Saturday, 16 May 2015 11:17

ረጲ ዊልማር በ7 ቢ. ብር 14 የማኑፋክቸሪንግ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

የአገሪቷን ዘይት ፍላጎት 80 በመቶ ይሸፍናል ተብሏል
             
   ረጲ ሳሙናና ዲተርጀንት አክሲዮን ማኀበር መቀመጫው ሲንጋፖር ከሆነው ዊልማር ኢንተርናሽናል ሊሚትድ ጋር በጋራ ለመሥራት በእኩል (50፣50) ድርሻ ረጲ ዊልማር ማኑፋክቸሪንግ አክሲዮን ማኅበር በ7 ቢሊዮን ብር 14 ማኑፋክቸሪንግ ፋብሪካዎች ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።
የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጡ ሥርዓት የተከናወነው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ረጲ ዊልማር በሁለት ምዕራፍ የማኑፋክቸሪንግ ኮምፕሌክስ ኢንዱስትሪዎችን በሚገነባበት በኦሮሚያ ክልል በሰበታ ከተማ አስተዳደር በዲማ ቀበሌ ሲሆን፣ ይህን ታሪካዊ የሆነ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚ/ር ክቡር ኃይለማርያም ደሳለኝና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ክቡር ሙክታር ከድር ናቸው፡፡
ዊልማር ኢንተርናሽናል ሊሚትድ እ.ኤ.አ በ1991 በማሌዥያ ሲንጋፖር የተመሰረተ ሲሆን፣ የእርሻ ሰብል ምርቶችን በማቀነባበር፣ ደረጃቸው በጠበቁ ዕቃዎች በማሸግና በማከፋፈል በኤስያ  ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅት መሆኑ ታውቋል። ዊልማር ከ50 በላይ በሆኑ አገሮች የንግድ ትስስር ፈጥሮ የሚሰራ ኩባንያ ሲሆን 450 የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችና 95ሺህ ሰራተኞች ያስተዳድራል፡፡
በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰሜን፣ በምዕራብ፣ በደቡብና በምሥራቅ በ13 አገሮች በተለያዩ ዘርፎች የሚንቀሳቀሰው ዊልማር፤ ከ5 ወር በፊት በተጠናቀቀው 2014 ባላውሪክና በፓልም ዘይት ማቀናበር በዓለም ቀዳሚ፣ በኤስያ ግዙፍ የፓልም ዘይት እርሻ ባለቤት፣ በቻይና ግንባር ቀደም የቅባት እህሎችና በአውስትራሊያ ቀዳሚ የስኳር አምራች፣ የፓልም ዘይትና ተረፈ ምርቶች እንዲሁም የሳሙናና ዲተርጀንት ምርቶች ወደ አፍሪካ በማስገባት መሪ ድርጅት መሆኑ በሥነ-ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
በመንግሥት ይተዳደር የነበረውን ረጲ ሳሙናና ዲተርጀንት አ.ማን ሊና ኃ.ተ.የግ.ማ በ1999 ዓ.ም ገዝቶ፣ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ያረጁ መሳሪያዎችን በአዲስ መተካታቸውን፣ ከነባሩ ፋብሪካ ተያያዥ የነበረውን 17,306 ካ.ሜ መሬት በሊዝ ገዝተው፣ በውቅር ብረት የማምረቻ መሳሪዎች መትከያ መገንባታቸውንና ፋብሪካው ቀደም ሲል ከሚያመርታቸው የዲተርጀንት ውጤቶች በተጨማሪ በተከሏቸው አዳዲስ መሳሪያዎች የላውንደሪ ሳሙና እያመረቱ መሆኑን የገለጹት የፋብሪካው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ካሚል ሳቢር፣ ሌሎች የምርት ማሳደጊያ ዘዴዎች በመጠቀም፣ 195 የነበረውን የሠራተኛ ቁጥር ወደ 600 በማሳደግ፣ በየዓመቱ የሚያመርተው ምርት የሚያስገኘውን ትርፍ በ10 እጥፍ ማሳደግ መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡
