Saturday, 02 May 2015 10:29

በሶማሊያ የባህር ዘራፊዎች ታፍኜ ነበር

Written by  ኑርሁሴን
Rate this item
(9 votes)

    “ሁላችንም በፍርሐት ውስጥ እንድንገባ አደረጉን፡፡ ግርፋቱንና ስቃዩን በአይኔ ባላየውም ጩኸቱን ግን እሰማው ነበር፡፡”
ባለፈው አመት ሚያዝያ ላይ ነበር ሙምባይ ውስጥ በሚገኝ የኬሚካል ኩባንያ አማካኝነት የባህር ሐይል ኦፊሰር ለመሆን ስልጠና የወሰድኩት። ስራችንን ለመጀመር ወደ መርከቧ የተሳፈርነው ሰዎች እኔን ጨምሮ 22 ነበርን፡፡ ከህንድ የተውጣጡ ፕሮፌሽናል መርከበኞች እና ኢንጂነሮች ይገኙበታል። መርከቧ ላይ ከተሳፈርነው ሰዎች መካከል በእድሜ ትንሹ እኔ ነበርኩ፡፡ 21 ዓመቴ ነው፡፡
መርከባችን የተነሳችው ከህንድ ሲሆን አቅጣጫዋ ደግሞ ወደ ኖርዌይ ነበር፡፡ ጉዞው 25 ቀናቶችን ይወስዳል፡፡ ጉዞ በጀመርን በአራተኛው ቀን ላይ አንድ ባልደረባችን ከፊት ለፊታችን የምትመጣውን ጀልባ ተመልክቶ ጩኸቱን አቀለጠው፡፡ ከኦማን 120 ማይል በሚርቅ ባህር ላይ ነበርን፡፡ ይህ ክልል ደግሞ አደገኛና አስፈሪ ነው፡፡ የጀልባዋን አመጣጥና መጠን ተመልክተን ዘራፊዎች መሆናቸውን አወቅን፡፡
ወዲያውኑ ህንድ ውስጥ ላለው የባህር ሐይል ጣቢያ የሬዲዮ ግንኙነት አደረግሁኝ፡፡ ነገር ግን ዘግይቼ ነበር፡፡ በደቂቃዎች ውስጥ ስድስት የባህር ዘራፊዎች መርከባችን ላይ በመንጠላጠል የጥይት እሩምታ ከፈቱብን፡፡ በጣም አስፈሪና አስደንጋጭ ነበር፡፡ እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አልነበረንም።
ወዲያውኑ በቀማኞቹ እየተገፈተርን ወደ ሞተር መቆጣጠሪያው ክፍል ውስጥ ገባን፡፡ ወለሉ ላይ በደረታችን እንድንተኛ ታዘዝን፡፡ ዘራፊዎቹ ለምንሰራለት ኩባንያ የ15 ሚሊዮን ዶላር ጥያቄ እንደሚያቀርቡና ገንዘቡን ካላገኙ እንደሚገድሉን በተሰባበረ እንግሊዝኛ ደነፉብን፡፡  ከፍተኛ ፍርሐት ዋጠን፡፡ እስከ ቀጣዩ ጧት ድረስ ሁላችንም ከተኛንበት ወለል ላይ ሳንንቀሳቀስ በዝምታ አሳለፍን፡፡ ሌሎች 6 ዘራፊዎች መርከባችንን ከተቀላቀሉ በኋላ ወደ ሶማሊያ ሊወስዱን እንደሆነ ነገሩን፡፡
በመርከብ ላይ ታፍነን ያሳለፍነው አስቸጋሪ ህይወት እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አልነበረም፡፡ በመቆጣጠሪያው ክፍል ውስጥ በየጥጉ ኩርምት ብለን ተቀምጠናል፡፡ መስኮት የሌለው ክፍል በመሆኑ የታፈነ አየር ለመሳብ ተገደናል፡፡ መፀዳጃ ቤት እንድንጠቀም ቢፈቀድልንም ተበላሽቶ በመጥፎ ጠረን ታውዷል፡፡ በዚህ ምክንያት ሁላችንም ታመምን፡፡ ምግብ የሚሰጠን በሳምንት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እሱም ህይወታችንን ለማቆየት እንዲረዳን ያህል ከድንች እና ሽንኩርት የተሰራ ነበር። በኋላ ላይ እግራችንን እንድንዘረጋ ስለፈቀዱልን ትንሽ ተንፈስ አልን፡፡
ዘራፊዎቹ የደቀኑብን ጠብመንጃ የማምለጥ ተስፋችንን ገድሎታል፡፡ ከነሱ ጋር ወዳጅነት እንዳንፈጥር ደግሞ ዘወትር ያስፈራሩናል፣ ይደበድቡናል፡፡ በኔ ላይ መጥፎ ድብደባ እንዳይደርስብኝ የተቻለኝን ባደርግም ባልደረቦቼ ግን ክፉኛ ሲቀጠቀጡና ሲሰቃዩ ተመልክቼያለሁ። አንደኛውን ባልደረባዬን በኤሌክትሪክ አሰቃይተውታል፤ ሌላኛውን ደግሞ ከብረት ጋር ጠፍረው በማሰር ለረዥም ሰዓት ደብድበውታል። በሌላኛው ክፍል ውስጥ የነበሩ ወዳጆቼ እንደሚሰቃዩ በድምፃቸው አረጋግጫለሁ፡፡ አሁን ድረስ የስቃይ ድምፃቸው ያቃጭልብኛል፡፡ እኔን ልክ እንደ ሌሎቹ ባልደረቦቼ ለምን ብዙ እንዳላሰቃዩኝ አላውቅም፡፡ ምን አልባት ገና ለጋ አልያም የማልጠቅም መሆኔን ተረድተው ይሆናል።
