Saturday, 16 May 2015 11:27

አዲስ ፍኖት

Written by  ሶፎንያስ መሐመድ
Rate this item
(22 votes)

ላንቺ…
እንደምወድሽ ክጄ አላውቅም፡፡ ትላንት አልካድኩም። ዛሬም፣ ነገም አልክድም፡፡ ፍቅርሽ ሰውነት እንዲሰማኝ አድርጓል፡፡ ቀዩ ፊትሽ መስታወቴ ነው፡፡ ሳይሽ እራሴን አያለሁ፡፡ ሳወራሽ ‘ራሴን ያወራሁ ያክል ይሰማኛል፡፡ አፍንጫሽ ቁሞ ሳየው፤ ቅጥና ልክ ባጣው ያንቺ ፍቅር አንድ ቦታ ላይ ቁሞ የቀረው ማንነቴ ትውስ ይለኛል፡፡ በስጋዊ ህይወቴም ሆነ በመንፈሳዊ ህይወቴ እንደ ጅግራ አንድ ቦታ ላይ ተገትሬ መቅረት እንደሌለብኝ አስባለሁ፡፡ ልቤ ውስጥ ለውጥ እያለ ሲጮህ እሰማዋለሁ፡፡
ወደፊት ባለመራመድ እንዳቆረ ውሃ ከጊዜ ብዛት መበከትና መሽተት እንዳልጀምር እሰጋለሁ፡፡ መፍትሄው መንቀሳቀስ፤ ‘ላይ ‘ታች ማለት መሆኑንም አምናለሁ፡፡ ኑሮን ለማሸነፍ እየሮጥኩ ቢሆንም የበለጠ መቀልጠፍ፣ የበለጠ መሮጥ እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ ይሄ ደግሞ ግላዊ ህይወቴን ለማደርጀትና ኑሮ ላይ ለመጀገን የታሰበ ብቻ አይደለም፡፡ አንቺን ለማስደሰት ነው፡፡ እንድትመኪብኝና እንድትኮሪብኝም ለማድረግ ነው።
ህይወት ሁለት መልክ አላት፡፡ አንዱ መልክ እንደ ወርቅ የደመቀ እና እንደ አልማዝ የተወደደ ነው። ሌላው መልክ ጨረቃ አልባ እንደሆነ እና ከዋክብት እንዳደሙበት ሰማይ ጨለማ የወረሰው ነው፡፡ ድቅድቅ ጨለማ እንደነገሰበት ሌሊት ነው፡፡
ህይወት ለድምቀቱም ሆነ ለፍዘቱ ደንታ እንደማይኖራት ግልፅ ነው፡፡ ደንታ ያለን እኛ ነን። ህይወትን የመሾፈሩም ሆነ የማብረሩ ድርሻ የእኛ ነው፤ የእኛ የሰዎች! እና አንቺ ከጎኔ ስትሆኚ ተዋበች የአፄ ቴዎድሮስ ቀኝ እጅና መካሪ ዘካሪ እንደሆነችው፤ እኔም የልብ ልብ የምትሰጭኝ ያንቺ የልብ ወዳጅና እውነተኛ አፍቃሪ ለመሆን እጥራለሁ፡፡