አቶ ካሚል አክሲዮን ማኅበሩ፣ ሳሙናና ዲተርጀንት በማምረት ያገኘውን ልምድ በመጠቀም፣ በ600 ሚሊዮን ብር ካፒታል፣ በዓይነቱ አዲስና ዘመናዊ የሆነ የሳሙናና የዲተርጀንት ፋብሪካ ለመገንባት ከሰበታ ከተማ አስተዳደር በፉሪ ቀበሌ 50 ሺህ ካ.ሜ በሊዝ መውሰዳቸውን፤ የሲቪል ግንባታው መጠናቀቁንና የማምረቻ መሳሪያዎቹን ከኢጣሊያ ተገዝተው ሙሉ በሙሉ ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን፣ ለመሳሪያዎቹ ተከላ ዝግጅት እያደረጉ ሳለ ፋብሪካውን የበለጠ ለማዘመንና ምርታቸው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው አብሯቸው የሚሠራ ሸሪክ ኩባንያ ማፈላለግ መጀመራቸው ተናግረዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ መሠረት የካፒታል እጥረት እንዳይፈጠር፣ ዘመናዊ የማኔጅመንት ልምድ ለመቅሰም፣ የተሻለ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም፣ የእውቀት ሽግግር ለማድረግና በቀላሉ ወደ ውጭ ገበያ ለመግባት የውጭ ተባባሪ ኢንቬስተር ሲያፈላልጉ ከሲንጋፖሩ ዊልማር ኢንተርናሽናል ሊሚትድ ጋር ውይይት እንደጀመሩ በተወካያቸው በኩል የገለጹት የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሳቢር አርጋው ናቸው፡፡
ዊልማር ኢንተርናሽናል አብሯቸው ሊሠራና በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ በመስማማቱ የስምንት ሰዎች ወጪ ችሎ በማሌዥያና በኢንዶኔዢያ ያሉትን የኢንዱስትሪ ማዕከሎች እንዲጎበኙ እንደጋበዟቸው የጠቀሱት የቦርድ ሰብሳቢው፣ የቴክኒክና የህግ ባለሙያዎችን ይዘው ሄደው ለ15 ቀናት የዘይት፣ የሳሙናና ዲተርጀንት፣ የስንዴ ዱቄት፣ የፓልም እርሻ፣ የግሪስሊንና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች… መጎብኘታቸውንና ዊልማር ኢንተርናሽናል በዓለም አቀፍ ያለውን አቅም፣ የምርቶቹን የጥራት ደረጃ፣ ዘመናዊ አሰራሩን፣ በአጭር ጊዜ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን የመገንባት አቅሙን፣ የወጪና ገቢ ምርቶች ማቀላጠፊያ ዘዴውን፣ የጥሬ ዕቃ፣ የምርት ማከማቻማና ማዘዋወሪያ ሥርዓቱ፣ የምርምር ተቋማቱ፣ የማኔጅመንት አመራሩ የተራቀቀ መሆን እንዳስገረማቸው አቶ ሳቢር አብራርተዋል፡፡
ይህ በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ አቅምና ልምድ ያለው ኩባንያ አብሯቸው ለመስራት በመስማማቱ ረጲ ሳሙናና ዲተርጀንት አ.ማ እና ዊልማር ኢንተርናሽናል ሊሚትድ ኩባንያዎች በእኩል 50 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ፣ በሰበታ ከተማ አስተዳደር በዲማ ቀበሌ በተፈቀደላቸው 100 ሄክታር መሬት ላይ በ7 ቢሊዮን ብር ካፒታል 14 የተለያዩ ፋብሪካዎች ለመገንባት ባለፈው ዓመት ሐምሌ 2006 ዓ.