Sunday, 10 May 2015 14:22

ከሊቢያ የተለቀቁ 27 ስደተኞች ትናንት አዲስ አበባ ገቡ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ጠ/ሚ ኃይለማርያም የግብጽን መንግስት አመስግነዋል
   በሊቢያ ታግተው የቆዩና የግብጽ መንግስት ባደረገው ድጋፍ የተለቀቁ 27 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ትናንት ማለዳ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምና ሌሎች ባለስልጣናት በቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በመገኘት ለስደተኞቹ አቀባበል አድርገዋል፡፡በግብጽ ወታደራዊ ሃይል ድጋፍ ከእገታ ተለቀዋል የተባሉት እነዚሁ ስደተኞች ከትናንት በስቲያ ካይሮ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ሲደርሱ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ አቀባበል እንደተደረገላቸው  ሮይተርስ፣ ፕሬዚደንቱ፤ “ስደተኞቹ በሊቢያ የታጠቁ ሃይሎች ታግተው በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ የቆዩ ናቸው” ማለታቸውን የአገሪቱ የዜና ተቋም “ሜና መዘገቡ ታውቋል፡፡የዜና ተቋሙ ስለስደተኞቹ ማንነት፣ ስለተለቀቁበት ሁኔታ እና ታግተው በቆዩበት ወቅት ስለነበረው ሁኔታ ግልጽ መረጃ ባይሰጥም፣ ሮይተርስ በበኩሉ፤ የሊቢያ ባለስልጣናት ከግብጽ የስለላ ተቋማት ያገኙትን መረጃ በመጠቀም በዴርና እና ሚስራታ ከተሞች በታጠቁ ሃይሎች ታግተው የነበሩትን እነዚህን ስደተኞች እንዳስለቀቁ መረጃ ደርሶኛል ብሏል፡፡ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ
አንድ የግብፅ ዲፕሎማት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያኑ ከሊቢያ የወጡት በወታደራዊ ሃይል ድጋፍ ሳይሆን የግብፅ መንግስት ባደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ከኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች አንዱ በበኩሉ፣ የሊቢያ መንግስት ከነበርንበት ቦታ ወደ አገሪቱ የጸረ ህገወጥ ስደት አካል ከወሰደን በኋላ፣ የግብጽ መንግስት ወደ ካይሮ አምጥቶናል ሲል መናገሩን ዘገባው አስረድቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ የስደተኞቹን መለቀቅ ተከትሎ ከትናንት በስቲያ ከግብጹ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ጋር በስልክ ባደረጉት ንግግር፣ ግብጽ ኢትዮጵያውያኑን ለማስለቀቅ ላደረገችው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ገልጸው፤ መሰል ጥረቶች በግብጽ፣ በአረቡ አለምና በአፍሪካ አገራት መረጋጋትን ለመፍጠር አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ማለታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባወጡት መረጃ እንዳሉት፤ በሊቢያ ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል የመጀመሪያዎቹ 11 ስደተኞች ባለፈው ረቡዕ በካርቱም በኩል ወደ አዲስ አበባ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡

Read 4572 times