Saturday, 02 May 2015 12:09

በኔፓል ርዕደ-መሬት የሞቱት ከ5ሺህ በላይ ደርሰዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው ቅዳሜ በኔፓል በተከሰተውና በሬክተር ስኬል 7.8 በተመዘገበው አሰቃቂ የርዕደ-መሬት አደጋ የሟቾች ቁጥር ከ5ሺህ በላይ መድረሱ መረጋገጡን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
በርዕደ-መሬቱ የተጎዱ ዜጎችን የማፈላለጉና እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎችን የመድረሱ እንቅስቃሴ በአስቸጋሪ የአየር ንብረት ሳቢያ አዳጋች ሆኖ የቀጠለ ሲሆን እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከ5ሺህ በላይ መድረሱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪ ከ10ሺህ በላይ ሰዎችም የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፣ ፍለጋው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የሟቾችም ሆነ የቁስለኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ተገምቷል፡፡  
ኔፓልን መልሶ ለማቋቋም ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል ተብሎ እንደሚገመት ያስታወቀው ዘገባው፣ የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት በበኩሉ፤ በአደጋው የደረሰው ጥፋት እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት መግለጹን አስታውቋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ላንግታንግ በተባለችው የኔፓል አካባቢ በደረሱ ሁለት የመሬት መንሸራተት አደጋዎች፣ ከ200 በላይ ሰዎች የደረሱበት እንደጠፋም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱሺል ኮይራላ በአደጋው ህይወታቸው ያለፈ ዜጎችን ለመዘከር ባለፈው ማክሰኞ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ብሄራዊ ሃዘን ያወጁ ሲሆን ባለፉት አስር አመታት በርዕደ-መሬት ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ዜጎች ቁጥር ከ10 ሺህ በላይ እንደሚደርስም አስታውቀዋል፡፡
በአደጋው የተጎዱ ዜጎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የድረሱልኝ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሂሊኮፕተር የታገዘ እንቅስቃሴ እየተደረገ ቢገኝም፣ ከፍተኛ ዝናብና ውሽንፍር ከመኖሩና ከቦታዎቹ ተራራማነት ጋር በተያያዘ፣ በከፋ ሁኔታ በተጎዱ አካባቢዎች ፈጥኖ ለመድረስ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የቅዳሜው የኔፓል ርዕደ-መሬት ስምንት ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ተጠቂ እንዳደረገ ያስታወቀ ሲሆን፣ ለአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ እርዳታ የሚውል 15 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የተመድ ቃል አቀባይ ፋራህ ሃቅ እንዳሉት፤ የገንዘብ ድጋፉ ተጎጂዎችን ለመታደግ በመስራት ላይ የሚገኙ የሰብዓዊ ተቋማትን እንቅስቃሴ ለማሳደግና ለተጎጂዎቹ የመጠለያ፣ የውሃ፣ የመድሃኒትና የሌሎች አገልግሎቶች አቅርቦቶችን ለማሟላት የሚውል ነው።
ህንድ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ማሌዢያ፣ ፓኪስታን እና እስራኤል ተጎጂዎችን ለመርዳት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ አውሮፕላኖችን ወደ ኔፓል የላኩ ሲሆን አሜሪካ በበኩሏ ለፈጥኖ ደራሽ እርዳታ የሚውል 10 ሚሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ከመግባቷ በተጨማሪ የእርዳታ ድርጅቶቿን በአደጋው የተጎዱትን ዜጎች እንዲረዱ ወደ ኔፓል ልካለች፡፡

Read 1216 times