Tuesday, 26 May 2015 08:36

አዲስ ፍኖት

Written by  ሶፎንያስ መሐመድ
Rate this item
(9 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)

   ፍቅሯ ስላልወጣልኝ በአቋሜ ልፀና አልቻልኩም።

ሌላ ጊዜ ጥቂት ቆይታ ደግሞ “ለጥፋቴ ይቅርታ ጠይቄ የለ? … ግንኙነታችንን ብንቀጥልና ባሌ ብትሆን ደስ ይለኝ ነበር፡፡ እንዲህ የምጠይቅህ ለሌላ ሳይሆን ስለምትወደኝ ነው፡፡”

ፍቅር እንደገና!

*         *         *

ላንቺ፡-

ስሜቴን መካድ እችላለሁ?! … በስሜት የመኖር እንጂ ስሜት የመካድ ተሰጥኦ የለኝም፡፡ ግልጽ ነው፡፡ … ወድጄያለሁ! …. ወድጄና ፈቅጄ ተንበርክኬያለሁ። በእርግጥ እስከ ምን እንደምድህ አላውቅም። ብዙ በመዳህ ጉልበትና ልቤ የተላጠበትን ዘመን አልረሳሁም፡፡ ቁስሉ አሁንም ልቤ ላይ ይሰማኛል። እና ከእንግዲህ ብዙ የመዳህ አቅም ያለኝ አይመስኝም፡፡ አቅሜን ጨርሰሽዋል ሊያ!! ጨ… ር…. ሰ….ሽ…ዋ….ል!!

እወድሻለሁ ወድሻለሁ እወድሻለሁ እወድሻለሁ እወድሻለሁ

ልክድሽ አልችልም …

መዝሙሬ ነበርሽ፡፡ ቋንቋዬም ነበርሽ፡፡ የምዘምረው ስላንቺ ነበር፡፡ የምግባባው ባንቺ ነበር። መልኬን አውቆ፣ ስምሽን የማያውቅ ጥቂት ነበር፡፡ ባልንጀሮቼ ጓደኛችን ነው ብለው እንጀራ ሲያጎርሱኝ፤ እኔ ካንቺ ጋር የምናብ እንጀራ እቆርስ ነበር፡፡ በፍቅር የወዛ፣ በክብር የራሰ እንጀራ ስታጎርሺኝ አልም ነበር። በእርግጥም ህልም ነበር፡፡

ጓደኛ ሁነን ብለው ይመጣሉ፡፡ ስለአንቺ ወዳጅነት ተሰብከው ይመለሳሉ፡፡ ወዳጅነቴን ፈልገው ስለ ወዳጄ ይጠመቃሉ፡፡ ሊያ ልክ ነሽ፤ ክፉ ነበርኩ፡፡ አንቺን እንጂ ሌሎችን አላይም ነበር። አንቺን ለማጽናት ለሌሎች የታወርኩ ክፉ ነበርኩ፡፡ አይኔም ልቤም የተከፈተው ላንቺ ብቻ ነበር፡፡ …

እዘፍንሽ ነበር ሊያ!

እዘምርሽ ነበር!

ወጌ ነበርሽ ሊያ!

እተርክሽ ነበር!

ሁሉ እንዳይሆን ሊሆን …

ግን ህይወት በተዓምር ጢቅ ያለች ናት፡፡ በህይወት ለመቆየት ስል የጣመነ ስጋዬንና የዛለች ነፍሴን ይዤ ከሸሸሁ፤ ፍቅሬን አፈር አልብሰሽ ካዳፈንኩ በኋላ፤ ይሄው ትንሳኤ መጥቷል፡፡