ባንቺ እይታ ጥረቴ ሰምሮ ይሁን ከሽፎ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እውነተኛ አፍቃሪሽ ስለመሆኔ ግን በአስር ጣቶቼ ብቻ ሳይሆን በሃያ ጣቶቼ (በእግሬ ጭምር) እፈርማለሁ፡፡ ከማያዋጣው ወደሚያዋጣው፤ ከማይበጀው ወደሚበጀው፤ ከሚያከስረው ወደማያከስረው፣ ከማያተርፈው ወደሚያተርፈው ማንነት ባንቺ እመራለሁ፡፡ አንቺ ምሪኝ፤ እኔም እከተልሻለሁ፡፡ እውነቱን ልንገርሽ! ካንቺ ምሬት ወዴትም አልሄድም፡፡ እመኝኝ ከመራሽኝ መንገድ ትንሽ እንኳ ዘመም አልልም። ምክንያቱም እተማመንብሻለሁ። ምክንያቱም አብዝቼ እመካብሻለሁ፡፡
ከንፈሮችሽን ሣይ ከንፈሮቼን አስታውሳለሁ። መስታወት ፊት ቆሜም አያቸዋለሁ፡፡ “የቱ ውብ ነው?” ብዬ ለማወዳደር አይደለም፡፡ ያንዱን መጠን ከሌላው ጋር (የኔን ካንቺ ጋር) ለማስተያየት አይደለም፡፡ ምን ያህል ተገልበው ጥርሶቼን ለዕይታ አጋልጠዋል? ምን ያህል እርስ በርስ ተግባብተዋል? ወይም ምን ያህል አንድ ላይ ተሰፍተዋል? የሚለውን ለማወቅ ነው፡፡
ከንፈሮችሽን በአትኩሮት እመለከታለሁ፡፡ ሊፕስቲክ ለብሰው ወይም በቻፕስቲክ ወዝተው ሊሆን ይችላል። እሱን ከቁብም አልቆጥረውም። ጉዳዬ ከከንፈርሽ ልብሶች ሳይሆን ከዕርቃኖቹ ከንፈሮችሽ ነው፡፡
ስታወሪ ተመስጬ አያቸዋለሁ፡፡  ስትስቂ ወይም ፈገግ ስትይ አትኩሬ አያቸዋለሁ፡፡ ዝም ስትይም ከንፈሮችሽ እንደተሰበሰቡ በአይኔ ፎቶ አነሳቸዋለሁ።
ልንገርሽ?! … በሶስቱም ሁኔታ ላይ ሆነው ሳያቸው ያስደምሙኛል፡፡ ዝም ብለው መግጠማቸው መልዕክት ያለው ይመሰልኛል፡፡
ስታወሪ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከአንደበትሽ ከሚወጡት ቃላት በላይ የሚናገሩት ያላቸው ይመስላቸዋል፡፡ ስትስቂ ወይም ፈገግ ስትይ ወደ ቀኝና ግራ ጉንጮችሽ ሸርተት ሲሉ ለጉንጮችሽ ምስጢር ለማካፈል የሚንፏቀቁ (የሚሳቡ) ይመስላሉ፡፡
እኔ እረዳለሁ፡፡ ፍላጎታቸው ይገባኛል፡፡ እንቅስቃሴያቸው የሆነ ነገር ሹክ ይለኛል፡፡ መሳም ያማራቸው ይመስለኝና ልስማቸው እጓጓለሁ፡፡
ጥያቄ አለኝ ሊያ … ከምት ትወጂኛለሽ?! …
እየጠየኩሽ ያለሁት እንደ ዓሣ ለብለብ የሆነውን ለብለብ ፍቅር አይደለም፡፡ እየጠየኩሽ ያለሁት ስለእውነተኛውና ጥልቁ ፍቅር ነው፡፡ እንደመነኩሴ ቆሎ ብቻ እየበሉና ውሃ ብቻ እየጠጡ በአንድነት ተስማምቶ ለመኖር ስለሚስችለው ፍቅር!
