Saturday, 16 May 2015 11:47

መንግሥት የስደትን ጉዳይ በጥልቀት መመርመር አለበት ተባለ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አሁን የወጣቱ ልብና አዕምሮ ከአገር ውጭ ነው
ከፍተኛው የስደት መንስኤ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው (ILO)
“በአገር ቤት ሰርቶ መለወጥ ይቻላል የሚለው ዲስኩር ለውጥ አያመጣም”
    አሊ ሃሰን፤ በቅርቡ በሜዲትራኒያን ባህር ህይወታቸውን ያጡት 8 የመርካቶ አባኮራን ሠፈር ልጆች አብሮ አደግ ነው፡፡ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም “በሰላም ያግባችሁ” ብሎ የሸኛቸው አብሮ አደጐቹ ድንገት የሞታቸውን መርዶ ሲሰማ ክፉኛ ከመደንገጡ የተነሳ ማመን አቅቶት እንደነበር ይናገራል፡፡ “ቤተሰቦቻቸው በድህነት ያሳደጓቸው አብሮ አደጐቼ፣ ያልፍልናል ብለው ነው ህይወታቸው ያለፈው” የሚለው የ25 አመቱ አሊ፤ እነሱ ከወራት በፊት ወደ ሊቢያ ለመሻገር የሱዳን ቪዛ ሲሰጣቸው በቂ ገንዘብ በእጁ ላይ ባለመኖሩ ተነጥሏቸው እንደቀረና ገንዘብ ሲያገኝ እንደሚቀላቀላቸው ቃል ገብቶላቸው መለያየታቸውን ያስታውሳል፡፡ አሁን አሊ ወደ ሱዳን የሚያስገባውን የ2 ወር የቱሪስት ቪዛ ለማግኘት እየተሯሯጠ ሲሆን በቅርቡ ተጓዥ ነኝ ብሏል - ለአዲስ አድማስ፡፡ “ይህን ሁሉ ሞትና አሰቃቂ ነገር እየሠማህ እንዴት ትሄዳለህ?” በሚል ለቀረበለት
ጥያቄ ሲመልስ፤ “እነሱ እድላቸውን ሞክረው አልተሳካላቸውም፤ እኔም እድሌን ልሞክር” ነው ያለው፡፡ በሃገር ቤት ሠርቶ መለወጥ ይቻላል፤ አሹቅ በልተን በእናቶቻችን ጉያ ውስጥ መኖር ምናምን  የሚባለው ለኔ ትርጉም የለውም” የሚለው አሊ፤ እዚህ ሀገር ተቀምጬ እስከ መቼ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ እመራለሁ ሲልም”  ይጠይቃል፡፡ ከሊስትሮ ጀምሮ አነስተኛ ሥራዎችን መስራቱን የሚናገረው ወጣቱ፤ ከ6 አመት በላይ የተለያዩ ተባራሪ የንግድ ስራዎችን ቢሰራም ከቤተሰብ ጥገኝነት መላቀቅ እንዳቃተው ይናገራል፡፡ ከእናቱና
ከሁለት እህቶቹ ጋር እንደሚኖር የጠቆመው አሊ፤ ከ3 አመት በፊት አባቱ መሞታቸውን ተከትሎ እህቶቹን የማስተማርና ወላጅ እናቱን የመጦር ሃላፊነት  እንደወደቀበት ይናገራል፡፡ ቤተሰቤ ፆም እንዳያድር ከጠዋቱ 12 ሰአት ጀምሮ እስከ ምሽት 2 ሰዓትና 3 ሰዓት ድረስ የተለያዩ ተባራሪ ስራዎችን ስሰራ ብውልም በቀን ከ60 እና 70 ብር በላይ ገቢ አላገኝም ይላል - ወጣቱ በምሬት። “በ70 ብር ምን ልታደርግበት ነው? ቁርስና ራትን እንተወውና ምሣ እንኳ ልብላ ቢባል ከ20 ብር በታች የሚሸጥ ምግብ የለም” የሚለው ወጣቱ፤ በቀን የሚያገኛትን 60 እና 70 ብር እንደምንም አብቃቅቶ ቤተሰቡን ከረሃብ እንደሚታደግ ነው የገለፀው፡፡ ግን በዚህ ሁኔታ እስከ መቼ እቀጥላለሁ በማለት ይጠይቃል፡፡ እናም ቀድሞ በጣሊያን አድርጐ እንግሊዝ ሃገር የገባ አብሮ አደጉ አሁን እስከ ሱዳን ሊያደርሰው የሚችል ገንዘብ እንደላከለትና በዚያም አስፈላጊውን የጉዞ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡ ባለፈው ሳምንት የ7ቱን አብሮ አደግ ጓደኞቻቸውን ሞት የተረዱት የአባኮራን ሰፈር ወጣቶች፤ ክፉኛ አዝነው የነበረ ቢሆንም አብዛኞቹ ግን ከአገር የመውጣት ከፍተኛ ጉጉት እንዳላቸው ገልፀውልናል፡፡ “እዚህ ሃገር 24 ሰዓት ቢሠራ ጠብ የሚል ነገር የለም” የሚሉት ወጣቶቹ፤ ከሃገር ከተወጣ ግን በተጨባጭ መለወጥ እንደሚቻል ከዚህ ቀደም የሄዱ ጓደኞቻቸውን በምሳሌነት እየጠቀሱ ያስረዳሉ፡፡ በሳሪስ አቦ አካባቢ በሊስትሮ ስራ የተሠማራው ጋዲሣ፤ ከትውልድ ሀገሩ አምቦ ወደ አዲስ አበባ የመጣው በመዲናይቱ ሰርቶ ለመለወጥ የሚል ዓላማ አንግቦ ሳይሆን ፓስፖርት ለማውጣት ነው፡፡ ፓስፖርቱን ከ4 ወራት በፊት ማውጣቱን የሚናገረው ወጣቱ፤ አሁን ደግሞ የሱዳን ቪዛ ለማግኘት
