Saturday, 16 May 2015 10:07

ሕብረት ባንክ ባለ 32 ፎቅ የዋና መ/ቤት ህንፃ ሊያስገነባ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ሕብረት ባንክ ባለ32 ፎቅ የዋና መ/ቤት ህንፃ ለማስገንባት ከቻይናው ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ጋር የግንባታ ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ከትናት በስቲያ በሂልተን ሆቴል በተደረገው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት የህብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ታየ ዲበኩሉና በኢትዮጵያ የጂያንግሱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዙ ጃን የግንባታ የውሉን ኮንትራት ተፈራርመዋል፡፡ ባንኩ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሊዝ በተረከበው 3,338 ካ.ሜ ቦታ ባለ 32 ፎቁ ህንፃ የሚገነባው በተለምዶ ሰንጋተራ በሚባለው አካባቢ ከንግድ ሥራ ኮሌጅ ፊት ለፊት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ታየ፣ ይህ እጅግ ዘመናዊ የዋና መ/ቤት ሕንፃ 119 ሜትር ቁመት (ከፍታ)፣ ምድር ቤቱ በአንድ ጊዜ 200 ያህል መኪኖች መያዝ የሚችል ባለ 4 ፎቅ መኪና ማቆሚያ የዋና መ/ቤት ቅርንጫፍ፣ የሰራተኞች መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የሥልጠና ክፍሎች፣ የሰራተኞች መዝናኛ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የህንፃ መቆጣጠሪያ (ቢኤምኤስ) ስምንት ዘመናዊ አሳንሰሮች፣ የባንክ ሴኪዩሪቱ ሲስተምና ዳታ ማዕከል እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡
ለዋና መ/ቤቱ ህንፃ ዲዛይን በወጣው ጨረታ ከ40 በላይ አርክቴክቶች ተወዳድረው ሰባቱ ለመጨረሻው ዙር ሲያልፉ፣ ከፍተኛ የህንፃ ዲዛይን እውቀት ሙያ ባላቸው ዳኞች እስክንድር ውበቱና ሸሪኮቹ የአርኪቴክቸሮች አማካሪና ኢንጂነሮች ኩባንያ ጨረታውን ማሸነፉ ታውቋል፡፡
አሸናፊው ድርጅት የህንፃውን ዝርዝር ዲዛይን አዘጋጅቶ እየተቆጣጠረ የሾሪንግና የቁፋሮ ሥራው መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ታየ ዲበኩሉ፤ የመሰረት ቁፋሮ በዚህ ወር ተጀምሮ ግንባታው በሶስት ዓመት ተኩል ያልቃል ብለዋል፡፡ (ጃንግሱ ኢንተርናሽናል ከቻይና ውጪ ባሉት ከ30 በላይ ቅርንጫፎቹ በርካታ ግንባታዎችን ያከናወነ ኮንትራክተር ነው፡፡ የወሰዳቸውን ፕሮጀክቶች የሚጨርሰው ከገባው ቀነ ቀጠሮ በፊት በመሆኑ፣ ይህንንም ፕሮጀክት በሦስት ዓመት ካልሆነም፣ በሦስት ዓመት ተኩል ይጨርሳል የሚል እምነት አለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

Read 3008 times