Print this page
Monday, 25 May 2015 08:42

ተመድ የአንዳርጋቸው ጽጌን አያያዝ እየመረመርኩ ነው አለ

Written by 
Rate this item
(13 votes)

     የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙትን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አያያዝና የወቅቱን አጠቃላይ ሁኔታቸውን በተመለከተ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ማስታወቁን ዘ ጋርዲያን ትናንት ዘገበ፡፡
የተመድ የግርፋትና ስቃይ መከላከል ልዩ ክፍል ባልደረባ የሆኑት ጁአን ሜንዴዝ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በየመን አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የተደረጉት አቶ አንዳርጋቸው፣በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ሁኔታና አያያዛቸውን እየመረመሩ እንደሚገኙ ለእንግሊዝና ለኢትዮጵያ መንግስታት በጻፉት ደብዳቤ አሳውቀዋል ያለው ዘገባው፤ግለሰቡ እንቅልፍ እንዳያገኙ ተደርገዋል፣ ለብቻቸው ታስረዋል የሚሉ ክሶች እየቀረቡ እንደሚገኙም አስታውሷል፡፡
ተቀማጭነቱ በለንደን የሆነውና በመላ አለም የሞት ፍርድ የተጣለባቸውን እንግሊዛውያን ሁኔታ የሚያጠናው ሪፕራይቭ የተባለ ተቋም የአጣሪ ቡድን ዳይሬክተር ማያ ፎኣ በበኩላቸው፣ አቶ አንዳርጋቸው በህገወጥ በመንገድ መያዛቸውንና ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸውን ጠቅሰው፣ ለአንድ አመት ያህል ባልታወቀ ቦታ ታስረው እንደሚገኙና ተመድም የአቶ አንዳርጋቸውን አያያዝ ለማጣራት መወሰኑ አግባብነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የእንግሊዝ መንግስት ለጉዳዩ የበለጠ ትኩረት በመስጠት ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባዋል ያሉት ዳይሬክተሯ፣ አቶ አንዳርጋቸው አለማቀፍ ህጎችን በሚጥስና አብዛኛዎቹን የፍትህ መርሆዎች ባላከበረ መልኩ በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው ግለሰቡ በአፋጣኝ ከእስር እንዲፈቱ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የአቶ አንዳርጋቸው ጠበቃ የሆኑት ቤን ኩፐር በበኩላቸው፤ግለሰቡ በህገወጥ መንገድ በሌሉበት በተላለፈባቸው የሞት ቅጣት ያለአግባብ መታሰራቸውንና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮም የተመድን የምርመራ ጅምር በመከተል ከእስር የሚለቀቁበትን ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በለንደን የሚኖሩት የአቶ አንዳርጋቸው ባለቤት የሚ ሃይለማርያም በበኩላቸው፤ ባለቤታቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ጊዜ አንስቶ አንድ ጊዜ ብቻ በስልክ እንዳነጋገሯቸውና የት ቦታ ታስረው እንደሚገኙ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ፤ ግንቦት ሰባት በአገሪቱ ፓርላማ በአሸባሪነት የተመዘገበ ድርጅት መሆኑንና ዋና ጸሃፊው የነበሩት አቶ አንዳርጋቸውም በአገሪቱ ሽብርና ብጥብጥ እንዲፈጠር በማሴርና ሽብርተኞችን በኤርትራ ውስጥ በማሰልጠን፣ በፋይናንስ በማገዝና በማቀናጀት ስርአቱን ለመናድ በማቀድ ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ በመሆናቸው የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸው አስታውቋል፡፡ የእንግሊዙ ጠ/ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በቅርቡ ለኢትዮጵያ አቻቸው ለጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጻፉት ደብዳቤ፤ ግለሰቡ ከእስር እንዲፈቱ ቢጠይቁም አዎንታዊ ምላሽ አለማግኘታቸውን በቅርቡ መዘገባችን ይታወቃል፡፡

Read 3483 times
Administrator

Latest from Administrator