እየጣረ መሆኑን ይገልፃል፡፡ “በአይኤስ አሸባሪ ቡድን ስለታረዱትም ሆነ በሜዲትራኒያን ባህር ስለሰመጡት ሰዎች በሚገባ ሰምቻለሁ፤ መስቀል አደባባይ አይኤስን ለማውገዝ በተጠራው ሠልፍ ላይም ተሳትፌያለሁ፤ ግን ወደ አውሮፓ በየትኛውም መንገድ የመሄድ ሃሳቤን አልሰረዝኩም። ምክንያቱም እዚህ ጠብ የሚል ነገር የለም፤ ጓደኞቼ የደረሱበት ደረጃ መድረስ እፈልጋለሁ” ሲል ዓላማውን ገልጿል፡፡ ከቴክኒክና ሙያ በአውቶ ኤሌክትሪሲቲ በሠርተፍኬት መመረቁን የሚናገረው ጋዲሳ፤ እንግሊዝ ወይም ፈረንሳይ ቢገባ በተማረው ሙያ ስራ ሊያገኝ እንደሚችል ተስፋ ያደርጋል፡፡ ከሁለት አመት በፊት በጣሊያን አድርገው እንግሊዝ የገቡ ሁለት አብሮ አደጐቹ በተማሩበት የመካኒክ ዘርፍ በጋራዥ ውስጥ ተቀጥረው እየሠሩ መሆኑን እንደነገሩት የጠቀሰው ወጣቱ፤ ጓደኞቹ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥም ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ መላክ እንደጀመሩ ይናገራል፡፡ የተወሰነ ለጉዞው ጉዳይ ማስፈፀሚያ የሚሆን ገንዘብም ለእርሱ እንደላኩለት ገልጿል፡፡ እናትና አባቱ ከሞቱ በኋላ ከሶስት ወንድሞቹ ጋር የተካፈላትን ውርስ ሸጦ ለጉዞው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሟላት ማሰቡንም ይናገራል፡፡ በጉዞህ ላይ አደጋ ቢያጋጥምህስ? በሚል ሲጠየቅ፤ “እሱ የእድል ጉዳይ ነው፤ እድሌን እሞክራለሁ” ባይ ነው፡፡ በሌላ በኩል በ2006 ዓ.ም ከሣኡዲ በተባረሩ ኢትዮጵያውያን ዙሪያ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ የሚንቀሳቀሰው የክርስቲያን ተራድኦ በጎ አድራጎት ድርጅት (CCRDA) ተመላሾቹ ስላሉበት ሁኔታ የሚገመግም የጥናት ሰነድ ሰሞኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የሣውዲ ተመላሾች ተመልሰው ከሃገር መሰደዳቸው ተጠቁሟል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ተጋባዥ ከነበሩ ጥቂት ተመላሾች መካከልም ሁለት ወጣቶች አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለተሰብሳቢው ገልፀው ነበር፡፡ ሣውዲ አረቢያ በሰው ቤት ለሁለት አመት ተቀጥራ ትሠራ እንደነበር የገለፀችው በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ዘይነብ፤ ለሁለት አመት የሠራችበት ደሞዟን ተከልክላና ተባራ ጐዳና ወድቃ የነበረ ባዶ እጇን ወደ ሀገሯ እንደተመለሰችም ትናገራለች፡፡ በወር 700 ሪያል እንደሚከፈላት ተዋውላ ትሠራ እንደነበር የገለፀችው ዘይነብ፤ ሣውዲ ለሁለት አመታት የደከመችበት ወደ 16ሺህ ሪያል ገደማ ሣይከፈላት ባዶ እጇን ከተመለሰች በኋላ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አስጠግቷት ለአንድ አመት እንደተንከባከባትና ከአንድ አመት በኋላ በምግብ ስራ ሙያ አሠልጥኗት ከ8 ሺህ ብር በላይ አውጥቶ የማብሰያ ማሽን ገዝቶ በመስጠት “በዚህ ስሪና ራስሽን ለውጪ” እንዳላት ተናግራለች፡፡ ይሁን እንጂ ዘይነብ ማሽኑን ታቅፎ ከመቀመጥ ውጪ ሥራ ልትሠራበትና ህይወቷን ልታሻሽልበት አልቻለችም፡፡ “መንግስት የመስሪያ ቦታ ሊሠጠኝ ፍቃደኛ ባለመሆኑና የንግድ መነሻ የሚሆን ገንዘብም ማግኘት ባለመቻሌ ዝም ብዬ ተቀምጬአለሁ” ብላለች፡፡ “በወጣትነቴ የሰው ጥገኛ ሆኜ መኖሬ ያሳስበኛል” ስትል የምታማርረው ዘይነብ፤ በሳውዲ ብዙ ግፍና መከራ የደረሰባት ቢሆንም አሁንም እድሉን ብታገኝ ወደዚያው አሊያም ወደ ሌላ ሀገር ከመሄድ ወደ ኋላ እንደማትል ገልፃለች፡፡ ሀገር ቤት ባለው ሁኔታ ተስፋ መቁረጧንም ወጣቷ በምሬት አስረድታለች፡፡