ፍቅሬ አላዛርን ሆኗል፡፡ አፈሩን አራግፎ ሲንቀሳቀስም ይታየኛል፡፡

ግን እፈራለሁ፡፡ …

እፈራለሁ ሊያ …

እፈራለሁ …

እፈራለሁ …

እባብ ያየ በልጥ አበረየ አይነት፡፡

ትላንት የቆሰለ ዛሬ ይደነብራል አይነት፡፡

ነገ ከወደቅክ መቼም አትራመድ አይነት፡፡

እፈራለሁ …

እፈራለሁ ሊያ …

ስወድ በሙሉ ልብ ነው፡፡ ስወድ እስከ ጥግ ነው፡፡ እንደ ፊኛ … እንደ ባሉን ልቤ ውጥር ብላ፡፡ … ውስጧን ፍቅር ሞልቷት፡፡ እና ፊኛ ወይም ባሉን በትንሽ ስንጥር ይተነፈስ የለ? … ሙሽሽ ጥፍት ይል የለ … እንደዛው ህልውናዬን አጣለሁ፡፡ የኑሮ ምህዋሬ ይበዛል፡፡ እሸነቆራለሁ፤ እጎድላለሁም፡፡

ያኔም የሆንኩት እንደዝዚህ ነው፡፡

ለምን እንደሆነ እንጃ አሁንም እፈራለሁ። ውሸት በላዬ ላይ ሲኖር የማልችለውን ያህል መዋሸትም አልችልም፤ እመኝኝ ተመልሼ መዳፍሽ ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ እኔ እርግብ ነኝ፡፡ … ወደ ከፍታ ልታበሪኝ ነው? … ጨፍልቀሽ ልትገይኝም ትችያለሽ!

የምለምንሽ እንድታኖሪኝ ነው፡፡

እና ደግሞ ናፍቄሻለሁ …

ንፍቅ!

ለአንባቢ፡-

የኔና የሊያ ፍቅር ከትቢያ ተነስቶ አቧራውን ገፈፈ፡፡ “ተሀድሶ” አካሄድን፡፡ ፍቅር ብቻ ሣይሆን ማንነታችንም ተሀድሶ ያካሄደ ይመስል እንደ ቸኮሌት ጣፋጭ የሆነ ግዜ ማሳለፍ ጀመርን፡፡ ዘመኑ ራሱ ዘመነ ተሀድሶ (Renaissance period) መሰለኝ፡፡ ይሄ ያለፈ ዘመን በየት በየት ዞሮ መጣ ባካችሁ?! … የፍቅር የማንነትና ተሀድሶን በአንድ ረድፍ ተሰልፎ ያየሁ ያህል ተሰማኝ፡፡ እና ደስ አለኝ፡፡ ደስታ ውድ በሆነበት አገር በደስታ መኖር ከጥቂት ዕድለኞች ውስጥ እንደ አንዱ የሚያስቀጥር መሆኑን አመንኩ። ቀንና ሌሊቱን የላቀ ደስታ ሀሰሳ መንቀሳቀስ ጀመርኩ። የንጉሥ (አፄ ቴዎድሮስ) ሚስት ተዋበች፤ ንጉሱን “ታጠቅ” ብላ እንዳነሳሳችሁና አባ ታጠቅ የሚለው ተቀጽላ መለያቸውና መጠሪያቸው እንደሆነ ሁሉ፤ እኔንም ታጠቅ የምትለኝ ሴት ያለች መሰለኝ፡፡ ስሜን ጠርታ ታጠቅ ስትለኝ የሰማሁ መሰለኝ፡፡ እናም ለዚህም ደስታ ተሰማኝ፡፡ ከደስታ ወደ ደስታ መሻገር እጣፈንታዬ ወይም ዕድሌ መሰለ።

ይህን ያጣው ስንቱ ነው? ቁጥሩን መዘርዘሩ አድካሚና አሰልቺ ነው፡፡ ጥቂት የማይባል “በርካታ” በሚል ቃል የሚገለጽ መሆኑ ግን ዕውነት ነው፡፡ መቼም ሀገሪቱ ደስታ (እና ሣቅ) እንደ አልማዝ ውድ የሆነባትና ደስተኞች እንደ ጁፒተር የማይሰፍሩባት እንደሆነች ማወቅ ለኢትዮጵያዊያን የጥበብ መጀመሪያ ነው፡፡