አንዳንድ ባልደረቦቼ ከዘራፊዎቹ ጋር ይፋጠጡ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን ከእንዲህ መሰሉ ነገር እጠነቀቅ ነበር፡፡ በእያንዳንዱ ቀን ጧት፤ ከተኛሁበት የብረት ወለል ላይ ስነቃ በዚያው ቀን እንድሞት እመኝ ነበር። ወዲያው ደግሞ ራሴን በማረጋጋት የወደፊቱን ለማየት እቅበጠበጣለሁ፡፡ ማድረግ የቻልኩት ግን ዝም ብዬ መጠበቅ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ከመካከላችን ውስጥ አንደኛችንን መርጠው ህንድ ለሚገኘው ኩባንያችን እንድንደውል ያደርጉ ነበር፡፡ እኛም በተሰጠን የስልክ እድል ተጠቅመን ህይወታችንን እንዲታደጉልን የኩባንያ ሰዎቻችንን እንማፀናለን፡፡ እነሱ ግን የገንዘቡ መጠን እስካልተቀነሰላቸው ድረስ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ይነግሩናል፡፡
በመጀመሪያዎቹ አራት ወራቶች ውስጥ፤ በወር አንድ ጊዜ ከቤተሰቦቻችን ጋር በስልክ እንድንገናኝ ተፈቀደልን፡፡ ዘራፊዎቹ ይህን ያደረጉት ቤተሰቦቻችን ኩባንያ ላይ ግፊት እንዲያደርጉ ነበር። ነገር ግን ከቤተሰቦቻችን ጋር ገና ጥቂት ቃላቶችን ብቻ እንደተለዋወጥን ስልኩን ይነጥቁናል፡፡ ከስልኩ መቋረጥ ጋር የኛም አንጀት አብሮ ይቆረጣል፡፡
ገንዘቡ ሳይከፈል ብዙ ወራቶች ካለፉ በኋላ ዘራፊዎቹ ካፒቴናችንን ወስደው በሌላ ጀልባ ለብቻው አስቀመጡት፡፡ ይገድሉታል በሚል ሁላችንም ጭንቀት ውስጥ ገባን፡፡ እነሱ ግን ኩባንያው የተጠየቀውን ገንዘብ እንዲከፍል አሁንም የበለጠ እንድንለምን ነገሩን፡፡ ከ238 ቀናቶች በኋላ፣ እንድናለን ብለን ባልገመትንበት ሰዓት ኩባንያችን አምስት ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማማ፡፡ የጀርመን መርከብ ሊወስደን እንደሚመጣም ተነገረን፡፡ ዘራፊዎቹ ገንዘባቸውን ካገኙ በኋላ ሌላ ጀልባ ላይ ተሳፍረው ከአካባቢው ጠፉ፡፡ የተባለችው የጀርመን መርከብ መጥታ ስትወስደን ደስታዬ ወደር አልነበረውም፡፡ ከ238 ቀናት በኋላ አይኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ብርሐን አየ፡፡ ደንዝዤ ስለነበረ አላለቀስኩም፡፡ ሌሎቹ ግን እየነፈረቁ ነበር፡፡ ለቅሷቸውን መቆጣጠር አልቻሉም፡፡ እኔ እንደገና የተወለድኩ ያህል ነበር የተሰማኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ የበላሁት ምግብ፣ የወሰድኩት ሻወር፣ የቀየርኩት ልብስ ሁሉ ለኔ የማይታመን እንግዳ ነገር ነበር፡፡ ከስድስት ቀናት በኋላ ቤተሰቦቼ ጋር ተቀላቀልኩ። ሰውነቴ ከመክሳቱ በተጨማሪ ሁለመናዬ አስቀያሚ ሆኗል፡፡ ይህን ጉስቁልናዬን የተመለከቱት ቤተሰቦቼ በጣም አለቀሱ፡፡ ወደተከራየሁት መኖሪያ እንደተመለስኩ መርከብ ላይ በተፈጠረብኝ አጠቃላይ ሁኔታ ንዴቴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም አይነት ህክምና ለመውሰድ አልፈለግሁም፡፡ በህይወቴ ውስጥ የተፈጠረው ይህ አስቀያሚ አጋጣሚ ስራዬን እንድተው አላደረገኝም፡፡ እንዲያውም ተጨማሪ የመርከበኝነት ስልጠና ከወሰድኩ በኋላ እንደገና ወደ ባህር ስራዬ ተመለስኩ፡፡ ዘራፊዎቹ የህይወቴን አቅጣጫ እንዲቀይሩት አላደረግሁም፡፡ ጉዳቱን እንደሆነ አንዴ ቀምሼዋለሁ፤ ከዚህ በላይ ምኔን ይጉዱት?
(ዲፔንድራ ይሀንን ታሪኩን በራሱ ድምፅ ቀርፆ በኢንተርኔት ለቆታል፡፡)   

Read 5851 times