Monday, 25 May 2015 08:30

ኢህአዴግ የተሳካ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረጉን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገንዘብ አቅም ተፈታትኖናል አሉ


ለ5ኛው አገራዊ ምርጫ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቁ  ትላልቅ ቢልቦርዶችና ፖስተሮችን በብዛት በመጠቀም ከተፎካካሪዎቹ ልቆ የታየው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ በምርጫ ቅስቀሳ በኩል እንደ ዘንድሮም ተሳክቶልኝ አያውቅም ብሏል - ከዕቅዱ 98 በመቶው ውጤታማ እንደሆነ በመግለፅ። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፤ ጠንካራ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ጠቁመው የበጀት እጥረት ያሰቡትን ያህል እንዳይሰሩ እንደተፈታተናቸው ተናግረዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ማስፈፀሚያ ብሎ ለኢህአዴግ ከ14ሚ. ብር በላይ፣ ለመድረክ 2.2 ሚ. ብር፣ ለኢዴፓ ወደ8 መቶ ሺ ብር፣ ለሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁ ወደ 8 መቶ ሺ ብር ገደማ በጀት እንደመደበላቸው ይታወቃል፡፡  
ለተወካዮች ምክር ቤት 165 እጩዎችን በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች ያቀረበው የኢትዮጵያውያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ)፤ ለምርጫው ወደ 1 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት ይዞ መነሳቱን ጠቁሞ አብዛኛውን ገንዘብ ለመኪና ላይ ቅስቀሳ፣ ለፖስተሮችና በራሪ ወረቀቶች እንዲሁም ባነሮች ዝግጅት ማዋሉን ገልጿል፡፡
የኢዴፓ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ወንደሰን ተሾመ፤ ፓርቲው እንግሊዝ ሀገር ከሚገኙ ደጋፊዎቹና አባላቱ የተሰበሰበውን 3 መቶ ሺህ ብር እንዲሁም ከምርጫ ቦርድ የተመደበለትን  8 መቶ ሺህ ብር ሙሉ በሙሉ ለምርጫው ማስፈፀሚያ እንደተጠቀመበት አስታውቀዋል፡፡
ኢዴፓ ከ1 ሚሊዮን ኮፒ በላይ በራሪ ወረቀቶች አሳትሞ መበተኑን የጠቆሙት አቶ ወንድወሰን፣ ለእጩ ተወዳዳሪዎች ለእያንዳንዳቸው 300 የሚደርሱ ፖስተሮች አዘጋጅቶ ማሠራጨቱን ገልፀዋል፡፡ ከፖስተሮችና በራሪ ወረቀቶች በተጨማሪ ባነሮችን አሠርቶ በተለያዩ አካባቢዎች ሰቅሎ እንደነበር የተናገሩት አቶ ወንደሰን፤ ባነሮቹ ባልታወቀ ሁኔታ ከቦታቸው መነሣታቸውንና አብዛኞቹ ፖስተሮችም ተቀዳደው መገኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢዴፓ የቢል ቦርድ ማስታወቂያ ለመጠቀም ቢያስብም በገንዘብ አቅም ማነስ መተግበር እንዳልቻለም ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ “አንድ ቢልቦርድ ለማሰራት ከ70ሺህ ብር በላይ ያስፈልጋል፤ ፓርቲው ደግሞ ይህን የማድረግ አቅም አልነበረውም” ብለዋል አቶ ወንድወሰን፡፡
