Saturday, 02 May 2015 12:45

“የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” ላይ የተደረገው ውይይት

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 የታሪክ አፃፃፉ ምን ይመስላል? ደራሲው ታሪኩ የተፈፀመበትን ዘመን የተረዳው እንዴት ነው? መረጃዎቹን ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከባህል… አንፃር እንዴት ነው የመዘነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ሚዛናዊነት መመዘን ይቻላል፡፡ ማነው መዛኙ ለሚለው ፀሐፊያንም አንባቢያንም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ታሪከ ፀሐፊ ፖለቲከኛ ሊሆን ይችላል። አንድን ታሪክ ሲጽፍ ምክንያታዊ መሆን ከቻለ ሚዛናዊ ታሪክ ፀሐፊ ነው ሊባል ይችላ

     ላለፉት 10 ዓመታት በየሁለት ሳምንቱ የመፃህፍት ላይ ውይይት ሲያካሂድ የቆየው ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ፤ በገጠመው ውስጣዊ ችግር ምክንያት የተለመደውን መድረክ ማዘጋጀት ካቋረጠ ስድስት ወራት ሆኖታል፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የጀርመን ባህል ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ እና እናት ማስታወቂያ ድርጅት በጋራ በመሆን በወር አንዴ የመፃሕፍት ላይ ውይይት እንደሚያካሂዱ የተገለፀ ሲሆን የመጀመሪያው ዝግጅትም ባለፈው እሁድ በወመዘክር አዳራሽ ተከናውኗል፡፡
ለውይይት የተመረጠው “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” በሚል ርዕስ በአምባሳደር ዘውዴ ረታ ተጽፎ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሦስት ጊዜ ለመታተም የበቃው መጽሐፍ ሲሆን፤ ለውይይት የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ አበባው አያሌው ነበሩ፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ከአገር ውጭ በመሆናቸው በዕለቱ ሊገኙ አልቻሉም፡፡
“የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ዘመን በአገሪቱ በርካታ ታሪኮች የተከናወኑበት በመሆኑ ልዩ ወቅት ነበር፡፡ ዘመናዊ ለውጥ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ተጀመረ የሚሉ አሉ፤ በተግባር የታየው ግን በአፄ ኃይለሥለሴ ጊዜ ነው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አወዛጋቢ ንጉሥ ነበሩ፡፡ የሚያደንቋቸው አሉ፡፡ በኋላ በአገሪቱ ለታየው ምስቅልቅል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለው የሚከሷቸውም አሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ብዙ የተፃፈ ቢሆንም ወደፊትም ብዙ የሚፃፍበት ይመስላል፡፡ አብዮተኞቹ ታሪክ ፀሐፊዎች አፄ ኃይለሥላሴን ሲያጠለሹ፤ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ውስጥ ያገለገሉ ታሪክ ፀሐፊዎች ያሞግሷቸዋል፡፡ ሦስተኛው ዓይነት ታሪክ ፀሐፊዎች የውጭ አገር ሰዎች ሲሆኑ የተደረገውን ሐቅ ከማስቀመጥ ውጭ ነገሩ ጥሩ ነው፣ መጥፎ ነው ብለው ትንታኔ ውስጥ አይገቡም፡፡ ከዚህ አንፃር እነዚህ ሚዛናዊ ሆነው ይታያሉ።”
በዚህ መልኩ ገለፃ የጀመሩት አቶ አበባው አያሌው፤ የአምባሳደር ዘውዴ ረታን መጽሐፍ የቃኙት በሰባት መመዘኛዎች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ደራሲው ለጉዳዩ ያላቸው ቅርበት ምን ይመስላል? የመረጃ ምንጫቸው ምን ነበር? መረጃዎቹስ በመጽሐፉ ውስጥ በምን ያህል ተንፀባርቀዋል? ሚዛናዊነቱ ምን ይመስላል? በመጽሐፉ የተገለፀው ዘመን ታሪክ ምን ያህል ሙሉ ሆኖ ቀርቧል? የታሪክ ሃተታውና የቋንቋ አጠቃቀሙ ምን ይመስላል? መጽሐፉ ምን አዲስ ነገር አሳወቀን?