ም በሽርክና (ጆይንት ቨንቸር) አብረው ለመሥራት ውል መፈፀማቸውን  አቶ ሳቢር አርጋው ተናገረዋል። ሁለቱ ኩባንያዎች በገቡት ውል መሠረት የሚገነቡት የፓልም ዘይት ማጣሪያ፣ የሳሙናና ዲተርጀንት፣ የገበታ ቅቤ፣ የሳሙና ሮድልስ፣ ሶዲየም ሲልኬት፣ የላውንደሪ ሳሙና፣ የብሎውና የኢንጄክሽን ሞልድ ፕላስቲክ፣ የዕቃ ማሸጊያ፣ የቅባት ክህሎት ማቀነባበሪያ፣ የግል ንፅህና መጠበቂያ፣ ሱፍና የአኩሪ አተር (ቦሎቄ) የተጣራ ዘይት፣ የስንዴ ዱቄት፣ የማካሮኒና የፓስታ፣ እንዲሁም የማዳበሪያ ፋብሪካዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ረጲ ዊልማር አ.ማ ፋብሪካዎቹን የሚገነባው በሁለት ምዕራፍ ከፍሎ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ካሚል፤ በመጀመሪያው ዙር በ3.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚገነቡት የፓልም ዘይት ማጣሪያ ፋብሪካ፣ የሳሙናና ዲተርጀንት፣ የገበታ ቅቤ፣ የሳሙና ኖድልስ፣ የሶዲየም ሲልኬት፣ የላውንደሪ ሳሙና፣ የብሎውና የኢንጀክሽን ሞልድ ፕላስቲክ፣ የዕቃ ማሸጊያና የቅባት እህሎች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንደሆኑ ገልጸዋል፡
በሁለተኛው ምዕራፍ በ3.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚገነቡት የግል ንፅህና ፋብሪካ፣ የሱፍና የአኩሪ አተር የተጣራ ዘይት፣ የስንዴ ዱቄት፣ የማካሮኒና የፓስታ፣ እንዲሁም የማዳበሪያ ፋብሪካዎች እንደሆኑ ጠቅሰው የመጀመሪያው ዙር ፋብሪካዎች ግንባታ በ18 ወራት እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡
አቶ ካሚል ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ የመጀመሪያዎቹ የፋብሪካ ግንባታ ጁን 15 ቀን 2015 ተጀምሮ ቀንና ሌት እየሰሩ በ18 ወራት እንደሚያጠናቅቁ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል። የዘጠኝ ፋብሪካዎች ግንባታ እንዴት በ18 ወራት ያልቃል? ተብለው ሲመልሱ፣ ዊልማርት፣ በኢንዶኔዢያ የ47 ፋብሪካዎች ግንባታ በ3 ዓመት ተኩል መጨረሱን በጉብኝታችን ወቅት አይተናል፡፡ ልምድ ስላለው የዘጠኙን ፋብሪካዎች ግንባታ በ18 ወራት ያጠናቅቃል ብለዋል፡፡
የፓልም ዘይት ማጣሪያ ፋብሪካው ግንባታ እንደተጠናቀቀ ማጣራት ይጀምራል ያሉት አቶ ካሚል፤ ፋብሪካው የሚያጣራው ድፍድፍ ዘይት ከማሌዢያና ከኢንዶኔዢያ እንደሚመጣ፣ ዊልማር 49 መርከቦች ስላሉት አንዱ መርከብ 4,000 ቶን ድፍድፍ ዘይት አምጥቶ በጂቡቲ ወደብ ያራግፋል ብለዋል፡፡ ከጂቡቲ መንግሥት 60 ሺህ ካ.ሜ ቦታ ተረክበው የድፍድፍ ዘይት ማጠራቀሚያ ዴፖ እየገነቡ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ድፍድፍ ዘይቱን በባቡር ወደ ማጣሪያ ፋብሪካው ማመላለሻ 50ሺህ ሊትር የሚይዝ ታንከር እያስገነቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመጀመሪያው ዙር እቅዳችን ከውጭ የሚገባውን ዘይት መተካት ነው ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በዓመት 420 ሺህ ቶን ዘይት እንደሚያመርቱ፣ በአሁኑ ወቅት የአገሪቷ የዘይት ፍላጎት 530 ሺህ ቶን እንደሚገመትና 420ሺህ ቶን በማቅረብ የገበያውን 80 በመቶ እንደሚሸፍኑ፣ ለገበያ የሚያቀርቡበትን ዋጋ አሁን ላይ ሆነው መናገር እንደማይችሉ ነገር ግን አሁን ከሚሸጥበት ዋጋ እንደሚቀንስ ገልጸዋል፡፡