139 እጩዎችን ለፓርላማ ያቀረበው ሠማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ ምርጫ ቦርድ ከሠጠው 800ሺህ ብር በተጨማሪ ወደ 1.2 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት ይዞ ቅስቀሳውን እንዳከናወነ ጠቁሟል፡፡ ከመኪና ላይ ቅስቀሳ ባሻገር ባነሮችን፣ ፖስተሮችንና በራሪ ወረቀቶችን እንዲሁም የተወሰኑ ቢልቦርዶችን በመትከል ቅስቀሳ ማድረጉንም የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው በተለያዩ ቦታዎች ቢልቦርድ ለመስቀል ሞክሮ ችግር እንደገጠመው የገለፁት ኃላፊው፤ “ከክፍለ ከተማ ፍቃድ አምጡ” የሚሉ ምክንያቶች የታሰበውን ያህል ቢልቦርድ እንዳንሰቅል አድርጎናል ብለዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ አዲስ ከተማና ኮተቤ ላይ ብቻ ወደ 10 የሚሆኑ ቢልቦርዶችን ለመትከል እንደቻሉ ሃላፊው ገልፀዋል፡፡
ፓርቲው ለአንድ እጩ እስከ 2ሺህ የሚደርሱ ፖስተሮችን ማሠራጨቱን የጠቆሙት አቶ ዮናታን፤ ወደ 1.5 ሚሊዮን በራሪ ወረቀቶች መበተናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው ለድረ ገጽ የምረጡኝ ቅስቀሳም ከ10ሺህ ብር በላይ ማውጣቱን ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ለ3 ተከታታይ ቀናት በ8 ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ሁሉም ክ/ከተሞች ቀኑን ሙሉ መቀስቀሱንና በክልል ከተሞችም በቂ የመኪና ላይ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን አክለው ገልፀዋል፡፡
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 270 እጩዎችን ያቀረበው መድረክ፤ ከምርጫ ቦርድ ከተሰጠው 2.2 ሚሊዮን ብር ውስጥ ወደ 700 ሺህ ብር ገደማ ለመኪና ላይ ቅስቀሳዎች ማዋሉን ጠቁሟል፡፡ የቀረውን ገንዘብ ለምርጫ ታዛቢዎች የውሎ አበል በነፍስ ወከፍ 50 ብር እንዲከፋፈል መደረጉን የመድረክ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንዳሻው ገልፀዋል፡፡
“መድረክ ሊሰራ ካሰበው አንፃር የገንዘብ አቅሙ የጠብታ ያህል ነው” ያሉት ኃላፊው፤ የገንዘብ ችግሩን ለመቅረፍ እያንዳንዱ እጩ የራሱን ወጪ በግሉ መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በራሪ ወረቀቶች ማሰራጨቱን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በኦሮሚያ ክልል ብቻ በኦፌኮ አማካኝነት ወደ 5 ሚሊዮን በራሪ ወረቀቶች ተበትነዋል ብለዋል፡፡ በሌሎች ክልሎችም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቅስቀሳ በራሪ ወረቀቶች መሰራጨታቸውን ተናግረዋል፡፡
“መድረክ ያሰበውን ያህል ቅስቀሳ እንዳያደርግ የፋይናንስ እጥረት ተግዳሮት ሆኖበታል” ያሉት አቶ ጥላሁን፤ በዚህም ምክንያት ቢልቦርድ ማዘጋጀት አልተቻለም ብለዋል፡፡
501 እጩዎችን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በበኩሉ፤ እስካሁን ለቅስቀሳ ስራ ያወጣው አጠቃላይ ወጪ በትክክል እንደማይታወቅ ጠቁሞ ፓርቲው ከምርጫ ቦርድ የተመደበለትን 14 ሚሊዮን ብር ገደማ፣ ከአባላት ከተሰበሰቡ መዋጮዎች ጋር በማጣመር ስኬታማ የቅስቀሳ ስራ መስራቱን አስታውቋል፡፡
በ2002 ምርጫ ከቅስቀሳ ዕቅዳችን 70 በመቶ ብቻ ነበር ያሳነካው ያሉት የኢህአዴግ ፅ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው በዘንድሮ ምርጫ 98 በመቶ ውጤታማ ቅስቀሳ አድርገናል ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ ቢልቦርዶችን፣ በየአካባቢው የሚደረጉ ህዝባዊ ስብሰባዎችን፣ ፖስተሮችን እንዲሁም፣ የመኪና ላይ ቅስቀሳዎችን በማከናወን ሁሉንም አማራጮች አሟጦ መጠቀሙንና ለህዝቡ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ መሆኑን አቶ ደስታው አክለው ገልጸዋል፡፡ 

Read 1477 times