እኔ ግን በየመዓልቱ ደስታን እንደ አስቤዛ ለመሸመት የታደለና በየሌሊቱ ሳቅ እንደ ሪችት መተኮስ የቻለ ዜጋ ሆንኩ፡፡ ሊያ የደስታዬ (እና የፍንደቃዬ)፤ የሣቄ እና (መፍነክነክያየ) ምንጭ ሆነች፡፡ የሣቅና የፈሽታ፤ የደስታና የሀሴት ወላድ! …

“ቀንና ሌሊቱን የላቀ ደስታ ሀሰሳ መንቀሳቀስ ጀመርኩ” ብዬ ነበር፡፡ ይሄ እውነት ነው፡፡

እንቅስቃሴውን የጀመርኩት ደግሞ ሊያን ለማስደሰት በመትጋት ነው፡፡ ስሜቷንና ፍላጎቷን ማጥናት ጀመርኩ፡፡ ትንሽ ነገር የሚያስደስታት (በደስታ ጣሪያ የሚያስነካት) እና ትንሽ ነገር የሚያስከፋት (በሀዘን ትቢያ የሚያለብሳት) ሴት መሆኗን አወቅሁ፡፡

እና እጠነቀቅላት ጀመር፡፡

በስሌት ወደ መኖርና በስልት ወደ መቅረብ ገባሁ፡፡ በመጨረሻም ስልቱና ስሌቱ ውጤታማ ሆነው አገኘሁ፡፡ እናም ተደሰትኩ፡፡

*   *   *

የፍቅራችን መደርጀትና መበጀት ምክንያቱ የኔ ጥረት ብቻ አልነበረም፡፡ ሊያም አለችበት፡፡ እንዲያውም የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው እሷ ናት፡፡ ባህሪዋን ለማረም ተግታለች፡፡ ጊዜ ልትሰጠኝና ልታስደስተኝ ጥራለች፡፡ ካለፈው ግንኙነታችን (ታሪካችን) ልምድ ሳትቀስም የቀረች አትመስልም። “አንድ ድንጋይ ሁለቴ ከመታህ ድንጋዩ አንተ ነህ።” የምለውን አባባል ምንነትና ትርጉም የተረዳች መስላለች፡፡ “ምንትስ በአንድ ጉድጓድ ሁለቴ አይገባም፡፡” ከሚለው አባባልም ትምህርት ወስዳለች፡፡

ለማንኛውም አብረው እንዳደጉ ሁለት የልብ ወዳጆች ለኔ ምቹ ሆና አግኝቻታለሁ፡፡ ውበትና ልስላሴ በቸረው ሶፋ ላይ ፈልሰስ ብሎ እንደመቀመጥ ወይም በኮንፈርት ተጠቅልሎ እንደመተኛት ምቾት ስጥታኛለች፡፡

አንዳንዴ ሳስበው ሊያን የሆነ መልአክ ለየት ያለ ሀሳብ ይዞ ከሰማይ በመውረድ አስተምሮ የለወጣት እንጂ በራሷ ጊዜ አገናዝባ የተለወጠች አይመስለኝም። እንዲህ ዓይነት ለውጥ በተለየ የመንፈስ ጫናና በልዩ መልዓክ እርዳታ ካልሆነ በስተቀር እውን የሚሆን አይመስልም፡፡

ሰው በአንድ ዓመት ውስጥ እንዲህ ይለወጣል?! ይህ ትንግርት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ፤ እባብም ዘንዶ የመሆን ዕድል አለው፡፡ እንዲህ ከሆነ፤ አይጥም ዝሆን የመሆን ተስፋ አላት፡፡ እንዲህ ከሆነ፤ ዝንጀሮም ሰው ለመሆን ቅርብ ነው፡፡ (አጋጣሚውን ካገኙ ማለቴ ነው፡፡ እንደዚያ፡፡ ወይም እንደዚያ የመሰለ ነገር!)