ሁለተኛው ዙር የፋብሪካዎች ግንባታ ሲጠናቀቅ፣ የአገር ውስጥ ፍላጎት ካሟሉ በኋላ ምርቶቻቸውን ወደ ጎረቤት አገሮች ማለትም ወደ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ …. በአብዛኛው ለኮሜሳ አባል አገሮች መላክ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህ አገር የሰሊጥ ዘይት ፍላጎት ባይኖርም፣ ቻይናውያን ለምግብ ጣዕም ስለሚፈልጉት እዚህ አምርተን ወደ ቻይና ኤክስፖርት እናደርጋለን፡፡ እዚህም ፍላጎቱ ካለ እናቀርለን ብለዋል፡፡
ከ2 ዓመት በኋላ ወደ ፓልም ተክል እርሻ እንገባለን ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በጋምቤላ አካባቢ እርሻውን ለመጀመር መጠነኛ ጥናት መጀመሩን፣ ዊልማርም እርሻ ለመጀመር የጠየቀ ስለሆነ ከእሱ ጋር በመሆን ጠለቅ ያለ የአዋጪነት ጥናት አድርገን ውጤታማ ከሆነ ወደ እርሻ እንገባለን ብለዋል አቶ ካሚል ሳቢር፡፡
በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ የኢንዱስትሪ ልማት ዋነኛ ሞተር የአገር ውስጥ ባለሀብት እንደሆነ ጠቅሰው አሁን ያሉት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ ትንሽ ነው፡፡ አቶ ሳቢር አርጋው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በራሳቸውም ሆነ ከውጭ ኢንቬስተሮች ጋር በመሆን የኢንዱስትሪ ሞተር መሆናቸውን በማሳየታቸው ለእሳቸው ታላቅ ክብርና ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚፈጠሩት ከአገልግሎት፣ ከንግድና ከኮንስትራክሽን ዘርፍ እንደሆነ፣ ለዚህ አብነት አቶ ሳቢርን ጠቅሰው እንደ አቶ ሳቢር ዓይነት ብዙ ሰዎች ስላሉ ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በሚያደርጉት ሽግግር፣ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብዋል፡፡
በርካታ ባለሀብቶች በኮንስትራክሽን ዘርፍ መሰማራታቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ ባለሀብቶች ብዙ የኮንስትራክሽን ግብአቶች ስለሚጠቀሙ ወደ ኢንዱስትሪ ግብአት ምርቶች ማምረቻ ቢሸጋገሩ በዘርፉ ልምድ ስላላቸው ቀላል ይሆናል፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች ለብቻ ወይም ከውጭ ኢንቬስተር ጋር በመሆን የቴክኖሎጂ፣ የገበያና የእውቀት ሽግግር በማድረግ ለአገር ልማት ሞተር መሆን አለባቸው፡፡ የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ የሚገኘው ከግብርና በመሆኑ የአገራችን ባለሀብቶች ወደ ግብርና ቢገቡ መንግሥት የእርሻ መሬት በማዘጋጀት፣ ብድር በማመቻቸትና አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ድጋፍ በማድረግ ያግዛል ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር ክልሉ ለኢንቬስትመንት አመቺና ምቹ በመሆኑ ወደ ክልሉ ለሚመጡ ኢንቬስተሮች አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር ይደረጋል ብለዋል፡፡
ፋብሪካዎቹ በግንባታ ወቅት ከ6,000 እስከ 8,000፣ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ ደግሞ ከ10,000 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ታውቋል፡፡  

Read 3013 times