Saturday, 25 April 2015 11:15

ህፃናቱን የማዳን ስራ ቀለል ተደርጎ ሊታይ አይገባውም

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

 ተከታዩ ገጠመኝ በቤተዛታ ሆስፒታል (አዲስ አበባ ለገሀር) ያገኘናት እናት ገጠመኝ ነው፡፡
“...የእርግዝና ክትትል ለማድረግ ወደ ሆስፒታል ስሄድ በመጀመሪያ የተነገረኝ የኤችአይቪ ቫይረስ በደሜ ውስጥ መኖር ያለመኖሩን ማረጋጋጥ እንደሚገባኝ ነበር። ሐኪሞቹ ሲነግሩኝ እንደከባድ ነገር አልቆጠርኩትም፡፡ ምንም ችግር የለም ...እሺ... በማለት ምርመራውን አደረግሁ። ...ያገኘሁት ውጤት ግን ስሜቴን እንደ መጀመሪያው ይዤ እንድቀጥል አላስቻለኝም። ደነገጥኩ... ፈራሁ... ተርበተበትኩ...፡፡ የምክር አገልግሎት የምትሰጠኝ ነርስ በጣም ተቸገረች፡፡ የእኔን ስሜት ለመጠበቅ ብዙ ታገለች። እኔም በተቻለ መጠን ስሜቴን አሰባስቤ ወደቤት ተመለስኩ፡፡ ስሜቴን ሊጋራ የሚችል ማንም ሰው አልነበረኝም፡፡ ለማንም መንገር አልፈለግሁም፡፡ እናቴ፣ እህቴ፣ ወንድሞቼ ሁሉ ዙሪያዬን ቢኖሩም ...በቃ ...ለአንድ ሳምንት ብቻዬን በሬን ዘግቼ ተኛሁ፡፡ የሁዋላ ሁዋላ ግን አስቤ... አሰቤ.. እራሴን አበረታትቼ... ወደ ህክምናው ተመለስኩ፡፡
ከዚያ በሁዋላስ? የእኛ ጥያቄ ነበር፡፡
“...ከዚያ በሁዋላ ጉዳዬን ለእራሴ ይዤ... ከነርስዋ እና ከሐኪሜ ጋር ብቻ እየተወያየሁ ልጄን በሰላም ወለድኩ፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ የወለድኩለት ሰው አብሮኝ የለም። ባሌም አይደለም፡፡ ለተወሰነ ጊዜ በነበረን የጉዋደኝነት ቆይታ ነበር ያረገዝኩት፡፡ ...ለነገሩ ገና ተመርምሮ ካልሆነ በስተቀር ልጁ የእርሱ ነው ለማለት አልችልም፡፡ ሌላም ጉዋደኛ ነበረኝ፡፡ ለማንኛውም... ችግሩ ሌላ ነው፡፡
ምንድነው ችግሩ?
“...ችግሩማ... ከወለድኩ በሁዋላ በዚያችው በአንድ ከፍል መኝታቤት ውስጥ እህቴ እናቴ ወንድሞቼ ሁሉ ከበውኛል፡፡ እንዴት አድርጌ ለልጄ የምሰጠውን መድሀኒት ልስጥ? የሚያዩትን ነገር ሁሉ ማወቅ ይፈልጋሉ። ለእራሴም በትክክል መድሀኒቴን መውሰድ ...ልጄንም መንከባከብ... አልቻልኩም፡፡ በተለይም እህቴ ለሁሉ ነገር በጣም ቅርቤ ስለሆነች እጅግ በጣም ነበር የተቸገርኩት። እንዳልነግራቸው ...ሁሉም ጥለውኝ ይሄዳሉ ብዬ ፈራሁኝ፡፡  ዝም እንዳልል ሐኪም በነገረኝ መመሪያ መሰረት ልጄንም እራሴንም መጠበቅ አቃተኝ። ስለዚህ ያለኝ አማራጭ የአራስነት ጊዜዬን ሳልጨርስ መነሳት እና እራሴን መርዳት ነበር...”
