Saturday, 16 May 2015 11:42

በትግራይ፤ ህውሓት እና አረና ይፎካከራሉ!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የመድረክ ግንባር መስራች ፓርቲ የሆነው “አረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ለዲሞክራሲ” በትግራይ ክልል ዋነኛው የገዢው ህውሓት ፓርቲ ተፎካካሪ ሆኖ በመጪው ሳምንት ምርጫ ይወዳደራል። አረና በአጠቃላይ ለምርጫው እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴና ዝግጅት እንዲሁም ከምርጫው ምን ውጤት እንደሚጠብቅ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የፓርቲውን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጎይቶም ጸጋን አነጋግሯል፡፡


“አረና” ለዘንድሮ ምርጫ በትግራይ ክልል ምን ያህል እጩዎች አቅርቧል?
ፓርቲው በክልሉ በ38ቱም የምርጫ ክልሎች ለመወዳደር እየሰራ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች እጩዎቹ ተቀንሰውበት አሁን 28 ናቸው ለተወካዮች ም/ቤት የሚወዳደሩት፡፡ ይህም ሆኖ ግን የክልሉን ህዝብ በመንግስትነት ለመወከል የሚያበቃ የእጩ ቁጥር ነው ያለን፡፡
ለምርጫው እያደረጋችሁት ያለው የመጨረሻ ዝግጅት ምን ይመስላል?
 በአጠቃላይ ቅስቀሳዎችን በተጠናከረ መልኩ እያካሄድን ነው፡፡ ህዝባዊ ስብሰባዎችንም እያደረግን ነው፡፡ እስካሁን በመቀሌ ብቻ ነው ያልተሳካው፡፡ እሱንም ቢሆን ዛሬ (ቅዳሜ) እናደርጋለን፡፡ በየቦታው ያሉ እጩዎችና አስተባባሪዎች በየአቅጣጫው ቅስቀሳቸውን እያደረጉ ነው፡፡ ከምርጫ ቦርድ የተመደበልንን በጀትም ሆነ ሌሎች የገንዘብ አቅሞቻችንን ተጠቅመን በ13 ያህል መኪኖች የመጨረሻውን ቅስቀሳ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡
አረና ለክልል ምክር ቤት ያቀረባቸው እጩዎች ብዛት የትግራይ ክልል መንግስትን ለመመስረት የሚያስችል ነው?
በክልሉ አጠቃላይ ወደ 152 እጩዎች ናቸው የሚያስፈልጉት፡፡ እኛ ደግሞ ወደ 77 ያህል አቅርበናል፡፡ እንግዲህ በውድድሩ አብላጫ ቁጥር ለመያዝ ነው ያሰብነው፡፡ መንግሥት እንመሰርታለን ብለን ነው እየሰራን ያለነው፡፡ ከግማሽ በላይ የምርጫ ክልሎችን ካሸነፍን መንግስት የማንሆንበት ምክንያት የለም፡፡
በገዥው ፓርቲ በኩል አረና ከግማሽ በላይ ለማሸነፍ የሚያስችል እጩ እንዲያቀርብ አልተፈለገም ነበር፡፡ የእጩዎች ቁጥር የተለያዩ ምክንያቶችን እያቀረቡ ነው እንዲቀነስብን የተደረገው፡፡
በየትኞቹ አካባቢዎች ነው በእርግጠኝነት ልናሸንፍ እንችላለን ብላችሁ የምታስቡት?
ለይተን የምናስቀምጠው አካባቢ የለንም። አጠቃላይ እንቅስቃሴ ነው እያደረግን ያለነው። እየተወዳደርን ያለነው አሸንፈን ፖሊሲያችንን በሃገራችን እናስፈፅማለን በሚል እምነት ነው። ዓላማችን ሁለት ወይም ሶስት ወንበር ብቻ አግኝቶ ለመቀመጥ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ በተወዳደርንባቸው ቦታዎች አብላጫውን ውጤት ይዘን እንወጣለን የሚል እምነት ነው ያለን፡፡
ከእስካሁኑ እንቅስቃሴያችሁ አንፃር ከምርጫው የምትጠብቁት ውጤት ምንድን ነው?