እነዚህን ጥያቄዎች አንስተው ምላሽ በመስጠት ማብራራት የቀጠሉት የዩኒቨርሲቲው ምሁር፤ የአገርም ሆነ የግለሰቦች ታሪክ በአንድ ሰው ብቻ ተጽፎ እንደማያበቃ ጠቁመው በአፄ ኃይለሥላሴ ዙሪያ 56 ያህል መፃሕፍት መታተማቸውን ገልፀዋል፡፡
ደራሲው ለፃፉበት ርዕሰ ጉዳይ ቅርበት ነበራቸው፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰራተኛ፣ የቤተ መንግሥት ጋዜጠኛና በኋላም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ  ከመሆኑም ባሻገር በአምባሳደርነትም ተሹመው መስራታቸው የቃል፣ የሰነድና የፎቶግራፍ መረጃዎችን ለማግኘት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው አቶ አበባው ገልፀዋል፡፡
አምባሳደር ዘውዴ ረታ በአገር ውስጥና በውጭም መረጃዎችን ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ያገኙትን በጥንቃቄ ማስቀመጥ በመቻላቸው “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በሚገባ ተጠቅመበውበታል፡፡ በአገር ውስጥ ከጽሕፈት ሚኒስቴር ሰነዶችን በቀጥታ አግኝተዋል። በዘመኑ ታላላቅ ባለስልጣናት ከነበሩት መኮንን ሀብተወልድ፣ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ፣ ይልማ ደሬሳ ከመሳሰሉት ቤተሰቦችም ብዙ መረጃ ሳያኙ አልቀሩም ተብሏል፡፡
“የቃል መረጃም በብዛት ተጠቅመዋል፡፡ ይህ በጥንቃቄ መታየት ያለበት ነው፡፡ ምስክርነቱን የሰጠው ሰው ማነው? የፖለቲካ አመለካከቱ፣ ዕውቀቱ … መጠየቅና መጣራት አለበት። የቃል ምስክርነት እውነታነቱ ሌላ ማመሳከሪያ ካልተገኘለት ለዘመን ፍርድ ክፍት ተደርጎ የሚተው ነው” ያሉት አቶ አበባው፤ በተመሳሳይ በዚህ መልኩ ጥያቄ አስነስቶ እስካሁንም እያነጋገረ  ነው በማለት “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” የተሰኘውን መጽሐፍ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
የቃልና የሰነድ መረጃዎች በስፋት ጥቅም ላይ ውለውበታል የተባለው “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” መጽሐፍ፤ በማጣቀሻነት የተጠቀማቸው መፃሕፍት ቁጥር ትንሽ እንደሆኑና የመረጃ አገላለጽ ችግር እንደሚታይበት ተጠቁሟል፡፡ የመረጃ ምንጩ ሰውም ይሁን ሰነድ የት እንደሚገኝ መገለጽ አለበት። በመጽሐፉ ላይ አባሪ ማኖር ገጽ ያበዛል ተብሎ ከተፈራ መረጃዎች ከየትኛው ሰነድ እንደተወሰዱ በግርጌ ማስታወሻ ቢገለጽ ጥሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ደራሲው ያገኘውን ምንጭ አንባቢያንም እንዲደርሱበት ያግዛል ተብሏል፡፡ መጽሐፉ በርካታ ፎቶግራፎችን ቢይዝም “የኤርትራ ጉዳይ” ከሚለው መጽሐፋቸው ጋር ሲነፃፀር ይኸኛው መጽሐፍ የያዛቸው ፎቶግራፎች ቁጥራቸው ማነሱም ተገልጿል፡፡
“የታሪክ ጠላት ፖለቲካ ነው፡፡ ፖለቲካ ታሪክን ወደራሱ ፍላጎት ይዞት ይሄዳል፡፡ ከዚህ አንፃር አምባሳደር ዘውዴ ረታ በመጽሐፋቸው ምን ያህል ሚዛናዊ መሆን ችለዋል?” ያሉት ምሁሩ፤ ደራሲው በአንዳንድ ቦታ ኃይለሥላሴን ከብዙ ነገሮች ነፃ ሲያደርጓቸው ይታያል፡፡ የታሪክ ፀሐፊ አይበይንም። ፍርዱን ለአንባቢያን ነው መተው ያለበት፡፡ እንዲህም ሆኖ መጽሐፉ ባነሳው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በአገር ውስጥ የነበረውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሁኔታና ተጽዕኖንም እያመሳከረ ታሪኩን ሚዛናዊ ለማድረግ ሞክሯል ተብሏል፡፡
ከ1923-1948 ዓ.ም ያለውን ዘመን ማዕከል አድርጎ የተዘጋጀው የአምባሳደር ዘውዴ ረታ መጽሐፍ፤ የ25 ዓመታቱን ታሪክ በምን ያህል መጠን ሙሉ አድርጎ አቀረበ? ለሚለውም ጥያቄ የአምስቱ ዓመት የአርበኞች ተጋድሎ ታሪክ አለመፃፉ (ደራሲውም ይህንን በመጽሐፉ መግቢያ አንስተውታል)፤ አፄ ኃይሥላሴ በስደት በእንግሊዝ በነበሩበት ጊዜ አኗኗራቸው ምን ይመስል እንደነበር አለመገለፁ፤ ከድል በኋላ አርበኞች፣ ባንዳዎች፣ ስደተኞች፣ ምሁራን በውስጣቸው የነበረው ትግል ምን እንደነበር አለመብራራቱ፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አውሮፓውያን ለስደተኛ መንግሥታት ዕውቅና ሲሰጡ ኢትዮጵያ ዕድሉ ስለመነፈጓ በስፋት አለመፃፉ … የመሳሰሉት የመጽሐፉን ሙሉእነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል ብለዋል - አቶ አበባው፡፡