ከላይ ካነበባችሁት ገጠመኝ ልንማር የምንችለው ነገር ግልጽነት የሚባለው ነገር እና አድሎና መገለል ዛሬም በትክክል አልተለመዱም የሚለውን ነው፡፡ ገጠመኝዋን የገለጸችው እናት ቤተሰቦቼ ምናልባት መገለል ያደርሱብኛል ከሚል እስዋ በበኩልዋ ድብቅ በመሆንዋ ብዙ እንደተቸገረች ነው፡፡ ነገር ግን አድሎና መገለልን አስወግደን ግልፅነት በተመላበት ሁኔታ መኖር ብንችል ቀጣዩ ትውልድ ከኤችአይቪ ቫይረስ ነጻ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡
ከኤችአይቪ ነፃ የሆነ ትውልድን በሚመለከት WHO በ2015 ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2010 በኬንያ 20/ የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ የተሰበሰቡ ሲሆን ስብሰባው የተቀናበረው በUNFPA’UNAIDS’ UNICEF እና WHO ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በስብሰባው የተሳተፉት 20 የአፍሪካ ሀገራት በአለም ከሚቆጠረው ኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ መተላለፍ 85% የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ በኬንያ በተደረገው ስብሰባ ህፃናቱን የማዳን ስራ እንደሌላ ስራ ቀለል ተደርጎ ሊታይ የማይገባውና በየአመቱ በመላው አፍሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ህፃናትን ህይወት ለማዳን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተሰምሮበታል፡፡
ዩኒሴፍ በ2012 ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ከሚገኝ እናቶች መካከል 24% የሚሆኑት ብቻ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ የሚሰጠውን ህክምና እንደሚያገኙ ጠቁሟል፡፡ በእርግዝና ወቅት ለእናቲቱ የሚሰጠው የኤች አይቪ የምክር አገልግሎት ህክምናውን በማስፋት እንዲሁም ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ እንዲወለድ በማድረግ እረገድ የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው።
ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የማድረግ እርምጃ ባደጉት ሀገራት ትልቅ ለውጥ እንዳመጣና ከሰሀራ በታች ባሉት የአፍሪከ ሀገራት ግን በየአመቱ (300000) ሶስት መቶ ሺህ ያህል አዲስ ህፃናት በቫይረሱ እንደሚያዙ የአለም የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡
የWHO መረጃ የሚከተለውን እውነታ ያሳያል፡፡
በ2008 የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው በአለም 45% የሚሆኑ እርጉዝ ሴቶች ብቻ ፀረ ኤችአይቪ ህክምና መውሰዳቸው ተረጋግጧል፡፡
በኢትዮጵያ ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ እና ልጆቻቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል ART የሚወስዱ እናቶች (18269) አስራ ስምንት ሺህ ሁለት መቶ ስድሳ ዘጠኝ ይሆናሉ፡፡
ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ ተብለው የሚገመቱ እና ART መጠቀም ያለባቸው እናቶች (ልጆቻቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል) VNAID  እና WHO ባወጡት አሰራር መሰረት ወደ (33000) ሰላሳ ሶስት ሺህ ይሆናሉ፡፡
ስለዚህ ART ተጠቃሚ እርጉዝ እናቶች 55% እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡
                         (World health organization, 2014)
ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፍ የሚችለው በእርግዝና፣ በምጥ፣ በወሊድ እና ጡት በማጥባት ሲሆን ስያሜውም MTCT  ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ይሰኛል፡፡ ይህንን ለመከላከል በሕክምናው ዘርፍ የሚሰራው ስራም PMTCT ወይም ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ መከላከል በሚል ስራ ላይ ውሏል፡፡ የ PMTCT አገልግሎት በማይሰጥበት ሁኔታ ኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ የሚኖረው መተላለፍ እንደየ ሀገራቱ ሁኔታ ከ15-45% ሊደርስ የሚችል ሲሆን የመከላከሉ ስራ ውጤታማ ከሆነ ግን ስርጭቱ እስከ 5% ይወርዳል ተብሎ ይታሰባል፡፡
አለማቀፉ የጤና ትምህርት እና ስልጠና ማእከል (I-TECH­) ከUS president’s emergency plan for HIV AIDS Relief ጋር በመተባበር የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ለሚገኝ ነብሰጡር እናቶች ድጋፍ ይሰጣል። ይህ ፕግራም ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት ማለትም በ2014 ያበቃ ሲሆን በአክሱም፣ ጎንደር እንዲሁም ዱፍቲ የሚገኙ እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ተጠቃሚ ከሆኑ እናቶች መካከል አንዱዋ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥታለች፡፡
“...አለምነሽ ቫይረሱ በደሟ እንዳለ ያወቀችው በፈረንጆቹ 2009 ወደ አረብ ሀገር ለመሄድ ባደረገችው ምርመራ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ውጪ የመሄድ ህልሟ እውን ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በ2013 የመጀመሪያ ልጇን ስታረግዝ ትልቁ ጭንቀቷ የነበረው የሚወለደው ህፃን እንዴት ከቫይረሱ ነፃ ሆኖ ይወለዳል? የሚል ነበር። ...ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሆኖ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ መውለድ እንደሚቻል ሳውቅ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ ምናልባት የዚህ ፕሮግራም አካል ባልሆን ኖሮ ልጄ ነፃ ሆና ላትወለድ ትችል     ነበር፡፡ ዛሬ ሂያብ የሰባት አመት ታዳጊ ሆናለች፡፡”
በኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል ያነጋገርናት ሲ/ር አልጣሽ ደሳለኝ እንደምትመሰክረው እናቶች ለምርመራ ሲመጡ የሚያሳዩት ፊትና ከውጤት በሁዋላ የሚኖራቸው ምላሽ እጅግ ይለያያል፡፡ ይህንን በምሳሌ ስታስረዳም...
