Saturday, 02 May 2015 10:32

ጣት መቀሰር እስከመቼ?!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

(ቆም ብሎ ማሰቡ ለራስም ለሀገርም ይጠቅማል!)

   “ህዝቡ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው፤ በሀገሪቱ ውስጥ ስራ አጥነት ተንሰራፍቶአል፤ መብራት፣ ውሃና ኔትወርክ የለም፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በትራንስፖርት ችግር እየተንገላቱ ነው፤ በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ፤ የግሉ ፕሬስ በነጻነት መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ለመጥፋት ተቃርቦአል፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚፈለገው መልኩ በነጻነት መንቀሳቀስ አልቻሉም፤ በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን ለአደጋ በሚዳርግ መልኩ እየተሰደዱ ነው፡፡…” ሌሎችም ለቁጥር የሚታክቱ ምሬቶችና አቤቱታዎች ከየአቅጣጫው በየጊዜው ይሰማሉ፡፡ በዚችው በእኛዋ ሀገር፡፡
ከእነዚህ አቤቱታዎች አንዳንዶቹ መንግስትም ጭምር የሚቀበላቸው (የሚያምናቸው) ቢሆኑም እስካሁንም ድረስ ችግሮቹ መቀረፍ አልቻሉም፡፡ ለምን?! ምክንያቱ የሚመስለኝ የችግሮቹ መንስኤዎች ላይ አትኩሮ ችግሮቹን ለመቅረፍ ከመስራት ይልቅ ሰበብ መስጠት ወይም ጥፋቱን ተሸካሚ ፈልጎ በማሸከም ላይ ስለሚታትር ይመስለኛል፡፡ ሐጢአቱን ለሌሎች አሸክሞ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ፡፡
እስቲ ጥቂት ወደ ኋላ መለስ እንበልና ከላይ ለተነሱትና ለሌሎች አንዳንድ ችግሮች መንግስት ተጠያቂ ያደረገው እነማንን እንደሆነ እናስታውስ፡፡… በአጭሩ ለየትኛውም ችግር ራሱን ተጠያቂ አላደረገም ማለት ይቀላል፡፡ በተደጋጋሚ ችግሮቹን ከጉዳዮቹ ጋር እጅግ በጣም ጥቂት ንክኪ ያላቸው አካላት ላይ ጭኖ ራሱን “ነጻ አድርጎአል፡፡” አሁንም እየሆነ ያለው እንደዛ ይመስለኛል፡፡ ጊዜ ያለወጠው አዙሪት!
ዛሬም እንደ ቀድሞው መንግስትና ሚዲያዎቹ በደቡብ አፍሪካ፣ በሊቢያ በረሀና በሜዴትራንያን ባህር ዳርቻ ስደተኛ ወገኖቻችን በግፍ መገደላቸውን ተከትሎ ለችግሩና ለጥፋቱ ብቸኛ ተጠያቂ “ህገ ወጥ ደላሎች” (ቃሉ ራሱ የተጣራ ፍቺን ይሻል) ናቸው እያሉን ነው፡፡ ዘይገርም ነው! መቼ ይሆን ጣታችንን ሌሎች ላይ ብቻ መቀሰር የምናቆው?! መቼስ ነው ማድበስበሱን ትተን ከእውነታው ጋር መጋፈጥ የምንችለው?! ያሰኛል፡፡
ከምንጊዜውም በበለጠ መልኩ በአሁኑ ወቅት በርካታ ወገኖቻችን ህይወታቸውን ለአደጋ በሚዳርግ መንገድ ከሀገራቸው ተሰደዋል፤ እየተሰደዱም ነው፡፡ በመንገዳቸውም ሆነ ተሰደው በሚኖሩባቸው ሀገሮችም ህይታቸውን እስከሚያጡ ድረስ በርካታ እንግልቶች እየደረሱባቸው ነው፡፡ ይሄ ሀቅ ነው፡፡ የአለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የሠርክ ወሬ የሆነና እኛም የምንስማማበት ሀቅ፡፡ ታዲያ ጉዳዩ አቅጣጫውን መሳት የጀመረውና አለመተማመኑ የጎላው ዜጎቻችን የሚሰደዱበትን ምክንያት መጠየቅ ሲጀመር ነው፡፡ ያኔ ጉዳዩ ከመፍትሔው መነጠል ጀመረ፡፡ የሚመለከተውም ለዜጎቹ ኃላፊነት እንደሚሰማው አካል የችግሩን ምክንያቶች አምኖና ተቀብሎ በመጋፈጥ ችግሩን ከስሩ ለመቅረፍ ከመሞከር ይልቅ ችግሩ የሚሳበብበትን አካል መፈለግ ያዘ፡፡ የዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂ እከሌ ነው ለማለት፡፡ ያስገርማል፤ ያሳዝናልም!