እውነት ነው፤ አሁን እንዳጦዝኩት ጥብቁ ፍቅር ይቅርና “ተራው” ፍቅር ራሱ አለ ወይ? የሚሉ ጓደኞች አሉኝ፡፡ ፍቅር የለም የሚሉት ከመህበ አልቦ አይደለም። ዘመኑን ቃኝተው ነው፡፡ ወጣቱን አጥንተው ነው፡፡
እኔ ግን እላለሁ፤ ፍቅር አለ፡፡ ስለመኖሩም እኔ እንደ አብነት ልታይ እችላለሁ፡፡ ፍቅር የለበስኩ፤ ፍቅር የጎረስኩ፤ ስለ ፍቅር መኖር እርግጥነት በእርግጠኛነት ልታመን የምችል ህያው ምስክር ነኝ።
ፍቅር እንዴት እንዴት ያደርጋል? ይህን እኔ አላብራራውም፡፡ ስሜቱ ካለሽ አንቺ ብትነግሪኝ ደስ ይለኛል፡፡ ይህን ካደረግሽ እኔም ምናልባት በተራዬ የኔን ልነግርሽ እችላለሁ፡፡
ለአንባቢ፡- …
ሊያን የማውቃት ድሮ ነው፡፡ ድሮ! … የዛሬ ስንት ዓመት ልበላችሁ? ምናልባትም አስር ምናልባት አስራ አምስት፣ እንደዛ! (የቀንና የዓመት ቆጠራ የማይሳካልኝ ዜጋ ነኝ)፡፡
መጀመሪያ የተለየ ስሜት አልነበረኝም፡፡ ጓደኛዬ ነበረች፡፡ እንደማንኛውም ሴት ጓደኛ ጓደኛ! የማናወራው ነገር አልነበረም፡፡ ገና በተዋወቅን በመጀመሪያው ቀን ነው ሰፊ ጊዜ አብሮ ማሳለፍን አሃዱ ያልነው፡፡ ስለራሷ ብዙ ነገር አወራችልኝ፡፡ በጥሞና ሰማኋት፡፡ እሷ አፍ፤ እኔ ጆሮ ነበርን፡፡
ካወራችው ነገሮች ጥቂቱን አስታውሳለሁ፡፡ አንዱ የወሬያችን ርዕስ አባቷ ነበሩ፡፡ አባቷን በጣም ነው የምትወዳቸው፡፡ ፍቅር የተባለ ሁሉ ተጠቅልሎ ልቧ ውስጥ ተኝቷል፡፡ ፍቅር ልቧ ውስጥ ዳስ ጥሏል። የአባት ፍቅር …
ብዙ ሰዎች ብዙ ጊዜ ሲያወሩ የሚደመጡት ስለ እናት እና ስለ እናት ፍቅር ነው፡፡ እሷ ግን ስለ አባቷ አውርታ አትጠግብም፡፡ ስለአባቷ አክርራና አግና ስትናገር እናት የላትም ወይም የነበራት ሁሉ አትመስልም፡፡ አባቷ ወንድም፣ ሴትም፤ አባትም እናትም ሆነው የወለዷት ይመስላል፡፡
“አባቴ ለኔ ያልሆነው ነገር የለም” ትላለች፡፡
“አባቴ አምላኬ ነው” ለማለትም አትፈራም፡፡ በድፍረትና በእርግጠኝነት ትላለች፡፡
“እግዜር መኖሩን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ኖረ ብለን ብናስብ እንኳን የሱ ውለታ የለብኝም፡፡ ያደረገልኝ ወይም ባለኝ ነገር ላይ የጨመረልኝ ነገር የለም፡፡ እግዜሬ አባቴ ነው፡፡”
አባቷ የጉልበት ሥራ እየሰሩ ነው ያሳደጓት። ባተሌ ነበሩ፡፡ አርፈው አያውቁም፡፡ ሥራም አይንቁም፡፡ ያገኙትን ሁሉ ይሰራሉ፡፡ ላባቸውን በብዙ አፍሰው፤ በጥቂቱ ያገኛሉ፡፡ ሱስ የለባቸውም። ሌላም ምንም አመል ስለሌለባቸው፤ ያገኙትን ይዘው ቤት ይገባሉ። እንደሰው መዝናናት ታይቷቸው አያውቅም፡፡ ራሳቸውን ለማስደሰት አንድም ቀን አስበው አያውቁም። ለራሳቸው ሱሪ ወይም ሸሚዝ ሳይቀይሩ ለሷ ቀሚስ ይገዛሉ። ለራሳቸው ማክያቶ እንኳን ሳይጠጡ እሷን ፊልም ይጋብዛሉ፡፡
እንደልጅም፣ እንደጓደኛም ነው የሚያኖሯት። ሌላ ወንድ ወይም ሴት የላቸው፡፡ እሷ ብቸኛዋ ልጃቸው ናት፡፡
“አባቴ” አለችኝ ሊያ “አባቴ ገና የራሱን ህይወት መኖር አልጀመረም፡፡ አሁንም ድረስ የሚኖረው ለኔ ነው፡፡ ውሎ የሚያድረው የኔን ውሎና አዳር ነው፡፡ ህይወቱ እኔ ነኝ፡፡”
