Sunday, 10 May 2015 14:22

ሠማያዊ ፓርቲ በመስቀል አደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ተከለከልኩ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

ምርጫ ቦርድ መብቱን እንዲያስከብርለት ጠይቋል
    ሠማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ማጠቃለያና የድጋፍ ህዝባዊ ስብሰባ በመስቀል አደባባይ ለማድረግ ያቀረበው የእውቅና ጥያቄ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቀባይነት ማጣቱን  አስታወቀ፡፡ ምርጫ ቦርድ መብቱን እንዲያስከብርለት በደብዳቤ መጠየቁን አስታውቋል፡፡የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ሠልፉ ሊከናወን የታሰበው በመጪው እሁድ ግንቦት 9 ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት በመስቀል አደባባይ ቢሆንም የከተማ አስተዳደሩ ቦታው ሠፊ የህዝብ እንቅስቃሴና የትራፊክ መጨናነቅ ያለበት ስለሆነ ፓርቲው የቦታና የጊዜ ለውጥ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የከንቲባ ጽ/ቤት ለፓርቲው በደብዳቤ በሰጠው ምላሽ ሰማያዊ ሚያዚያ 21 ቀን 2007 ዓ.ም ለአስተዳደሩ ምርጫውን ምክንያት በማድረግ በመስቀል አደባባይ ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ 9 ሰአት ድረስ የሚቆይ ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ጥያቄ ማቅረቡን ጠቅሶ፤ አደባባዩ የትራፊክ መጨናነቅ ያለበትና የከተማው ነዋሪ መተላለፊያ በመሆኑ እውቅና ለመስጠት እንደሚቸገር  ጠቁሞ ፓርቲው በሌላ ቦታና ቀን ጥያቄውን ቢያቀርብ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ  ዝግጁ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በቅርቡ መንግስት የጠራው ሠልፍ በመስቀል አደባባዩ መካሄዱን ጠቅሰው ቦታውን አስመልክቶ የቀረበው ምላሽ አሳማኝ አይደለም ብለዋል፡፡ ፓርቲው አስተዳደሩ ያቀረበው ምክንያት አሣማኝ አለመሆኑን በዝርዝር ጠቅሶ  ከትላንት በስቲያ በድጋሚ ደብዳቤ ማስገባቱን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን የህዝብ ድጋፍ የማሰባሰብና የአደባባይ ቅስቀሳ የማድረግ መብቱን እንዲያስከብርለት የሚጠይቅ ደብዳቤም ለቦርዱ ማስገባታቸውን አቶ ዮናታን ገልፀዋል፡፡

Read 3412 times