱ ምርጥ ቡድን ሽልማትን ያገኘው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ይጠቀሳል፡፡
የላውሬስ ሽልማት በየዓመቱ በስፖርቱ ጎልቶ ለወጡ ስፖርተኞች የሚሰጥ የክብር ሽልማት ሲሆን ከተለያዩ የዓለም ስፖርቶች የተውጣጡና የላውረስ አካዳሚ አባላት የሆኑ 50 ዝነኛ የዓለማችን ስፖርተኞች ምርጫውን ያከናውናሉ፡፡ በላውረስ አካዳሚ ካሉ ትልልቅ ስፖርተኞች ጀርመናዊው የእግር ኳስ ቄሳር ፍራንዝ ቤከንባወር፤ ታዋቂው የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ቦሪስ ቤከር፤፤ ዝነኛው ራሽያዊ የምርኩዝ ዘላይ ሰርጄይ ቡብካና እንግሊዛዊው የእግር ኳስ ባለታሪክ ቦቢ ቻርልተን ይገኙበታል፡፡
የ24 ዓመቷ ገንዘቤ በመካከለኛ ርቀት 1500፤ 3000 እና 5000 ሜትር ውድድሮች በትራክ እና በቤት ውስጥ ውድድሮች 8 የሩጫ ዓመታት አሳልፋለች፡፡ ያስመዘገበቻቸው ሪከርዶች እና የሜዳልያ ውጤቶች ከዚህ በታች ቀርበዋል፡፡
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2 የወርቅ ሜዳልያዎች በ1500 እና በ3000 ሜትር
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና 2 የወርቅ ሜዳልያዎች በወጣቶች ውድድር
በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና 1 ወርቅና 1 ብር ሜዳልያ በ5ሺ ሜትር
በአይኤኤፍ ኮንትኔንታል ካፕ 1 ወርቅ ሜዳልያ
3 የዓለም ሪከርዶች በቤት ውስጥ አትሌቲክስ
1500 ሜትር 3፡55.17 በካርልሱርህ ጀርመን በ2014 እኤአ
3000 ሜትር 8፡16.6 በስዊድን ስቶክሆልም 2014 እኤአ
5000 ሜትር 14፡18.86 በስዊድን ስቶክሆልም 2015 እኤአ
6 የአፍሪካ አትሌቲክስ ሪከርዶች
በ1500ና በ5000 ሜትር ትራክ፤ በ2 ማይል፤ እንዲሁም በቤት ውስጥ አትሌቲክስ በ1500፤ በ3000 እና በ5000 ሜትር ውድድሮች

Read 3243 times