“በጣም ይወዱሻል ማለት ነው?” ስል ጠየኳት። “በጣም እንጂ! በጣም! በአፍ ቃል አውጥቶ ነግሮኝ አያውቅም፡፡ ድርጊቱን ግን አነባለሁ፡፡ ድርጊቱን በማንበብ ብዙ ነገር እረዳለሁ፡፡ እንደሚወደኝና እንደሚያምነኝ ብቻ ሳይሆን እንደሚሞትልኝ ጭምር አውቃለሁ፡፡” አለች በእርግጠኝነት፡፡
“ከሚስቱ (ከእናቴ) ጋር ከተፋቱ ቆይቷል። እናቴን ብዙም አላውቃትም፡፡ እናትም አባትም የሆነኝ አባቴ ነው፡፡ እናቴ ሌላ ባል አግብታ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ትኖራለች፡፡ እዚህ እየኖረችም ብዙ አንገናኝም። አትፈልገኝም፡፡ አንዳንዴ እንገናኛለን። ብዙም ሳንጫወት እንለያያለን፡፡ እና የእናቴን ጣዕም አላውቅም። ብትሞት እንኳ የምደነግጥ ወይም የማዝን ወይም የማለቅስ አይመስለኝም፡፡ እናቴን አላውቅም፡፡ እናቴ ለኔ ባዳ ነች።” ብላ ተረከችልኝ።…
ሌላው የማስታውሰው ነገር ስለ ብርሃኑ ያወራችልኝን ነው፡፡ “ስጠራው ብሩ ነበር የሚለው፤ አሁን አሁን ግን ብርሃኑ እያልኩ ነው የማወራው። ብርሃኔ ብርሃኑ ሆኖ ነበር፡፡ የቶማስ ኤዲሰን ስሪ ከሆነው አምፖልና የእግዜር ስሪት ከሆኑት ፀሐይና ጨረቃ በላይ ነበር ለኔ ብርሃንነቱ። ይጠራልኝም ያበራኝም ነበር፡፡” አለችኝ፡፡ ዝም ብዬ ማድመጤን ቀጠልኩ፡፡
ፈገግ ብላ መልሣ ኮስተር አለች፡፡ ከፈገግታ ወደ መኮሳተር ስትሻገር መብራት የሄደ መሰለኝ፡፡
“ምን ያደርጋል … ሁሉም በነበር ቀረ” አለች ትክዝ ብላ “ተጣልታችሁ ነው?” አልኳት፡፡
“አይደለም፡፡ መጣላት አይባልም፡፡ መደባበር ሳይሆን አይቀርም”፡፡ ዞር ብላ፤ አየችኝ፡፡ እያዳመጥኩ እንደሆነ በአንገቴ ንቅናቄ ነግሬያት ፈገግ አልኩ፡፡ ፈገግታው ተጋባባት፡፡ ፈገግ ስትል ዙሪያ ገባችን በብርሃን ተጥለቀለቀ፡፡ አባቴን አይወደውም ነበር አለች፡፡
ከሱ ጋር ሆኜ ሳለ አባቴ ፈልጎኝ ከደወለልኝ “አባቴ ጠራኝ” ብየው እለየዋለሁ፡፡ ከብርሃኑ ጋር ተቀጣጥረን ከጨረስን በኋላ አባቴ ከኔ ጋር ሊያወራ ወይም ሊጫወት ፈልጎ ከሆነ ቀጠሮውን እሰርዛለሁ። ከአባቴ የማስቀድመው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ብርሃኑ በዚህ ይናደድ ነበር። አንድ ቀን ተማሮ አባቴን ሲሰድብ ሰማሁት፡፡ አባቴ በመሰደቡ ተብከነከንኩ፡፡ ከዛ በኋላ ፍቅሬ ቀነሰ፡፡ አባቴን ምንም እንዲጀካብኝ፤ ማንም እንዲናገርብኝ አልፈልግም፡፡ ይህና ሌላ ሌላም ምክንያትም እየተጨማመረ ለመለያየት በቃን” ገረመኝ። ለአባቷ ያላት ስሜት ጥንካሬና ጥልቀት ደነቀኝ፡፡
“ታድሏል” አልኩኝ አባቷን፡፡ እሷ ግን “እኔ ነኝ የታደልኩት” ትላለች፡፡
“እንደዚህ ዓይነት አባት በማግኘቴ እድለኛዋ እኔ ነኝ።”
*   *   *
ከሊያ ጋር በጓደኝነት ለብዙ ዓመታት አብረን ኖርን፡፡ በኋላ ግን ከመቀራረብም ከመግባባትም ብዛት ግንኙነታችን ወደ ፍቅር ተለወጠ፡፡ “መላመድ ፍቅር ነው” ይባል የለ?!
