Saturday, 30 May 2015 11:44

“ምርጫው በተለያዩ ተፅዕኖዎች መሃል የተደረገ ነው” የአውሮፓ ህብረት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

 

 

 

“የዲሞክራቲክ ተቋማት አለመጠናከር በምርጫው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል” የአሜሪካ እምባሲ

 የዘንድሮውን ምርጫ የመታዘብ እድል ያላገኘው የአውሮፓ ህብረት፤ ምርጫው በተለያዩ ተፅዕኖዎች መሃል የተደረገ እንደነበር የገለፀ ሲሆን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ፤ ምርጫው ሰላማዊ ቢሆንም የዲሞክራሲ ተቋማት አለመጠናከር በምርጫው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል ብሏል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ ሃገሪቱ ሰላማዊ የምርጫ ሂደት ማስተናገዷን ጠቅሶ ከምርጫው በፊት የጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች መታሰር መታሰር እንዲሁም የጋዜጦችና መፅሄቶች መዘጋት፤ ፓርቲዎች በፖሊሲያቸው ላይ ሰፊ ክርክር እንዳያደርጉ እንቅፋት በመሆን በአጠቃላይ የምርጫው እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ምርጫ ቦርድ ላሳየው ትጋትና የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን ላቀረበው የትዝብት ሪፖርት እውቅና ሰጥቶ፣ በሃገሪቱ የሲቪክ ማህበራት ላይ የተጣለው ገደብ፣ የሚዲያ ነፃነትና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት በሚገባ አለመከበሩ አሳሳቢና በዲሞክራሲያዊ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

“ምርጫውን ለመታዘብ ፈልገን ተከልክለናል” ያለው ኤምባሲው፣ ሌሎች አካላትም ምርጫውን እንዳይታዘቡ መደረጉና የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች ምርጫውን በተገቢው ሁኔታ መታዘብ አለመቻላቸው በምርጫው የታዩ ጉልህ ግድፈቶች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡የአውሮፓ ህብረትም ሆነ የአሜሪካ ኤምባሲ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሰረት በማድረግ በአካባቢያዊና አለማቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጋር ለወደፊትም በጋራ እንደሚሰሩ በመግለጫቸው አስገንዝበዋል፡፡ የዘንድሮው ምርጫ ብቸኛ አለማቀፍ ታዛቢ ቡድን በመሆን የታዘበው በናሚቢያው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሄፊኬቱንዬ ፖሃምባ የተመራው የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድን ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ ምርጫው ተአማኒና ሰላማዊ ነው ቢልም በምርጫው እለት የታዘባቸውን ግድፈቶች በዝርዝር ገልጿል፡፡ ህብረቱ በሃገሪቱ ካሉት 45ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች በ356ቱ ብቻ 59 አባላቱን በማሰማራት መታዘቡን ጠቁሞ ከታዘባቸው ጣቢያዎች መካከል በ22.7 በመቶ በሚሆኑት የምርጫው እለት የቅስቀሳ መልዕክቶችና ፖስተሮች ሲሰራጩ እንደነበር፣ 23 በመቶ በሚሆኑት ደግሞ በምርጫ ጣቢያ ውስጥ ቅስቀሳ ሲካሄድ መታዘቡን ሪፖርት አድርጓል፡፡ ህብረቱ ከተመዘገበው መራጭ በላይ የምርጫ ወረቀት በኮሮጆ ውስጥ የተገኘበት የምርጫ ጣቢያ እንዳጋጠመውና የኮሮጆ ፍተሻ ሳይካሄድ ምርጫ የተጀመረባቸው ጣቢያዎችን እንደታዘበ ጠቁሟል፡፡ ህብረቱ ይፋ ባደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት፤ ጉድለቶች ቢኖሩም ምርጫው ሰላማዊ የተረጋጋና ተአማኒ እንደነበር የገለፀ ሲሆን ከሁለት ወር በኋላ ሙሉ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡

 

 

 

Read 3985 times