እንግዲህ በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ መታወቅ ያለበት ግን የኛ እንቅስቃሴ ብቻ አይደለም ውጤታማ ሊያደርገን የሚችለው፡፡ የህዝቡም ሚና አለ፡፡ አቅማችን በፈቀደ መጠን እንቅፋቶችን ተቋቁመን ለመሄድ እየሞከርን ነው፡፡ ጠንካራ ስራም እየሰራን ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ምርጫ ተአምር አንጠብቅም፡፡ በጣም ከባድ ሊሆንም ይችላል። ምክንያቱም ገዥው ፓርቲ ህዝቡ ድምፁን እንዲሰጥ ነፃ ያደርገዋል የሚል እምነት የለንም፡፡ የሰራነው ነገር በቂ ነው ብለው ስለሚያስቡ መንገዱን ሁሉ ሊዘጉት ይችላሉ፡፡ ታዛቢዎችን ማስፈራራት ሊኖር ይችላል። ከዚህ አንፃር ካለፈው ምርጫም ተነስተን በነዚህ ጫናዎች የተነሳ አሁንም ኢህአዴግ ሊያሸንፍ ይችላል የሚል ስጋት ነው ያለኝ። ምክንያቱም ታዛቢ ጫና ከተደረገበት ምርጫው እንዴት ውጤት ሊገኝበት ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ እኛ ተስፋ አንቆርጥም። በዚያች ቀን እንኳ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ ከሆነ መንግስት የማንሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ህዝቡ እኮ ከኢህአዴግ ጋር አይደለም፡፡ በእርግጥ እነሱ ያን ቀን ምርጫውን ያለ ታዛቢ አፍነው ከያዙት አሁን ካላቸው የ99.6 በመቶ ውጤት ወደ 100 በመቶ ሊያመጡት ይችላሉ፡፡
እናንተ ግን ለምርጫው የሚጠበቅብንን ስራ ሰርተናል፤ በቂ ዝግጅት አድርገናል የሚል እምነት አላችሁ?
የኛም ስራ መቶ በመቶ ውጤታማ ነው ለማለት አይቻልም። ጉድለቶች አለብን፡፡ ግን ምርጫው የሚወሰነው በኛ እንቅስቃሴ ብቻ አይደለም፤ የህዝቡ ፍላጎት ወሳኝ ነው፡፡ በጣም ብዙ ክፍተቶች እንዳሉብን እናውቃለን፤ በቀጣይ መማሪያ ይሆኑናል።
ከምርጫ 2002 እና ከአሁኑ ምርጫ “አረና” ይበልጥ ተጠናክሬ ቀርቤአለሁ የሚለው በየትኛው ነው?
ባለፈው ምርጫ የእጩዎች ቁጥር ይበዛል፡፡ የአሁኑ በተለያዩ ምክንያቶች ቀንሷል፡፡ በእጩ ቁጥር ሲታይ ባለፈው ምርጫ የተሻለ ቁጥር ያቀረብን ቢሆንም በአጠቃላይ እንቅስቃሴው ግን በአሁኑ ጠንካራ ሆነናል፡፡ አረና እየተዳከመ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በ2002 ምርጫ ቅስቀሳና ስብሰባዎችን በማድረግ ጥሩ የነበርን ቢሆንም በአሁኑ በተለያዩ ምክንያቶች ትንሽ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ። ዞሮ ዞሮ በኛ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን በህዝቡም ይወሰናል፡፡
እናንተ ከተፎካካሪያችሁ የበለጠ የህዝብ ተቀባይነትና ድጋፍ አለን ብላችሁ ታምናላችሁ?
ምንም ጥርጥር የለውም፤ ተቀባይነት አለን። ለዚያ አይደለም እንዴ ፈርተው እያሰሩን ያሉት። ይሄንንማ ህውሓቶችም በሚገባ ያውቃሉ፡፡ በትግራይ ስብሰባና ሰልፍ የሚከለክሉበት ምክንያት እኮ  ስለሚፈሩንና ተቀባይነት እንዳለን ስለሚያውቁ ነው፡፡
በትግራይ ከህውሓት ውጪ ጠንካራ ተቀናቃኝ የምትሉት ፓርቲ አለ?
ዋነኛው ተቀናቃኛችን ህውሓት ነው፡፡ እሱም ዋነኛ የሆነው በጉልበት ነው፡፡ ሌላ ፓርቲ ግን ያለ አይመስለኝም፡፡ ከተቃዋሚዎች የተሻለ እጩ ያቀረበው አረና ነው፡፡ ፉክክሩ በዋናነት በህውሓትና በአረና መካከል ነው፡፡

Read 2814 times