በጣም የምወዳት ሊያ ለፍቅር የማታመች ሆና አገኘኋት፡፡ ይህን ሳውቅ አዘንኩ፡፡ ሀዘኔ አንገት አስደፋኝ። ምን አደረገች?!
ወዳጀ ብዙ ናት፡፡ ዘመደ ብዙ ጠላው ቀጭን ነው ሳይሆን ወዳጀ ብዙ ፍቅሩ ቀጭን ነው ቢባል ሳይሻል አይቀርም፡፡ ብዙ የወንድና ሴት ጓደኞች አሏት፡፡ ሁሌም ቢዚ ናት፡፡ ለኔ ጊዜ አልሰጥ አለችኝ፡፡ ባይ ባይ አትለውጥም፡፡
ከኔ ጋር ገና ተገናኝተን ቁጭ ከማለቷ አባቷ ከደወሉ ጥላኝ ትሄዳለች፡፡ የአባቷን እንኳ እንደምንም ለመረዳት ሞክሬ ነበር፡፡ የባሰብኝ የሌሎቹ ነው፡፡ ላግኝሽ ብዬ ስደውልላት፡-
አበራን ቀጥሬዋለሁ፡፡ ማህሌትን አገኛታለሁ፡፡ ከተሸም ጋር ተቀጣጥረናል፡፡ ተሻለ ይጠብቀኛል፡፡
ሰለሞንን ላገኘው ነው፡፡ ….ትለኛለች፡፡ በድርጊቷ መናደድ ጀመርኩ፡፡ በመጨረሻ ምክንያቴን ሁሉ ነገሬ ተለየኋት፡፡ እየወደድኳት ተውኳት፡፡ ፍቅሬ አልወጣልኝም ነበር፡፡ ፍቅሬን አልጨረስኩም ነበር፡፡ ግን ምን ላድርግ? ከአቅሜ በላይ ሆነ፡፡ ብስጭቱን አልቻልኩትም፡፡ ሁሌ በንዴትና ቅናት ከመድበን አንደኛውኑ ተለያይቶ ናፍቆቱን መቻል ይሻላል ብዬ ወሰንኩ፡፡ ናፍቆቱን ግን በአግባቡ ልቆጣጠረው አልቻልኩም። በጣም ትናፍቀኝ ነበር፡፡ መደዋወሉን አቆምን። መገናኘቱን አቆምን፡፡ እና ሙሉ ለሙሉ የፍቅርን አጀንዳ ዘግተን ተጠፋፋን፡፡
*   *   *
ከሊያ ጋር ከተለያየን ከዓመት በኋላ መንገድ ላይ ተገናኘን፡፡
“በጣም እፈልግህ ነበር” አለችኝ፡፡
“አንድ ቀን አግኝቼህ ባጫውትህ ደስ ይለኝ ነበር፡፡”
ተገናኘን፡፡
“አጥፍቻለሁ” አለችኝ፡፡ “ለጥፋቴ ይቅርታ አድርግልኝና ጓደኝነታችንን ብንቀጥል ደስ ይለኛል፡፡”
ተስማማሁ፡፡
(ይቀጥላል)

Read 5827 times