Monday, 11 May 2015 09:12

“ኢንፌክሽን...እስከሞት ሊያደርስም ይችላል...”

Written by 
Rate this item
(24 votes)

የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ በአለማችን ላይ እድሜያቸው ከ15-49 የሆነ 340/ ሚሊዮን
ሰዎች በመራቢያ አካላት ኢንፌክሽን እንዲሁም በተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች እንደሚያዙ ቁሟል። ይህ የመራቢያ አካላት ኢንፌክሽን እንደኛ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ትልቁን ቁጥር የሚሸፍን የስነተዋልዶ ጤና ችግር እንደሆነም በተለያየ ግዜ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡የመራቢያ አካላት ልክ እንደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎቻችን ሁሉ በተለያየ ግዜ እና አጋጣሚ ተለያዩ በሽታዎች ሊጠቁ ይችላሉ፡፡ በተለያየ ምክንያት የሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖች ወይም በህክምናው ሳይንስ RTIs (Reproductive tract infections)  ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ዛሬው ፅሁፋችን በእነዚህ በመራቢያ አካላት ላይ በሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች እንዲሁም የአባላዘር ሽታዎች ዙሪያ ባለሙያ አነጋግረን ያገኘነውን ምላሽ እንዲህ ልናስነብባችሁ ወደናል፡- ለዛሬ ያነጋገርናቸው ባለሙያ ዶክተር መብራቱ ጀንበር ይባላሉ፡፡ ዶክተር መብራቱ በብራስ የእናቶች እና ህፃናት ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ሀኪም ናቸው። የምናወራው በመራቢያ አካላት ላይ
በሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች ዙሪያ ነውና በአጠቃላይ የስነተዋልዶ አካላት ስንል የትኛውን የሰውነት ክፍል የሚያጠቃልል ነው? ብለን በቅድሚያ ላነሳንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡
“...የስነተዋዶ አካል ስንል በሴት በኩል የሴት ብልትን እና የማህፀን ክፍሎችን ባጠቃላይ እንዲሁም ልጅ  ከተወለደ በኋላ ወተት በማመንጨት የሚያገለግሎ ጡቶችንም ይጨምራል፡፡ በወንድ በኩል ደግሞ የወንድ ልጅ ብልት አለ የዘርፍሬዎች እንዲሁም ሌሎች ሆርሞን በማመንጨት የሚያገለግሉ እጢዎች አሉ፡፡ እነዚህ በሙሉ ከስነተዋልዶ ጋር  ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት ያላቸው የሰውነታችን ክፍሎች ናቸው፡፡” የስነተዋልዶ አካላትን የሚያጠቁ ኢንፌክሽኖች በብዛትም ሆነ በአይነት እጅግ በርካታ ሲሆኑ በእነዚህ የሰውነት ክፍሎች ላይ በሚፈጠር ባክቴሪያ መንስኤነት የሚከሰቱ እና በግብረስጋ ግንኙት አማካኝነት የሚተላለፉ የአባላዘር በሽታዎች በሚል በሁለት እንደሚከፈሉ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ “...የስነተዋልዶ አካላትን የሚያጠቁ የኢንፌክሽን አይነቶች በጣም ብዙ ናቸው ነገር ግን በዋናነት በሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ አንደኛው በጥገኛ ህዋስ ወይም ባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በግብረስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ የበሽታ አይነቶች ወይንም sexually  transmitted infections ተብለው የሚጠሩት ናቸው፡፡”ምንም እንኳን ሁሉም አይነት ኢንፌክሽኖች የተለያየ የጤና ችግር የሚያስከትሉ ቢሆንም ትልቁ ትኩረት መሰጠት ያለበት በግብረስጋ ግንኙት አማካኝነት ሊተላለፉ የሚችሉት የበሽታ አይነቶች ላይ ነው ይላሉ ዶክተር መብራቱ፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የሚያነሱት እነዚህኞቹ የኢንፌክሽን አይነቶች ብዙውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያጠቁ እና በግብረስጋ ግንኙነት አማካኝነት ተላላፊ መሆናቸውን ነው፡፡ ስለዚህም ይላሉ ዶክተር፡-
“..ስለዚህ sexually transmitted infections  ወይንም በግብረስጋ ግንኙነት አማካኝነት ሊተላለፉ የሚችሉ የበሽታ አይነቶች የትኞቹ ናቸው? እንዴትስ መከላከል ይቻላል? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እና በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡”አንዳንዶቹ የኢንፌክሽን አይነቶች ከማህፀን ውጨኛው ክፍል አንስቶ በተለያዩ የማህፀን ክፍሎች ላይ ሊዛመቱ የሚችሉ ሲሆን በማህፀን ውጫዊ ክፍል ላይ ብቻ ተከስተው በህክምና ክትትል ወዲያው ሊጠፉ የሚችሉም አሉ፡፡  “...vulval area ወይንም ደግሞ የብልት የውጨኛውን ክፍል ሊያጠቁ የሚችሉ ወይም ቆዳው ላይ ብቻ የሚወጡ አንዳንድ ኢንፌክሽኖች አሉ፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ የውጪውን አካል ከሚያጠቁ ኢንፌክሽኖች መካከል የውስጠኛውን ክፍልም ሊያጠቁ የሚችሉ ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ ፈንገስ የምንለው የውጪውን ክፍል ከማሳከኩ እና ከማቅላቱ በተጨማሪ የውስጠኛው ክፍል ላይም ከፍተኛ የሆነ የማሳከክ ስሜት ያመጣል፡፡ በተጨማሪም ነጭ የሆነ አይብ የመሰለ ፍርፍር የሚል አይነት ፈሳሽ ይኖረዋል፡፡ ይህ በብዛት የሚከሰት የፓራሳይት አይነት ሲሆን በተለይ በእርግዝና ሰአት በጣም ይበዛል፡፡     በተቃራኒው ደግሞ በውስጠኛው የማህፀን ክፍል ላይ የሚከሰቱ የኢንፌክሽን አይነቶችም  አሉ፡፡ ለምሳሌ የግብረ ስጋ ግንኙነት በመልካም ሁኔታ እንዲካሄድ ሊያደርጉ የሚችሉ እርጥበት የሚያወጡ እጢዎች መውጫ በር ላይ የሚፈጠሩ የኢንፌክሽን አይነቶች አሉ። በዚህም ምክንያት የፈሳሽ መውጫ ቀዳዳው ይጠባል ወይም ይዘጋል፡፡ ይህም በብልት አካባቢ እብጠት ለሚያመጣው Bartholin’s cyst ወይም Bartholinitis  ለሚባለው ኢንፌክሽን መፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡”ሌሎች በቫይረስ አማካኝነት  የሚተላለፉ የኢንፌክሽን አይነቶችን ሲያብራሩም፡-  “ሌሎች ልክ እንደ chancroid, wart  ወይም ደግሞ papillomavirus  ወይም ኪንታሮት በመባል የሚጠራው አይነት  በቫይረስ አማካኝነት የሚተላለፉ  ኢንፌክሽኖች አሉ፡፡ እንዲሁም ደግሞ Herpes zoster  ወይም ደግሞ Herpes simplex የሚባል አለ፡፡ ይህም በቫይረስ የሚተላለፍ ሲሆን የብልት ውጨኛውን አካባቢ ያቆስላል፡፡” በባክቴሪያ አማካኝነት ከሚከሰቱት ይልቅ በግብረስጋ ግንኙነት አማካኛነት የሚመጡት ኢንፌክሽኖች  በይበልጥ ወንዶችን ያጠቃሉ ይላሉ ዶክተር መብራቱ፡፡
