Saturday, 02 May 2015 10:17

“ሠማያዊ” ከፓርቲያችን ዕውቅና ውጭ ፖስተሮቸ እየተለጠፉ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

     ለምርጫ ቅስቀሳ ባልተፈቀዱ ቦታዎች ላይ ፖስተር ለጥፏል በሚል ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስጠንቀቂያ የደረሰው ሠማያዊ ፓርቲ፤ ድርጊቱ በሌላ አካል እንደተፈፀመና የፈፀመውን አካል ምርጫ ቦርድ አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድለት ጠየቀ፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት ምርጫ ቦርድ የፓርቲው ፖስተሮች በእምነት ተቋማትና ት/ቤቶች አካባቢ ተለጥፈው መገኘታቸውን መግለፁ ትክክል ነው፤ ፓርቲያቸው በማያውቀው መልኩ ተለጥፈው የተገኙ በመሆናቸው ቦርዱ ለጣፊውን አካል አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለቦርዱ አስገብተዋል፡፡
የፓርቲው የቅስቀሳ ፖስተሮችም እየተቀደዱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዮናታን፤ ፓርቲው ቅስቀሳ በሚያደርግባቸው አካባቢዎች ጭምር የቅስቀሳ ፖስተሮቹ የእምነት ተቋማት ላይ ተለጥፈው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱን ሊፈጽም የሚችል የተደራጀ ቡድን ሊኖር እንደሚችልም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግስት አይኤስንና ሽብርተኝነትን ለማውገዝ በጠራው ሠልፍ ላይ ለተፈጠረው ሁከትና ግርግር ሠማያዊ ፓርቲን ተጠያቂ ማድረጉን የተቃወመው ፓርቲው፤ የመንግስት ውንጀላ የሚቀጥል ከሆነ መንግስትን፣ ፌደራል ፖሊስንና የሃሠት ወሬዎችን እያሠራጨ የፓርቲውን ስም እያጐደፈ ነው ያለውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ለመክሰስ እንደሚገደድ አስታውቋል፡፡

Read 1603 times