“...አንዲት እናት ለእርግዝና ክትትል ስትመጣ በመጀመሪያው የምክር አገልግሎት ጊዜ ...የኤች አይቪ ቫይረስ በደምዋ ውስጥ ቢገኝ ምንም ማለት እንዳልሆነ ...ከባለቤቷ ጋር በሰላም ተፈቃቅራ እንደምትኖር... ልጅዋንም በሰላም ተረጋግታ እንደምታሳድግ ነበር የነገረችኝ፡፡ ነገር ግን ልክ የደም ውጤትዋ ሊነገራት ሲል ሰውነትዋ ሲደፈርስ ይታይ     ነበር፡፡ በጣም ለማግባባት ሞክሬ ሁኔታውን ስነግራት ማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ነበር የተለወጠችው፡፡ እዚያው እኔው ፊት ...ባለቤተዋን መውቀስ... ማልቀስ... ጀመረች፡፡ ለማባበል ብዙ ብሞክርም አልሰማችኝም፡፡ ከዚያ በሁዋላ አልተመለሰችም፡፡ በስልክ... እንዲሁም በተለያየ መንገድ ብከታተልም የት እንደገባች ማወቅ አልቻልኩም፡፡ ለካስ     ይህች ሴት ስልኩዋን ከስራ ውጭ አድርጋ በቀጥታ ወደቤተሰቦቿ ጋ ወደገጠር ነበር ያመራችው፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ እራስዋ በአካል ወደ ሆስፒታላችን መጥታ የነገረችኝ ...ሁኔታውን ያወቁት በዚያ የሚኖሩ ወንድሞቿ አግባብተው በቅርብ ወደሚገኘው ጤና ጣብያ እና ሆስፒታል እያመላለሱ... እያግባቡና እያባበሉዋት ልጅዋን በሰላም እንድትወልድ ማድረጋቸውን ነው፡፡ በሁዋላም ልጁ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ እስኪረጋገጥ     እዛው ቆይታ ልጁን ለቤተሰቦቿ ትታ መምጣትዋን ነገረችኝ፡፡ ስለባለቤትዋ ያለውን     ሁኔታም ስጠይቃት... እሱንማ ያኔውኑ ነው የፈታሁት... ምክንያቱም ዋሽቶኛል... ለካስ እሱ አስቀድሞውኑም ቫይረሱ በደሙ ውስጥ እንደሚኖር ያውቅ የነበረና በድብቅም መድሀኒት የሚወስድ ሰው ነበር፡፡ በቃ... አይኑን ማየት አልፈልግም ብላ ለእራስዋ ወዴት     መሄድ እንዳለባትና ምን ማድረግ እንዳለባት ጠይቃኝ መክሬአታለሁ፡፡”
ከዚህችኛዋ እናት ታሪክ የምንረዳው አሁንም ግልጽነት በጎደለው መንገድ ባለቤቷ እንደበደላት እና ...ነገር ግን በቤተሰቦቿ በኩል ያለው እውነታ መገለልን ያስወገዱ እና ነገሮችን በአግባቡ የተረዱ መሆናቸውን ያመላክታል፡፡
ይቀጥላል

Read 3436 times