“...በወንዶች ላይ ባክቴሪያል ኢንፌክሽን የተለመደ አይደለም፡፡ ነገር ግን ወንዶች በግብረስጋ አማካኝነት በሚተላለፉ የኢንፌክሽን አይነቶች በብዛት ሲጠቁ ይስተዋላል፡፡ በተለይ Gonorrhea እና syphilis,  የምንላቸው የአባላዘር በሽታዎች ዋነኞቹ ናቸው። በተጨማሪም ከርክር ወይም chancroid, wart  እንዲሁም ደግሞ papillomavirus     የምንላቸውም ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡”በፈረንጆቹ 2008 በናይጄሪያ የተደረገ አንድ ጥናት የግብረ ስጋ ግንኙነት እንዲሁም ደካማ የሆነ የንፅህና አጠባበቅ 44.6% የሚሆነውን የበሽታው መተላለፊያ መንገድ እንደሚይዝ ጠቁሟል፡፡“...መተላለፊያ መንገዱ አብዛኛውን ግዜ የሰውነት አቅም መድከም ነው፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ የጣፋጭ ይዘት ያላቸው ምግቦች ወይም መጠጦች ማዘውተር እና አብዝቶ መጠቀም በሽታው የሚኖረውን ተጋላጭነት ሊጨምር ይችላል፡፡ እንዲሁም አዘውትረው ብልታቸውን የሚታጠቡ ሴቶች ይህ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። የብልት ተፈጥሯዊ እርጥበት ታጥቦ መወገድ የለበትም
ምክንያቱም ብልት የእራሱ የሆነ በሽታ ተከላካይ ፈሳሽ አለው፡፡ ይህ መከላከያ ደግሞ አላስፈላጊ
ፓራሳይቶችን ያጠፋል፡፡ ስለዚህ የብልት አካባቢ ቢያንስ በቀን ሁለት ግዜ ጠዋትና ማታ ከታጠበ በቂ ነው፡፡ ሌሎቹ የኢንፌክሽን አይነቶች ደግሞ ቀደም ሲል እንደ ገለፅኩት በግብረስጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚተላለፉ     ናቸው፡፡ ለዚህም እንደ Gonorrhea, syphilis, Trichomoniasis እንዲሁም papillomavirus የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላ፡፡” አብዛኞቹ በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጡት ኢንፌክሽኖች ከግል ንፅህና ጉድለት ወይም ተገቢውን የንፅህና አጠባበቅ ባለመከተል የሚከሰቱ መሆናቸውንም ጨምረው ይገልፃሉ፡-
“ከሰገራ ጋር የሚወጡ በጣም አጥቂ የሆኑ ህዋሳቶች አሉ በጣም በብዛት የሚገኘው Escherichia coli  ወይም E. coli  የምንለው  የባክቴሪያ አይነት ነው፡፡ ይህ ባክቴሪያ በማህፀን አካባቢ ሲገኝ የማህፀን ኢንፌክሽን እንዲሁም የሽንት መተላለፊያ ቱቦ ኢንፌክሽኖችን ያመጣል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን የግል ንፅህና አጠባበቅ ስልቱን ማወቅ ያስፈልጋል ወይም ደግሞ የጤና ባለሙያ ጋር በመሄድ እንዴት ባደርግ ነው እነዚህን ኢንፌክሽኖች መከላከል የምችለው የሚለውን በተመለከተ የምክር አገልግሎት መቀበሉ በጣም ጥሩ ይሆናል፡፡” የዚህ አይነት የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ተገቢው ህክምና ካልተደረገላቸው ለመሀንነት፣ ከመሀፀን ውጪ ለሚፈጠር እርግዝና ብሎም ለኤች አይቪ ቫይረስ የማጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ችግሩ እየተባባሰ ከሄደም ለሞት መዳረጋቸው አይቀሬ ነው ብለዋል ዶ/ር መብራቱ ጀምበር፡፡ “...እነዚህ ኢንፌክሽኖች እስከ ሞት ደረጃም ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ኢንፌክሽኑ ሀይለኛ እየሆነ በሄደ ቁጥር ወደ ሌሎች የሰውነታችን ክፍሎች መዛመቱ አይቀርም፡፡ ሌላው ያልጠቀስነው ደግሞ ኤችአይቪም ነው፡፡ ኤች አይቪም እንደዚሁ በግብረስጋ ግንኙነት ነው።  ምንም እንኳን የግብረስጋ ግንኙነት ብቻ የመተላለፊያ መንገዱ ባይሆንም በግብረስጋ ግንኙነት የመተላለፍ ሀይሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ እየጠና ሲሄድ     ህክምና በወቅቱ ካልተገኘ የመሞት አጋጣሚም ይኖራል።”

Read 30337 times