መሶብና ወሰከንቢያ ሆነናል፡፡ ማናችን መሶብ ማናችን ወስከንቢያ (ማን ከላይ ማን ከታች) እንደሆንን እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፤ ገጥመናል፡፡

እሷ ግጣሟን አግኝታለች፡፡

እኔም ግጣሜን አግኝቻለሁ፡፡

ላንቺ፡-

አሁን ፍርሃት የለብኝም፡፡

አሁን ስጋት የለብኝም፡፡

አልበሳጭም፡፡

አልናደድም፡፡

ብስጭትና ንዴትን እንደ በግ ቆዳ ከልቤ ላይ ገፍፌ ገንዳ ውስጥ ጥያለሁ፡፡ ተስፋ መቁረጥን ገርዤ ወደ ተስፋ ለውጨዋለሁ፡፡ ጨለምተኝነትን ገንዤ ቀብሬዋለሁ፡፡ የፊቴ ሰሌዳ ላይ ደስታ ቦግ ብሎ ይታያል፤ ተስፈኝነት በደማቁ ተጽፎ ይነበባል፡፡

ይህ ሁሉ የሆነው ባንቺ ምክንያት ነው፡፡

ወደ ህይወት መልሰሽኛል ሊያ! …

ኑሮን አስጀምረሽኛል!

ከደስታ ጋር ጉንጭ ለጉንጭ አሳስመሽኛል ሊያ!…

በተስፋ የታጨቀና ኃይል የተሞላ ወጣት አድርገሽኛል! …

አንቺ ባትደርሽልኝ ፍጻሜዬ ይሆን ነበር፡፡

ህይወት እንደሞት አስጠልታኝ ነበር፡፡

ሞት እንደ ገነት ናፍቆኝ ነበር፡፡

ግን ተመስገን፤ ሁሉ ባንቺ ተቀለበሰ፡፡

ለአንባቢ፡-

“ጨምሯል ፍቅር ጨምሯል፡፡

ጨምሯል ፍቅር ጨምሯል፡፡” እያሉ ወዳጆቹ የሚያንጎራጉሩለትና እሱ ራሱም መልሶ የሚያንጎራጉር ሰው ሆንኩ፡፡ መዋቅራችን ግዝፈቱ እንደ ዝሆን፤ ቁመቱ እንደ ግመል ሆነ፡፡

ፍቅራችን ከኛም አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ፤ ሌሎችንም የሚማርክና የሚያስቀና ሆነ፡፡ ከአዲስ አበባ ህዝብ  አንድ ሶስተኛው አጀብ ሲልልን፤ ሩቡ ሲቀናብን፤ ኩርማኑ ሲደሰትልን፤ የተቀረው ሲያደንቀን ከረመ፡፡

ላንቺ፡-

ብስል ትመስይኝ ነበር፡፡ ለካ ጥሬ ነሽ፡፡ ይሄንን በመሰለ ዓረፍተ ነገር በመጀመሬ አዝናለሁ፡፡ ግን ምርጫ የለኝም፡፡ እውነቱ እንደታሸ ሎሚ መፍረጥ አለበት። እውነታን በእውነትነቱ መቀበል ምርጫ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው፡፡ ስለዚህ ስሜቴን ልደብቅሽ አይገባም፡፡ በግልጽ እኮንንሻለሁ፡፡ “ወጉ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” ማለት ያንቺ ፈንታ ነው። ለእግዜርም ሆነ ለሰው ኩነኔ ከመሳቢያ ውስጥ የሚሳብበት ጊዜ አለ፡፡

ይሄው ላንቺም እጄ ከመሳብያው እጀታ ላይ የሚያርፍበት ጊዜ ደርሷል፡፡ ኩነኔን ለመታጠቅ አጥብቀሽ ተሰናጂ፡፡

ግን ምን ነው?

