Sunday, 10 May 2015 15:18

“የወንድምህን ስም ራስህ እወቅ እንጂ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንትና… በቀደም ቲቪ ላይ ‘ትገኝበታለህ’ ብዬ ያልጠበኩህ ቦታ አየሁህሳ! የጨዋታው ህግ እንዲህ ሆኗል እንዴ! ሁለትና ከሁለት በላይ ወገኖችን ‘አታጣርስ’ እንጂ! ቂ…ቂ...ቂ… በነገራችን ላይ ምን መሰላችሁ… ዘንድሮ ነገርዬው በ‘ሁለት ባላ’ ብቻ መንጠልጠል ሳይሆን በሀያ ሁለት ባላ መንጠላጠል ሆኗል፡፡ ልጄ ሰዉ ሁሉ የጨዋታውን ህግ አውቆበታል፡፡
የምር ግን ቲቪ እኮ አንዳንዴ አሪፍ ነው፡፡ ልክ ነዋ…ቢራ ላይ የቼ ጉቬራና የማልኮም ኤክስን ንግግሮች የሚያስንቅ ዲስኩር እያደረጉላችሁ ‘ተናግረው ካናገሯችሁ’ በኋላ፣ እዛኛው ‘የኮኑነት ቤት’ ውስጥ ስታዩዋቸው… አለ አይደል… ባለፉት ሦስት ወራት ‘ከአፋችሁ ያመለጣችሁን’ ሁሉ መለስ ብላችሁ ታሰላስላላችሁ፡፡ ሦስት ወር ያልኩትማ… ከሦስት ወር በኋላ ‘ይርጋ’ ሊኖር ይችላል ብዬ ነው። (ቂ...ቂ…ቂ…) እናማ…ቀን፣ ቀን ከእኛ ጋር ‘ብላክ ጠላ’ ማታ፣ ማታ ከሌሎቹ ጋር ‘ብላክ ሌብል’… አሪፍ ብልጠት አይደለም፡፡ በቲቪ ብልጭ ያልክብን ወዳጃችን ሆይ፣ ማሳሰቢያ አለን…ከዛሬ ጀምሮ ከእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር ትንፍሽ እንዳንል በነፍስ አባቶቻችን ግዝት እንደተጣለብን እወቅልንማ! ፈረንጅ… ‘ሴቲንግ ዘ ሬከርድ ስትሬት’ የሚለው ይህን አይደል!
እኔ የምለው... እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ሚዲያ ውስጥ ያለን ሰዎች ነገሮችን በደንብ ማየት ያለብን ጊዜ ላይ የደረስን አይመስላችሁም!
ይቺን ስሙኝማ…እንደ ፌዝም የሚያደርጋት ነገር ነች፡፡ የሆነ ጋዜጣ ያልሞተውን ሰውዬ መሞቱንና ግብአተ መሬቱ መፈጸሙንም ይጽፋል፡፡ ሰውየው በማግስቱ እዝግጅት ክፍሉ ይሄድና “ሳልሞት ሞቶ ተቀበረ ብላችኋልና ያለመሞቴን ገልጻችሁ ማረሚያ አውጡልኝ…” ይላል፡፡ አዘጋጁም ምን ይላል… “በፖሊሲያችን መሠረት አንዴ የወጣ ዜና ቢሳሳትም ማረሚያ አናወጣም…” ይላል፡፡ ሰውየውም “እንደዛ ከሆነማ ወደ ህግ እሄዳለሁ…” ሲል አዘጋጁ ምን ‘አስታራቂ ሀሳብ’ አመጣ መሰላችሁ… “ባይሆን ዳግም እንደተወለድክ አድርገን የልደት ዜናዎች ዓምድ ላይ እናወጣልሀለን…” ብሎት አረፈላችሁ፡፡
እናማ… ዘንድሮ ብዙ ማረሚያ የሚያስፈልጋቸው ስህተቶች እየተሠሩ እንደዋዛ እየታለፉ ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…አንድ የሆነ አገር ውስጥ የሆነ ፖለቲከኛ የምርጫ ንግግር ሲያደርግ ምን አለ መሰላችሁ… “ተወዳዳሪያችን ፓርቲ አሥር ዓመት ሙሉ ስልጣን ላይ በቆየበት ዘመን አገሪቱን ሙልጭ አድርጎ በልቷታል፡፡ እስቲ አሁን ደግሞ ለእኛ ዕድሉን ስጡን…” ብሎ የምርጫ ቅስቀሳ አደረገ አሉ!
