Saturday, 02 May 2015 12:09

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና ዮሃንስ ሳህሌ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

የባሬቶ ስንብት
ለሁለት ወራት ስፖርት ቤተሰቡን ውዥንብር ውስጥ ከቶ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ቆይታ ባለፈው ሳምንት  መቋጫውን አግኝቷል፡፡ ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ ባለፈው ማክሰኞ ወደ ትውልድ አገራቸው ከማምራታቸው በፊት የስንብት መግለጫቸውን ሰጥተው ነበር፡፡በትውልድ ህንዳዊ በዜግነት ፖርቹጋላዊ የሆኑት አሰልጣኙ  በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ለ10ወራት አገልግለዋል፡፡ ሰውነት ቢሻውን  ተክተው ስራቸውን ከጀመሩ በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እና ሌሎች የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ 19 ግጥሚያዎችን አከናውነው በ11ዱ ተሸንፈዋል፤ በአራቱ አቻ ሲወጡ እንዲሁም አራቱን ድል አድርገዋል፡፡ ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ ስምምነት መለያየታቸውን ለማመልከት በተዘጋጀው የስንብት  መግለጫቸው ላይ ሲናገሩ ‹‹በስንብቱ ሁለት ዓይነት ስሜቶች ተፈራርቀውብኛል፡፡ ጥሩው ስሜት ወደ ቤተሰቤ እና ሀገሬ መመለሴ ሲሆን መጥፎው  ደግሞ ከጥሩው የኢትዮጵያ ህዝብ መለያየቴ ነው፡፡ ኢትዮጵያን መቼም አልረሳትም ህዝቧ እግር ኳስን ይወዳል በተለይም ሀገሪቷ እንደ ቤት እንድትሰማኝ ላደረጉት በየስፍራው የደገፉኝን አመሰግናለሁ፡፡ ወደ ትግራይም ደብረዘይትም አዳማም በሄድኩባቸው ሁሉ ላየሁት ነገር ተደስቻለሁ›› ብለዋል፡፡ ለ10 ወራት በቆዩበት ሃላፊነት በተለይ ሶስት ኢትዮጵያዊ  አሰልጣኞች ገብረመድህን ሀይሌ፤ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እና ጳውሎስ ጌታቸው  ለሰጧቸው እገዛ ምስጋናቸውን የገለፁት ባሬቶ፤ ከፌዴሬሽን በኩል የፅህፈት ቤት ሀላፊውን አቶ ዘሪሁንን እንዲሁም ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ ፤ አብርሃም ተክለሀይማኖትን እና የተቋሙ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ ተክለወይኒ አሰፋን ጭምር ላደረጉላቸው ቅን ትብብር ልባዊ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡ በስንብት መግለጫቸው ለመገናኛ ብዙሃናት ልዩ መልዕክት ያስተላለፉት ማርያኖ ባሬቶ፤ ለአገር ውስጥ የእግር ኳስ ውድድሮች በቂ ትኩረት መሰጠት እንዳለባቸው ፤ በሊጉ ታዳጊዎች እና ብቃት ያላቸው ተጫዋቾችንን ለማየት ጫና በመፍጠር መስራት እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡
የዮሃንስ ቅጥር
ከማርያኖ ባሬቶ ስንብት በኋላ የኢትዮጵያ  እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዮሐንስ ሳህሌን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ እንዲሰራ የሾመው  አስቸኳይ ስብሰባ በማካሄድ ከብሄራዊ ከቴክኒክና ልማት እንዲሁም ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተውጣጣ ኮሚቴ በማቋቋም ምርጫውን በፍጥነት በማከናወን አቅዶ ነበር፡፡
በብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ምርጫው በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋና አሰልጣኞች እድል የሰጠው ፌደሬሽኑ ባዘጋጀው የመምረጫ መስፈርት  የሁሉንም ብቃትና ደረጃ በዝርዝር በማየት አራት ተወዳዳሪዎችን በኮሚቴው አማካኝነት ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለይቶ አቅርቧል፡፡ አሰልጣኞቹ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ያላቸው ውጤት እና የትምህርት ደረጃቸውን ሲያወዳድርም ከአራቱ አሰልጣኞች ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም እና ፋሲል ተካልኝ የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ሲያገኙ አዲሱ የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ለመሾም የበቃው ዮሐንስ ሳህሌ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት የደደቢት ክለብ ዋና አሰልጣኝ ለሆነው ዮሃንስ  ሳህሌ አስፈላጊውን የቅጥር ስርዓት በፍጥነት በማጠናቀቅ በቀጣይ ሳምንት ስራውን እንደሚጀምር ፌደሬሽኑ ገልጿል፡፡
የዮሃንስ ልምድ፤ ደሞዛቸው
በእግር ኳስ ስልጠና ትምህርታቸው የኢንስትራክተርነት ማእረግ እንዳላቸው የሚነገርላቸው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በተጫዋችነት ዘመናቸው ለራስ ሆቴል፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጫወት አሳልፈዋል፡፡ በ1975 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ዋንጫን ከጊዮርጊስ ጋር ማሸነፍም ችለዋል፡፡ በአሜሪካም ለተለያዩ ክለቦች ተጫውተው ያሳለፉት ዮሃንስ ሳህሌ፤ በአሰልጣኝነት ህይወታቸው በአሜሪካ የተለያዩ የኮሌጅ ክለቦችን ለማሰልጠንም የቻሉ ነበሩ፡፡ ከአሜሪካ መልስ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ቴክኒክ ዳይሬክተርም የነበሩ ሲሆን ከዚያ በኋላ የሃረር ቢራ ክለብ ስራ አስኪያጅ ሆነው ከሰሩ በኋላ በ2006 አ.ም የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድንን ዋና አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል፡፡ አስቀድመው የደደቢት እግርኳስ ክለብን በቴክኒካል ዳይሬክተርነት ካገለገሉም በኋላ የክለቡ አሰልጣኝ ሆነው በመቀጠር ያለፉትን ወራት ቡድኑን በሃላፊነት መርተዋል፡፡ ከኢትዮጵያዊነታቸው በተጨማሪም የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው አሰልጣኙ እግር ኳስን በአሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሆላንድ እና ጀርመን በመማር የስልጠና ብቃታቸውን አሳድገዋል፡፡ አሰልጣኙ በተለይ በስፖርት ቤተሰቡ የሚታወቁት ከአሜሪካ የረጅም ዘመን ቆይታቸው ከተመለሱ በኋላ በ1990ዎቹ አጋማሽ ለአሰልጣኞች በሰጧቸው የአሰልጣኝነት ስልጠና ኮርሶች ነው፡፡ በብሄራዊ ቡድን  ደረጃ የማሰልጠን ልምድ ባይኖራቸውም በዩናይትድ ስቴትስ የወጣቶች አካዳሚዎች ውስጥ መስራታቸውና የማስተዳደር ክህሎት በመያዛቸው  ቡድኑን ወደፊት ሊያራምዱት ይችላሉ ተብሏል፡፡
የ59 ዓመቱ ማርያኖ ባሬቶ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነታቸው የተጣራ ወርሃዊ ደሞዛቸው 18ሺ ዶላር ሲሆን ሌሎች ወጭዎችን ሳይጨመር በ10 ወራት ቆይታቸው  በደሞዝ ብቻ 180ሺ ዶላር አግኝተዋል፡፡ ኮንትራታቸው ሲቋረጥ ደግሞ የ3 ወራት ደሞዛቸው 54ሺ ዶላር በፌደሬሽኑ ተከፍሏቸዋል፡፡ ማርያኖ ባሬቶ በአጠቃላይ በደሞዝ ብቻ ፌደሬሽኑን ያስወጡት 234 ሺ ዶላር ነበር፡፡ በአንፃሩ የአሁኑ የብሄራዊ ቡድን ኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቢያንስ ከ80ሺህ-100ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ ይከፈላቸዋል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ከማርያኖ ባሬቶ በፊት የነበሩት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ደሞዛቸው 60ሺ ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ስለ ኢትዮጵያዊ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለብሄራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ቅጥር የጀመረው ከ1946 ጀምሮ እንደሆነ ታዋቂው የእግር ኳስ ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ ባንድ ወቅት አቅርቦት በነበረው ጥናታዊ ፅሁፍ ተመልክቷል፡፡ በእግር ኳስ ፌደሬሽን ከመጀመሪያው ተቀጣሪ የውጭ አሰልጣኝ ኦስትሪያዊው ጆርጅ ብራውን እስከ ማርያኖ ባሬቶ ድረስ 39 የውጭ አሰልጣኝ በመቅጠር ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ መሞከሩን በፅሁፉ ያመለከተው ገነነ መኩርያ፤ ከዚህ ጋር አያይዞ ባቀረበው ትንታኔ በዋና ብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት ከዮሃንስ ሳህሌ በፊት 41 ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች በሃላፊነቱ ማለፋቸውን ሲዘረዝር  አዳሙ አለሙ፤ጸሀዬ ባህረ፤ሉቻኖ ቫሳሎ፤ታደሰ ወልዳረጋይ፤ሽፈራው አጎናፍር፤፤መንግስቱ ወርቁ፤ዶክተር ተስፋዬ ጥላሁን፤አስራት ሀይሌ፤ስዩም አባተ፤ጌታሁን ገብረጊዮርጊስ፤ ካሳሁን ተካ አዳነ ሀይለየሱስ፤ጸጋዬ ደስታ፤ሰውነት ቢሻው ፤መኩሪያ አሸብር........ እና ሌሎችም መሆናቸውን ጠቃቅሷል፡፡ የእግር ኳስ ጋዜጠኛው ገነነ መኩርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው ከሰሩት 41 ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች መካከል 13ቱ 2 እና ከሁለት ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ ተቀጥረው መስራታቸውን አብራርቷል፡፡  ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት የተሾሙ 42ኛ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ናቸው ማለት ነው፡፡
የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በአፍሪካ እግር ኳስ ከፍተኛ ክብር ቦታ ያላቸው ይድነቃቸው ተሰማ ሲሆኑ በ1962 እ.ኤ.አ ለአንድ አመት በሃላፊነቱ ቆይተዋል፡፡ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ለብሄራዊ ቡድኑ መቀጠር የቻለው ከ20 ዓመት በኋላ ሲሆን ሃላፊነቱን ሊያገኙ የበቁት በተጨዋችነት በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያ ብቸኛውን የሻምፒዮንነት ክብር እንድታገኝ ያስቻሉት ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ ነበሩ፡፡ ከ1982 እስከ 87 እኤአ ድረስ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በሃላፊነት የሰሩት ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ ለአምስት አመታት በሃላፊነቱ መቆየት በተከታታይ ዓመታት ለረጅም ጊዜ የቆዩ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ ስዩም አባተ፤ ካሳሁን ተካ እያንዳንዳቸው ለሶስት ጊዜያት በተለያዩ ጊዜያት፤ ሰውነት ቢሻው ለሶስት አመት በተከታታይ፤ አስራት ሃይሌ ለሁለት ጊዜያት በተለያየ ቅጥር ብሄራዊ ቡድኑን በሃላፊነት በመምራታቸው ታሪክ ያስታውሳቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተሳተፈባቸው 10 የአፍሪካ ዋንጫዎች ሁለት ጊዜ ብቻ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኞች በሃላፊነት ሰርተዋል፡፡ እነሱም መንግስቱ ወርቁ እና ሰውነት ቢሻው ናቸው፡፡ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ አሰልጣኞች ውጤታማው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ናቸው፡፡ በእርግጥ አሁን 63 ዓመት የሞላቸው ሰውነት ቢሻው