መጽሐፉ በታሪክ አተራረክና በቋንቋ አጠቃቀሙ የተሳካለት መሆኑን የመሰከሩት አቶ አበባው  መጽሐፉ ምን አዲስ ነገር አሳየን? ለሚለውም “ትኩረት ያልተሰጣቸው ጥቃቅን ነገሮችን አሳይቶናል፡፡ ማን ምን ብሎ ጠይቆ፤ ማን ምን ብሎ መለሰ የሚለውን ሁሉ እናይበታለን። የ1923ቱ ሕገ መንግሥት ሊፀድቅ በሂደት ላይ እያለ በዘመኑ ምሁራንና ባለስልጣናት መሐል የተደረገውን ሰፊ ክርክር አቅርቦልናል (የሞኝ ዘመን መጽሐፍ ሆኖ ነው እንጂ በህገ መንግሥቱ ዙሪያ የቀረበው ርዕስ ብቻ አንድ መጽሐፍ ይወጣው ነበር)፡፡ በሊግ ኦፍ ኔሽን የተደረገውን ክርክር በተመለከተ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ሰዎች ዘንድ ያለው አመለካከት ምን ይመስል እንደነበር በስፋት ገልጿል፡፡ ስለ መኮንን ሀብተወልድ፣ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ፣ ይልማ ደሬሳ ካሁን ቀደም የማናውቃቸውን አዳዲስ መረጃዎች ሰጥቶናል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ምን ያህል ውጤታማ (በባሩድ ሳይታጠኑ በንግግርና ውይይት በማሳመን) መሆናቸውን አይተንበታል፡፡ መጨረሻ ላይም የንጉሠ ነገሥቱ ምኞት፣ የምሁራኑ ፍላጎትና የባለሥልጣናቱ መሻት መለያየቱንና ሁሉም ብቻውን መቆሙን አመላክቶናል፡፡” ብለዋል፡፡
አቶ አበባው መጽሐፉን አስቃኝተው ከጨረሱ በኋላ ከተሰብሳቢዎች የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ አንዳንዴ በሚጽፉት ስሜታዊ ገለፃ ፀሐፊ ትዕዛዛትን ይመስላሉ፡፡ በዚህ ላይ የምትለን ነገር አለ? ደራሲው የታሪክ ሰው አይደሉም፤ አምባሳደር (ዲፕሎማት) ናቸው የሚሉ ክርክሮች አሉ፡፡ ማረፊያው የቱ ነው? ታሪክን ፖለቲካ ስለሚጎትተው ታሪክ ፀሐፊ ሚዛናዊ እንዲሆን እንዴት ይጠበቃል? ታሪክ ፀሐፊ ይመዘናል ከተባለ፤ መዛኙ ማነው? ታሪክ ፀሐፊው ላይ የቀረበው አድናቆትና ነቀፌታን ለመዳኘት ዲስፕሊኑ ከየት ነው የሚገኘው?
ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ የሰጡት አቶ አበባው አያሌው፤ “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” የተሰኘው መጽሐፍ የንጉሡ ታሪክ ላይ ትኩረት ቢያደርግም አምባሳደር ዘውዴ ረታ ጸሐፊ ትዕዛዝ አይደሉም ብለዋል፡፡ በተፈጥሮም የተገኘ ይሁን በልምድ አተራረክና አቀራረቡ ጥሩ የሆነ መጽሐፍ አቅርበውልናል፡፡ ታሪክን ማንም ይጽፈዋል። ፀሐፊዎቹም ህዝባዊና ሙያዊ ተብለው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ ተነባቢነት ያላቸው አብዛኞቹ የታሪክ መፃሕፍት የተፃፉት በጋዜጠኞች ነው፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስለሰሩ የታሪክ መጽሐፉ ለመፃፍ ችለዋል፡፡
“በታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ሚዛናዊነት መኖሩን የምናረጋግጠው ደራሲው ምን መረጃ አገኘ? መረጃውን እንዴት አቀረበው? አተረጓጎሙስ እንዴት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎችን በማንሳት፤ ጥያቄዎቹ የሚተነተኑበትን ሂደት ተከትሎ በመመርመር ነው። የታሪክ አፃፃፉ ምን ይመስላል? ደራሲው ታሪኩ የተፈፀመበትን ዘመን የተረዳው እንዴት ነው? መረጃዎቹን ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከባህል… አንፃር እንዴት ነው የመዘነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ሚዛናዊነት መመዘን ይቻላል፡፡ ማነው መዛኙ ለሚለው ፀሐፊያንም አንባቢያንም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ታሪከ ፀሐፊ ፖለቲከኛ ሊሆን ይችላል። አንድን ታሪክ ሲጽፍ ምክንያታዊ መሆን ከቻለ ሚዛናዊ ታሪክ ፀሐፊ ነው ሊባል ይችላል” በማለት አቶ አበባው ማብራሪያቸውን ቋጭተዋል፡፡      

Read 3626 times