አሁን ለዚህ አርእስት አውጡ ብንባል…
‘የእንትን ፓርቲ እጩ አገሪቱን ሙልጭ አድርጎ ለመብላት ዕድል እንዲሰጣቸው መራጮችን ተማጸኑ…’
‘የእንትን ፓርቲ እጩ ከተመልካችነት ወደ ተጠቃሚነት ለመሸጋገር ህዝቡ ድምጽ በመስጠት እንዲተባበራቸው ጠየቁ…’
‘አገሪቱን ሙልጭ የማድረግ ዕድል ለሌሎቹም መዳረስ እንዳለበት የእንትን ፓርቲ እጩ ድምጽ ሰጪዎችን አሳሰቡ…”
ሰውየውን ወይንም ፓርቲያቸውን ጥምድ እድርጎ የያዘ አዘጋጅ ቢኖር ደግሞ… አለ አይደል… ሰውየው በስሜት እንዳሉ ፎቶ በትልቁ ያወጣና ርእሱን ደግሞ ምን ይለው መሰላችሁ… ‘አገሪቱ ካዝና ላይ የተጋረጠ አደጋ!’ ቂ…ቂ…ቂ…
እንዲህ አይነት የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርግ ‘ተወዳዳሪ’ ከገጠማችሁ ርዕስ በማውጣት ለመተባበር ፈቃደኞች መሆናችን ይታወቅልንማ! ወይ “ዕድል ስጡን…” ብሎ ነገር! ዕድል ከፈለገ ሎተሪ ይቁረጥ እንጂ ቦተሊካ ውስጥ ምን ጥልቅ ያደርገዋል!
ስሙኝማ…‘ቦተሊካ’ ውስጥ ዘው ካልን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…በዛ ሰሞን እንግሊዞቹ ቱባ፣ ቱባ ቦተሊከኞች ሰፊው ህዝብ ዘንድ ቀርበው በጥያቄ ሲፋጠጡ ቢቢሲ ላይ ላይቭ ሲያሳዩን ምን አልኩ መሰላችሁ… “ከዕለታት አንድ ቀን…” አልኩ፡፡ ልክ ነዋ… እንዲሁ ዝም ብሎ መራቀቅ አይደለማ…እኛ ሰፊ ህዝቦቹ ዘንድ ፊት ለፊት ቀርቦ ለጥያቄዎቻችን መልስ መስጠት ነዋ!       የምር… ቦተሊከኞች እኛ ፊት ቀርበው በጥያቄ ስናፋጥጣቸው ታየኝና “አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ያዢ...” ብዬ ተረትኩ፡፡
በአንድ ወቅት አንድ አለቃችን አንድ ስብሰባ ላይ ያሏት ነገር ትዝ ትለኛለች፡፡ ጋዜጠኛው የሆነ ሰልፍ ላይ አንዱን ተሰላፊ ይጠጋና… “የወንድሜን ስም ማን ልበል?” ይለዋል፡፡ ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው… “የወንድምህን ስም ራስህ እወቅ እንጂ እኔ የት አውቅልሀለሁ…” ‘አንጀት የሚያርስ’ መልስ አይደል!
እናማ… “የወንድምህን ስም ራስህ እወቅ እንጂ…” የምንባል ብዙ ነን፡፡
በሁሉም ሚዲያ ላይ ውስጥ ሊታረሙ የሚችሉ ብዙ ስህተቶች እየተሠሩ ነው፡፡
ኮሚኩ ነገር እኮ አሁን መሸወድ የማይቻልበት ዘመን እንደሆነ ነገሬ አለማለታችን ነው፡፡ በቂ የመመገቢያ ሳህን የሌለን ሁሉ ‘ሳተላይት ዲሽ’ የገጠምንበት ዘመን ነው፡፡ እናማ…ተደብቆ የሚቆይ ነገር የለም፡፡ ሃሎ…ይሰማል!