ለሁለት ጊዜያት ብሄራዊ ቡድኑ ይዘው ለአምስት አመታት ሰርተዋል፡፡ የሴካፋ ዋንጫን አግኝተዋል፤ ከ31 ዓመታት ቆይታ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ አብቅተዋል፡፡መንግስቱ ወርቁ ደግሞ በ5 አመታት የስራ ዘመናቸው በ1982 ብሄራዊ ቡድኑን ለ10ኛው አፍሪካ ዋንጫ ይዘው የቀረቡ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ የሚጠቀሱት አሰልጣኝ አስራት ሃይሌ ሲሆኑ በሶስት የተለያዩ ጊዜያት ብሄራዊ ቡድኑን በሃላፊነት ይዘው ሁለት የሴካፋ ዋንጫዎችንም አግኝተዋል፡፡
ዮሃንስ የሚፈተኑባቸው ማጣርያዎችና ተቀናቃኞቻቸው
የኢትዮጵያ  ብሄራዊ  ቡድን ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በቻን 2016 እና በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ  የማጣርያ ውድድሮች የሚሳተፍ ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ በ2018 እኤአ ለሚካሄደው 21ኛው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የጥሎ ማለፍ ማጣርያዎች ናቸው፡፡ አዲሱ የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ  ዮሃንስ ሳህሌ  በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የሚሰጣቸው የኮንትራት ቆይታ ከላይ በተጠቀሱት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚኖራቸውን ስኬት በመንተራስ የሚለካ ይሆናል፡፡ ለዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የመጀመርያው የነጥብ ጨዋታቸው ከወር በኋላ በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሌሶቶን የሚያስተናግዱበት ይሆናል፡፡ ከዚያም በሁለተኛ ጨዋታቸው በ2016 የቻን ማጣርያ ኬንያን በሜዳቸው ከዚያም  ከሶስት ሳምንታት በኋላ ከሜዳቸው ውጭ የሚገጥሙበት ነው፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ ዞን በ2018 በራሽያ አዘጋጅነት ለሚደረገው 21ኛው ዓለም ዋንጫ ማጣርያዎቹ በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም ላይ ይጀመራሉ፡፡ 52 አገራት  በ9 ወራት ውስጥ በአራት ዙር የማጣርያ ምእራፎች ለሚገቡበት ፉክክር የመጀመርያው የቅድመ ማጣርያ ድልድል ከወር በኋላ በሩስያ የሚወጣ ሲሆን ኢትዮጵያ በሶስት ዙር ቅድመ ማጣርያዎች በጥሎማለፍ ከሶስት የአፍሪካ ቡድኖች ጋር የምትገናኝ ይሆናል፡፡
በ2017 እኤአ ጋቦን በምታዘጋጀው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሚሳተፍበት የምድብ ማጣርያ በምድብ 10 ከአልጄርያ፤ ከሌሶቶ እና ከሲሸልስ ጋር መደልደሉ ይታወቃል፡፡ በዚሁ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ውድድር ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ተቀናቃኝ ሆነው ከሚቀርቡት አሰልጣኞች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ፈረንሳዊው ክርስትያን ጉርኩፍ ናቸው፡፡
በ2017 በጋቦን በሚስተናገደው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በሚደረገው ማጣርያ ምንም የምንዘናጋበት ሁኔታ የለም በማለት ባለፈው ሰሞን የተናገሩት ክርስትያን ጉርኩፍ፤ የምድብ 10 ትንቅንቅ በእኛ እና በኢትዮጵያ ይሆናልም ሲሉ ተናግረው፤ ግን ሲሸልስ እና ሌሶቶንም እንደማይናቁ አስገንዝበዋል፡፡ በማጣርያው ከሚያደርጓቸው ግጥሚያዎች ከኢትዮጵያ ጋር በአዲስ አበባ የሚያደርጉትን ከባድ ጨዋታ እንደሆነ በመጥቀስም ምንም አይነት ስህተት መፍጠር የለብንም ሲሉ ለቡድናቸው አባላት አሳስበዋል፡፡ የአልጄርያ ቡድን ለማጣርያው የሚያደርገውን ዝግጅት ከሁለት ሳምንት በኋላ ካምፕ በመግባት ይጀመራል፡፡በፈረንሳዊው የቡድኑ አሰልጣኝ ጉርኩፍ ስር ከ10 በላይ ባለሙያዎች አብረው እንደሚሰሩ መጥቀስ ለንፅፅር ይሆናል፡፡ አሰልጣኙ የአልጄርያን ቡድን በሃላፊነት የሚመሩት በስራቸው  ሁለት ምክትል አሰልጣኞች ከአልጄርያ ፤ አንድ ስራ አስኪያጅ ከአልጄርያ፤ ሁለት የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ከአልጄርያ እና ከፈረንሳይ፤ ሁለት የአካል ብቃት አሰልጣኞች ከፈረንሳይ እንዲሁም ሁለት ዶክተሮች ከአልጄርያ ተመድበውላቸው ነው፡፡
