Monday, 25 May 2015 08:32

የኢህአዴግ አንጋፋ ባለስልጣናት ከዋናዎቹ ተቃዋሚዎች ጋር ተፋጠዋል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(6 votes)

በዘንድሮው 5ኛ አገር አቀፍ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን በቦሎሶሶሬ ሁለት ምርጫ ክልል ከሰማያዊ ፓርቲ እና ከአዲስ ትውልድ ፓርቲ  እጩ ተወዳዳሪዎች ጋር ይፎካከራሉ፡፡ በክልሉ የመድረክ እጩ የነበሩት አቶ ተስፋ ኃይሌ ከምርጫው ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ በ2002 ምርጫ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በተወዳደሩበት የአድዋ ከተማ ምርጫ ክልል ደግሞ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ከመድረክ እጩ ጋር የሚወዳደሩ ሲሆን፤ የመድረኩ ዶ/ር መረራ ጉዲናም በኦሮሚያ ምዕራብ ሸዋ ቶኬ ኩታዬ አምቦ 2 ምርጫ ክልል ከኢህአዴግ ኦህዴድ እጩ ጋር እንደሚወዳደሩ ታውቋል፡፡ በዚሁ ክልል አርሲ ዞን ኢታያ ምርጫ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ ከአንድነትና ከአትፓ እጩ ተወዳዳሪዎች ጋር ይፎካከራሉ፡፡ በአማራ ክልል ምዕራብ ጐጃም ዞን ጢስአባይ ምርጫ ክልል የኢዴፓው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ለምርጫ ይወዳደራሉ፡፡ በዚሁ አማራ ክልል ጐንጂ ምርጫ ክልል፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ የሚወዳደሩ ሲሆን በአዊ ዞን ቻግኒ ምርጫ ክልል ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከኢራፓና አንድነት እጩዎች ጋር ይፎካከራሉ፡፡  
ኢህአዴግን ወክለው ለዘንድሮው ምርጫ ከሚቀርቡት የአገሪቷ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኀኖም በትግራይ፣ ብዛት ምርጫ ክልል አረና መድረክን ወክለው ከሚወዳደሩት ከአቶ ኪዳነ አመነ ጋር ይፎካከራሉ፡፡
በመቀሌ ምርጫ ክልል ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማ ከአረና መድረክ እጩው ከአቶ ገብሩ አስራት እና ከኢዴፓ እጩ ጋር የሚፎካከሩ ሲሆን የአረና መድረክ እጩዋ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ ለክልል ምክር ቤት በዚሁ ምርጫ ክልል ይወዳደራሉ፡፡ በትግራይ፣ ሰለክላካ ምርጫ ክልል አቶ አባይ ፀሐዬ ኢህአዴግን ወክለው ከአረና መድረኩ እጩ ጋር ይፎካከራሉ ተብሏል፡፡
በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ምርጫ ክልል ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ከመኢአድና ከሰማያዊ ፓርቲ እጩዎች ጋር የሚወዳደሩ ሲሆን፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ፅሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን ደግሞ ከመድረክ እጩ ጋር ይፎካከራሉ፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል የመንግሥት ተጠሪ የሆኑት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ዞን በቅባት ምርጫ ክልል ብቸኛዋ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው ይቀርባሉ፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን በኦሮሬሳ ምርጫ ክልል ከመድረክ እጩ ጋር የሚፎካከሩ ሲሆን የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በሃዲያ ዞን ሶሮ 02 ምርጫ ክልል ከሰማያዊ እና መድረክ እጩዎች ጋር ይወዳደራሉ፡፡ በ1992 እና በ1997 ዓ.ም በተደረጉ ምርጫዎች አሸንፈው የፓርላማ አባል የነበሩት ታዋቂው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ መድረክን ወክለው በዚሁ በሃዲያ ዞን ሰቄ 02 ምርጫ ክልል ይወዳደራሉ፡፡ የቤቶችና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ፤ በክልሉ ጉራጌ ዞን እዥ 1 ምርጫ ክልል ከሰማያዊና ቅንጅት እጩዎች ጋር ይፎካከራሉ፡፡
በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ወ/ሮ አስቴር ማሞ ደግሞ በአዲስ አበባ ጨርቆስ ክፍለ ከተማ ይወዳደራሉ፡፡

Read 5541 times