እርግጥ ነው፡፡ ለአንድ ክስተት መፈጠር በርካታ ምክንቶች ሰበብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን እያንዳንዱ ምክንያቶች ምን ያህል ድርሻ አላቸው? የምክንያቶቹ መነሻስ (ሰበብ) ምንድን ነው? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ እውነታውን እስከፈለግን ድረስ ይህ ወደ እርግጡ ድምዳሜ የሚያደርሰን ጤናማ መንገድ ይመስለኛል፡፡…
እርግጥ ነው ሰዎች ከሀገራቸው እንዲሰደዱ “ህገ ወጥ ደላሎች” የሚያደርጉት የራሱ አስተዋጽኦ አለ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ሌሎች ጭፍጫፊ ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ መልካም፡፡… ቀጥለን ግን መጠየቅ ያለብን እነዚህ ምክንያቶች ለችግሩ የሚያዋጡት ድርሻ ምን ያህል ነው? የሚለውን ነው፡፡ መልሱ ብዙም ጥናትን የሚፈልግ አይደለም፡፡ ብዙም ሳንደክም ልንመልሰው እንችላለን፡፡ በመንግስት እየተጠቀሱ ያሉት ምክንያቶች በምንም መልኩ ለዜጎች መሰደድ በዋና ምክንያትነት ሊጠቀሱ ቀርቶ ስሌት ውስጥም የሚገቡ አይደሉም፡፡ ድርሻቸው ጥቂት ነውና፡፡
እውነቱን እንናገር ከተባለ፣ ወገኖቻችን እንዲሰደዱ ግፊት የሆኗቸው ሌሎች በዋናነት ሊጠቀሱ የሚገቡ ምክንያቶች አሉ፡፡ እነዚህን ምክንያቶች ለማወቅ የሚፈልግ አካል ካለ ተጓዦቹንና ከስደት ተመላሾቹን ቀረብ ብሎ ይጠይቃቸው፡፡ ሀገራቸውንና ወገኖቻቸውን ተለይተውና ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚሰደዱባቸውን ምክንያቶች ይነግሩታል፡፡…  ምክንያታቸው የኢኮኖሚ ችግር ነው፡፡ የእንጀራ ጥያቄ! ደግሞም ይህንን ማወቅ ውስብስብና የበዛ ምርምርን የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሽሽቱንና ማድበስበሱን ስለፈለግነው እንጂ ለማንም ያልተደበቀ ያፈጠጠ ሀቅ ነው፡፡
አንዳንድ ነጥቦችን እያነሳን ጉዳዩን ለመመርመር እንሞክር፡፡ እስቲ በመንግስትና በሚዲያ ተቋማቱ “ፍረጃ” ተስማምተን፣ ለጥፋቱ ተጠያቂዎች “ህገ ወጥ ደላሎች ናቸው” ብለን እንነሳ፡፡ የምንደርስበት ውጤት (ብዙም ስሌት ውስጥ ሊገቡ የማይገቡ ሌሎች ጭፍጫፊ ሰበቦች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ) አሁንም የችግሩ ዋና ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እንዴት?
ሲጀመር ዜጎች የ“ህገ ወጥ ደላሎቹ”ን ስብከት ሰምተውና አምነው ከሆነ የሚሰደዱት፣ ደላሎቹ ጋር የወሰዳቸውም ሆነ ደላሎቹን እንዲያምኑ ያደረጋቸው ያለባቸው የኢኮኖሚ  ችግር ነው፡፡ የኢኮኖሚ ችግር ከሌለባቸውና የዳቦ ጥያቄያቸውን መመለስ የሚችሉ ከሆነማ ለምን ከደላሎቹ ጋር ይገናኛሉ? ለምንስ ደላሎቹ የሚሏቸውን ያምናሉ? መቼስ “መረጃው ስለሌላቸው ነው” የሚል የዋህ እንደማይኖር እገምታለሁ፡፡
ሀገር አቋርጠው ሲጓዙም ሆነ ደርሰው በሚኖሩባቸው ሀገሮች ህይወትን እስከማጣት የሚደርስ እንግልት ሊያገኛቸው እንደሚችል እኮ “ህገ ወጥ” ደላሎቹ “ታገኛላችሁ” ብለው ከሚሰብኳቸው በበለጠ መንግስትም ሆነ በርካታ መገናኛ ብዙሀን ያለማቋረጥ ነግረዋቸዋል፤ እየነገሩአቸውም ነው፡፡ ግን ከመሄድ አላመነቱም፡፡ ለምን? ማመን ስለማንፈለግ እንጂ መልሱ አሻሚ አይደለም፡፡ ይህንን የሚያጠነክር ሌላም ነጥብ እዚህ ጋ ማንሳት እንችላለን፡፡ በተሰደዱበት ሀገር ሲደርስባቸው ከነበረው እንግልት፣ ከሞት መንጋጋ አምልጠው… የመጡት ወገኖቻችንም ውለው ሳያድሩ አሁንም ተመልሰው ከሞት ወዳመለጡባቸው ሀገሮች እየሄዱ ነው፡፡ መቼም እጅግ የዋህ ካልሆንን በቀር “እነሱም በደላሎቹ ተታለው ነው” አንልም፡፡ አይተውታልና፡፡ ይኸው ነው፤ ማመን ቢገደንም ቅሉ በዚህም አልን በዚያ ዜጎቻችን ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ከሚሰደዱባቸው ምክንያቶች ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የኢኮኖሚ ችግር፣ የእንጀራ ጥያቄ… ነው፡፡ ይህንን ማመን ግን ተጠያቂ ስለሚያደርገን ሳይሆን አይቀርም፤ ሐጢአቱን ሁሉ ለደላሎች ሰጥተን ለመንጻት የምንሞክረው፡፡