ስሙኝማ…ይቺን ካወራናትም እንድገማትማ። ‘ባለፈው ዘመን’ ነው፡. እናላችሁ…ወታደሩ ጦር ሜዳ ይቆስልና ሁለት እግሮቹን አጥቶ ሆስፒታል ይተኛል፡፡ ታዲያላችሁ…አንዱ ጋዜጠኛ ሲጠይቀው ምን ይለዋል… “ሁለት እግሮችህን በማጣትህ ምን ይሰማሀል?” አይነት ጥያቄ ይጠይቀዋል፡፡ ይሄ ነገር በሰሙት አካባቢ የሆነ ማጉረምረም ነገር ፈጥሮ ነበር። ሁለት እግር የማጣትን ያህል ጉዳት የደረሰበትን ሰው እንደዛ አይነት ጥያቄ መጠየቁ የምርም የሚዘገንን ነበር፡፡ ነገርዬውማ ምን መሰላችሁ…ጋዜጠኛው አስቀድሞ ‘እሱ የሚፈልገውን አይነት መልስ’ እንዲሰጠው አድርጎ መጠየቁ ነው፡፡ አለ አይደል… “ደስታ ነው የሚሰማኝ፡፡ ደግሞ ለአገሬ… አይደለም እግሮቼን ህይወቴን ብሰጥስ!” ምናምን እንዲለው ነበር፡፡
ዘንድሮም… አለ አይደል… በሁሉም ወገን እኛ የምንፈልገው መልስ እንዲሰጠን አመቻችተን የምንጠይቅ መአት ነን፡፡ ብዙ ‘ተጠያቂዎችም’…አለ አይደል…የሚፈልግባቸውን ስለሚያውቁት የእኛን የጠያቂዎቹን ‘አንጀት የሚያርስ መልስ’ ይሰጣሉ። ግንላችሁ… ዋናውን ነገር ብቻ እንሰማና እንደነገሩ ጣል የሚደረጉ ነገሮች ያልፉናል፡፡
“እንደሚያውቁት በአሁኑ ጊዜ የሠራተኞች መብት እየተጠበቀ ነው፡፡ አሠሪዎች እንደፈለጋቸው ሠራተኛን የሚበድሉበት ዘመን አልፏል፡፡ እርሶ ምን ይላሉ?”
“ተመስገን ነው እንጂ ሌላ ምን እላለሁ፡፡ ለመንግሥት ምስጋና ይግባውና አሁን መብታችን ተጠብቋል፡፡”
“አሁን እርሶ ምን ሥራ ላይ ነዎት?”
“ሥራ ላይ አይደለሁም
“ለምን
“ከነበርኩበት መሥሪያ ቤት አለአግባብ ተቀንሼ…”
ቂ…ቂ…ቂ…
“እማማ፣ ምን እያደረጉ ነው?”
“ለበዓል ዶሮ እየሸመትኩ…”
“እንደሚያውቁት በአሁኑ ጊዜ ዋጋ ለማረጋጋት በሚመለከታቸው ክፍሎች ከፍተኛ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ በዚህም ለውጦች እየተመዘገቡ ነው፡፡ እማማ እርሶ ምን ይሰማዎታል?”
“ደስታ..ደስታ ነው የሚሰማኝ፡፡ ሌላ ምን ይሰማኛል፡ እሰዬው ነው፡፡”
“ለመሆኑ ዘንድሮ የዶሮ ዋጋ እንዴት ነው?”
“ሰማይ… ሰማይ ነው፡፡ እንደው ነጋዴውን ሀይ የሚለው ይጥፋ! ለበዓል ቤቱ ጭር እንዳይል ነው እንጂ፣ ባይገዛስ ቢቀር…”
ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…የምር ግን ሚዲያ ውስጥ ያለን አንዳንዶቻችን ምን ችግር ያለብን ይመስለኛል…አለ አይደል… ሰዉ የማያውቅ ይመስለናል፡፡ በቃ ሚዲያው በእጃችን ስለሆነ፣ ነገሮችን ለእኛ በሚመቸን መንገድ ብቻ ማቅረብ ስለምንችል… ድፍን አገር… “በእናንተ መጀን…” የሚል ይመስለናል። ሰዋችን ግን ያውቃል…በጣም ያውቃል፡፡ አይደለም ስለ አገር ጉዳይ ስለ ሶሪያ ጦርነት የእኛን መቶ እጅ የሚያስከነዳ ትንታኔ መስጠት የሚችል ሰው መአት መሆኑን ማወቅ ሸጋ ነው፡፡
እናማ…መቅደም እንኳን ባንችል ቢያንስ ከሰዉ ኋላ እንዳንቀር መሞከሩ አሪፍ ነው፡፡ እግረ መንገዴን…የስፖርቱ ነገርማ ግርም ይላል፡፡ ‘ከት ኤንድ ፔስት’ ሆኖ እንኳን… “ኧረ መቀሱ ይስተካከል!” እያልን ነው፡፡ የሚገጥሙን የትርጉም ስህተቶች… አለ አይደል…አይመቹም፡፡ ዲ.ኤስ.ቲቪ ቀን ማታ እየታየና እዛ ላይ መቶ ጊዜ ሲባሉ እየተሰማ እንኳን…‘ዋይኔ ሩኒ’ የሚባል ተጫዋች የለም ‘ዌይን ሩኒ’ ነው ሲባል መስማት አቅቶናል፣ ‘ሁል ሲቲ’ የሚባል ቡድን የለም፣ ‘ኸል ሲቲ’ ነው ስንባል መስማት አቅቶናል፡፡
እናማ… ቢያንስ ሰዉን መቅደም ቢያቅተን እንኳን ወደኋላ ላለመቅረት እንሞክርማ!
“የወንድምህን ስም ራስሀ እወቅ እንጂ…” ከመባል ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2958 times