 በሌላ በኩል በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው ለኢትዮጵያው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ተቀናቃኝ ሆነው የሚቀርቡት የሲሸልስ እና የሌሶቶ አሰልጣኞች ሁለቱም በአገራቸው በምርጥ ተጨዋችነት ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡ የሲሸልስ እና የሌሶቶ ብሄራዊ ቡድኖች በእግር ኳስ ደረጃቸው ከኢትዮጵያ በታች በመሆናቸው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በሁለቱ ተቀናቃኞቻቸው ላይ ብልጫ ለመውሰድ የሚችሉበትን እድል ያመለክታል፡፡ የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩት ኡሊርች ማቲሆልት ይባላሉ፡፡ ኡልሪች በሲሸልስ  እግር ኳስ ብቸኛው ፕሮፈሽናል ተጨዋች በመሆን የሚጠቀሱ ባለታሪክ ሲሆኑ  በ1991 እና በ2008 እኤአ የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ከሰሩ በኋላ በ2014 ለሶስተኛ ጊዜ ሃላፊነቱን በመረከብ እየሰሩ ናቸው፡፡ ከዚያ በፊት በ2010 እኤአ የሲሸልስ እግር ኳስ ፌደሬሽን የእግር ኳስ ዲያሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በገቡበት የምድብ ማጣርያ ዙርያ ኡሊርች ማቲ ሆልት አስተያየት ሲሰጡ የምንመጥነው ሌሶቶን ነው ካሉ በኋላ፤ የኢትዮጵያ ቡድን እየጠነከረ የመጣ እና የሚበልጠን ነው ብለው አልጄርያ ግን ከአቅማችን በላይ ናት በማለት ተናግረዋል፡፡ በህንድ ውቅያኖስ አገራት ሻምፒዮና በነሐሴ የሚኖራቸው ተሳትፎንም ለማጣርያው ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረውም ገልፀዋል፡፡ የሌሶቶ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ደግሞ በ1970 እና 80ዎቹ ለብሄራዊ ቡድናቸው የተጫወቱት ሞቺኒ ማቴቴ ናቸው፡፡ የሌሶቶ የምንግዜም ምርጥ ተጨዋች የሚባሉት ሞቺኒ ሃላፊነቱን ዘንድሮ የተረከቡት አስቀድመው የነበሩት አውሮፓዊ አሰልጣኝ ከሃላፊነት ከተነሱ በኋላ በምትክነት ነው፡፡
በ2016 ሩዋንዳ ለምታዘጋጀው አራተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን ውድድር በሚደረግ የጥሎ ማለፍ ቅድመማጣርያ ለኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ተቀናቃኝ ሆኖ የሚቀርበውን የኬንያ ብሄራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩት ደግሞ የ53 ዓመቱ ስኮትላንዳዊ ቦቢ ዊልያምሰን   ናቸው፡፡ በተጨዋችነት ዘመን በተለያዩ የስኮትላንድ ክለቦች የተጫወቱት እና አሰልጣኝ ከሆኑ በኋላ ኪልሞርክ ከተባለ የስኮትላንድ ክለብ ጋር የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ያገኙት ቦቢ ዊልያምሰን፤ በአሰልጣኝነት ልምዳቸው የእንግሊዙን ክለብ ቼስተር ሲቲ፤ የኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን፤ የኬንያውን ክለብ ጎሮማሃያ በማሰልጠን ሰርተዋል፡፡ በ2013 እኤአ ላይ የኡጋንዳን ብሄራዊ ቡድንን በመያዝ በቻን ውድድር የተሳተፉት ቦቢ ኬንያ ባሏት ምርጥ ተጨዋቾች ከኢትዮጵያ ተሽላ ቅድመ ማጣርያውን በማለፍ ለቻን ውድድር ትበቃለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡

Read 4574 times