Sunday, 10 May 2015 14:14

የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ግጭቶችን የመከላከልና የመፍታት ሥራ እያከናወንኩ ነው አለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

አዲስ የፀረ - አክራሪነት ንቅናቄ ተጀምሯል ብሏል
የሃይማኖት ተቋማት ለአክራሪነት ሃይማኖታዊ ይሁንታ እንዳይሰጡ አሳስቧል

   በክልሎች መካከል ግጭቶች እንዳይከሰቱ በመከላከልና በዘላቂነት በመፍታት ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ያስታወቀው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፤ ግጭቶች ወደ ብጥብጥ ሳያመሩ ባሉበት እንዲመክኑ እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የስምንት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ይፋ እንዳደረገው፤ በዘንድሮ የበጀት ዓመት ለግጭት ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው
በተመረጡ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በኦሮሚያና ሶማሌ፣ በአፋርና ሶማሌ እንዲሁም በአፋርና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሣኝ አካባቢዎች ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ ዕለታዊ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን በመሰብሰብና በመተንተን ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርስና በየደረጃው ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግም ግጭቶች ወደ ብጥብጥ ሳያመሩ ባሉበት እንዲመክኑ እያደረገ መሆኑን በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡ የተዳፈኑ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በአፋርና የሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ማለትም ገዳማይቱ፣ እንድፎ እና አዳይቱ ቀበሌዎችና በአጎራባች ህዝቦች መካከል ለረዥም ዘመናት የቆየውን አለመግባባትና ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም ጠቁሟል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች አስተዳደራዊ ወሰን የማካለል ተግባር ከፌደራል መንግስትና ከሁለቱ ክልሎች በተውጣጡ አካላይ ኮሚቴዎች መከናወኑም ተገልጿል፡፡ ባለፉት ስምንት ወራት በ18 ዩኒቨርሲቲዎች የሰላም ፎረሞችን የማቋቋምና የማጠናከር ስራ ማከናወኑን የጠቆመው የሚኒስቴር መ/ቤቱ ሪፖርት፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የሰላም ፎረሙ በተቋቋመባቸው አስራ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ግምገማ ማካሄዱንም ገልጿል፡፡ በ2007 በጀት ዓመት አዲስ የፀረ አክራሪነት ንቅናቄ መጀመሩን የገለፀው ሪፖርቱ፤ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በጋምቤላ፣ በሀረሪ ክልሎችና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የማህበረሰብ ተኮር የፀረ አክራሪነት ትግል ንቅናቄ መፍጠሩንና በህብረተሰቡ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ብዥታ ለማጥራት ጥረት መደረጉን ጠቁሟል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት አክራሪነትና ፅንፈኝነት በአስተምህሮዎቻቸው
ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ መሆኑን መነሻ በማድረግ ለአክራሪዎቹ ሃይማኖታዊ ይሁንታ እንዳይሰጧቸው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡

Read 2339 times