ምን ነው ሊያ? …

ነገሮች የሚገባት ሴት ናት ብዬ ስመሰክር፤ አስተዋይ ናት ብዬ አታሞ ሳስመታ፤ አዋቂ ነች ብዬ እምቢልታ ሳስነፋ፤ ትረዳኛለች ብዬ ከበሮ ስደልቅ … ምነው ሊያ?!

በተራ ወሬ ሰው ይዘጋል?! … በተራ ወሬ! እኔማ ወደ ኋላ ሄጄ ሳስብ ገርሞኝም አላባራ አለ፡፡ “እኔነቴን አልተቀበለችም ነበር ማለት ነው? “አልኩ፡፡

በማንነቷ የማታፍር፣ ኮርታ የምታስኮራኝ እንቁዬ ናት ብዬ ስተማመንብሽ መርጬ ባላመጣሁት ማንነት ስትርቂኝ ደነቀኝ፡፡

ለማንኛውም የኔ እምነት እንዲህ ነው፤ ከምንም ነገር በላይና ከምንም ነገር በፊት እኔ ሰው ነኝ፡፡ የምኮራውም ሆነ ልኮፈስ የምችለው በሰውነቴ ነው። በሌላ በኩል ልወገዝም ልጠላም የሚገባው ሰው ከመሆኔ ጋር የማይመጣጠን ማንነት ይዤ ብሆን ነው፡፡ እኔ ግን ሰው ከመሆን የማስቀድመው ምንም ነገር የለም፡፡

እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወራሽ ነበርኩ። ኃይማኖቴ ከቤተሰቦቼ የተወረሰ ነው፡፡ ብሄሬ ከቤተሰቦቼ የተወሰደ ነው፡፡ እነዚህን በራሴ ፈቃድ ላናገኛቸውምሆነ፤ ልፍቃቸው አልችልም፡፡

ለማንኛውም አንቺ የተከፋሽብኝና የዘጋሽኝ እኔ ልመርጥ በማልችለው ማንነቴ ነው፡፡ ስለዚህ ፍርዱ ከኔ ይልቅ አንቺን አንገት ወደ ማስደፋት ያዘነብላል፡፡

ለአንባቢ፡-

ከጉራጌ ማህበረሰብ ጀገር የሚባለው ጎሳ አባል ነኝ። በዚህ ጎሳዬ ምክንያት ገጠር ጥዬው የመጣሁ የመሰለኝ ግን የተከተለኝ ስያሜ ሰለባ ነኝ፡፡

በሰባት ቤት ጉራጌ ጅግሮ የሚታወቁት በተለየ ጉዳይ ነው፡፡ ደስ የሚል አይደለም፡፡ ግን እጠቅሰዋለሁ ማህበረሰቡ ጅግሮች ቡዳዎች ናቸው ብሎ ያምናል። እንደ ጅብ ሰው ይበላሉ፡፡ ጅብ ሆነው ሌሊት ሌሊት ይንቀሳቀሳሉ ወዘተ እየተባለ ይወራል፡፡ ይሄን ስም ገጠር ትቸው መጥቻለሁ ብዬ አምን ነበር፡፡ ነገር ግን እዚህ አዲስ አበባ የሚያውቁኝ (በጅግሮነቴ) ሰዎች ነበሩና “ቡዳነቴ” አልተረሳም፡፡

ሊያ ይህን ሰማች እና እንዳይበላይ ብላ ሸሸች። አዘንኩ!

ማገናዘብ የምትችል ናት ብዬ አስብ ነበር፡፡ እስከ ሁለተኛ ደረጃ የዘለቀው ትምህርቷ ከአሉባልታ እንድትፋታና ተጨባጭ እውነት ላይ ብቻ እንድታተኩር ያደርጋታል ብዬ አምን ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ 

ወሬውን በእርግጠኝነት አምና ወደእኔ መቅረብ ፈራች፡፡

በሆነው ሁሉ አዘንኩ፡፡

አንገቴን ደፍቼ አነባ ገባሁ፡፡

Read 4412 times