ደግሞም እኮ (ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ ትርፍ ካልሆነ በቀር) በደሉን የሚሸከም አካል ፈልገን እሱ ላይ ጣት መቀሰር በምንም ስሌት መፍትሔ አይደለም፡፡ መፍትሔው ስህተትንና ድክመትን አምኖ መቀበልና ችግሩን ፊት ለፊት መጋፈጥ ነው፡፡ በዚህም የችግሮቹ ምክንያቶች ላይ በማተኮር መስራት ነው ለሀገርም ለራስም የሚጠቅመው፡፡ ችግሩን ሌሎች ላይ ስላንከባለልንና ጣታችንን ስለቀሰርን ወይም ጉዳዩ ሌላ አቅጣጫና ትርጉም እንዲይዝ ስለደከምን “ነጻ” የምንሆን ይመስለናል እንጂ አንሆንም፡፡ ይህንንም በተደጋጋሚ አይተነዋል፡፡ እያየነውም ነው፡፡
የትናንት ቀመር ለትናንት እንጂ ለዛሬ አይሰምርም፡፡ ይህ ዘመን ሌላ ነው፡፡ የህዝቡ አስተሳሰብም ሆነ እውቀት የቀድሞው አይደለም፡፡ ተለውጦአል፤ አድጓልም”፡፡ ያልነውንና የሰጠነውን ብቻ የሚያምንበትና የሚቀበልበት ዘመን አልፎአል፡፡ ስለ ሁሉም ነገር ምናልባትም ከምንነግረው በላይ ያውቃል፡፡ ስለ ሁሉም መረጃ አለው፡፡ ለቴክኖሎጂው ምስጋና ይግባውና ትውልዱ መረጃን በእጁና በኪሱ ይዞ ነው የሚዞረው፡፡ ለዚህም ነው በአዎንታም ይሁን በአሉታ ለየክስተቱ ምላሽ ሲሰጥ የሚስተዋለው፡፡ ይህንን ማወቅና መገንዘብ፣ ተገንዝቦም ራስን ከትውልድና ከሁኔታዎች ጋር ማዘመን ከአንድ መንግስት የሚጠበቅ ብልህነት ነው፡፡ ቆም ብሎ ማሰቡ እንደ ግለሰብ፣ እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ መንግስት… ይጠቅማል፡፡
በተለይ አሁን ከምንጊዜውም በላይ ሀገራችንና ዜጎቿ በየአቅጣጫው እየተፈተኑ ያሉበት ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም ሀገሩንና ህዝቦቿን እወዳለሁ የሚል ዜጋም ሆነ መንግስት ዛሬ ትናንት እንዳልሆነ ሊያስተውል፣ ቆም ብሎም ሊያስብ ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ ለሁሉም ይጠቅማልና፡፡… በተለይ መንግስት ከተለመደው አዙሪት መውጣት፣ ኃላፊነት መውሰድና ከችግሮች ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ ይኖርበታል፡፡ እስከፈለገ ድረስ ይህንን ማድረግ አያቅትም፡፡ ሥራን መስራት፣ ኃላፊነትን መወጣት ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ሁሌም ሌሎችን ተጠያቂ ማድረግና ጣትን መቀሰር ራስን ለትዝብት ከመዳረግ ባለፈ አንዳች ትርፍ የለውም፡፡ ደጃፍን እንጂ ወንዝ አያሻግርም፡፡  
አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር እውነቱን አምኖና ተጋፍጦ ዘላቂ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ ጣት የምንቀስርበትን መፈለግ ለጊዜው የሚበጅ ቢመስለንም የነገ እጥፍ ኪሳራ ነው፡፡ ደግሞም እኮ ድክመትን መቀበል ጀግንነት እንጂ ሽንፈትና ክስረት አይደለም፡፡ አያስከፋምም፡፡ የሚያስከፋውስ ችግሮችን ሌሎች ላይ መጣል፣ ለማድበስበስ መሞከርና ችግሩን ላልተገባ የፖለቲካ ትርፍ ለማዋል መድከም ነው፡፡
ደግሞም እንደ መንግስት በዚህ ሂደት ውስጥ የምናደርጋት እያንዳንዷ ክንውን፣ የዛሬ አንድምታዋንና ነገ የምታፈራውን ፍሬ መገመት ይገባል፡፡ እስከ ዛሬ የዘራነው ምን እንዳፈራልን እያየን ነው፡፡ ዛሬ የምንዘራውም ነገ ልጆቻችንን ሊያጠፋ እንደሚችል እንገንዘብ፡፡ ፊታችን ስለቆመው ዛሬ ብቻ ሳይሆን ስለነገም ቆም ብለን እናስብ፡፡ ደግሞም የምር ከፈለግን አያቅተንም፡፡ በፍጹም!
መልካም ሰንበት!

Read 2424 times