ሣውዲ እያለች ልጆቿን ጥሩ ትምህርት ቤት ታስተምር፣ ቤተሰቦቿንም በሚገባ ትረዳ እንደነበር ያወሳችው ሌላኛው ወጣት በበኩሏ፤ በአሁን ሰአት ከልጆቿ ጋር የቤተሰቦቿ ጥገኞች ለመሆን እንደተገደዱ ትገልፃለች፡፡
“በቴሌቪዥን ስጠየቅ በሃገር ቤት ሠርቶ መለወጥ ይቻላል ብዬ ነበር” ያለችው ወጣቷ፤ አሁን ግን ይሄን የማለት ድፍረት የለኝም ብላለች፡፡ መንግስት አደራጅቶና ብድር አመቻችቶ መለስተኛ የንግድ ስራ ከጓደኞቿ ጋር መጀመሯን እንዲሁም እዳቸውንም መክፈል መጀመራቸውን የጠቆመችው ወጣቷ፤ እዳቸውን እንኳ ሳይጨርሱ የ5ሺህ ብር ግብር እዳ አለባችሁ እንደተባሉ ተናግራለች፡፡ “በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ተመላሾች ሊቋቋሙና በሀገራቸው ሠርተው ሊለወጡ የሚችሉት?” ስትልም ትጠይቃለች፡፡በቤተሰቦቿ እጅ ላይ ተመልሣ መውደቋ ክፉኛ እንደሚያሳስባት የገለፀችው ወጣቷ፤ የቤተሰቦቿንም ሆነ የልጆቿን ህይወት ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስ የግዴታ ወደ ውጭ ወጥታ መስራት እንዳለባት ማመኗንና ለመሄድ አጋጣሚዎችን እየጠበቀች መሆኑን በምሬት ተናግራለች፡፡ በመድረኩ ላይ የታደሙት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ በበኩላቸው፤ መንግስት ስደቱን እያባባሱ ነው በሚላቸው ህገ ወጥ ደላሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን እንዲሁም ዜጐች በሀገራቸው ሰርተው የሚለወጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከወትሮው በተለየ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከመንግስት ጐን ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ መሣተፍ እንዳለበትም ተወካዩ አሳስበዋል፡፡ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ የማህበረሰብ ጥናት (ሶሺዮሎጂ) ባለሙያ በመሆን የሚሰሩት ዶ/ር ተካልኝ አባተ በበኩላቸው፤ አሁን ከመንግስት እየቀረቡ ያሉት ምክንያቶችና የመፍትሔ ሃሳቦች በቂም፤ አሣማኝም አይደሉም ይላሉ፡፡ “በሃገር ቤት ሠርቶ መለወጥ ይቻላል የሚለው የቀን ተቀን ዲስኩር አሠልቺ ከመሆን ያለፈ የግንዛቤ ለውጥ አያመጣም፣ መንግስት የፖሊሲ አማራጮቹን በሚገባ ማየትና መገምገም ይገባዋል” ብለዋል ምሁሩ፡፡ የማህበረሰብ ጥናት ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ጥልቀት ያለው ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉም መንግስት መጋበዝ
እንዳለበት ዶ/ሩ ይመክራሉ፡፡ አለማቀፉ የሰራተኞች ድርጅት (ILO) ከግንቦት እስከ ሐምሌ 2014 ወደ አገራቸው በተመለሱ ስደተኞች ላይ ያደረገው ጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው፤ ለስደታቸው መንስኤ ከሆኑ ምክንያቶች ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዘው የተሻለ ህይወትን ፍለጋ የሚደረገው ስደት ነው፡፡ በህገወጥ ደላሎች ጉትጐታ አማካኝነት የሚደረገው ስደት እጅግ አነስተኛ ቁጥር ያለው መሆኑን አመልክቷል፡፡ እንደ ILO ሪፖርት፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከስደት ተመላሾች ዳግም መሰደድ የሚፈልጉ ናቸው፡፡




Read 2638 times