Saturday, 30 May 2015 12:25

‹‹ይህ ሰው የት ነበር?››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

     በዚህ እትም የምናስነብባችሁ አንድ ገጠመኝን ነው፡፡ በሕክምናው ዙሪያ ያጋጠማቸውን እውነታ ያወጉን አቶ አምቢበል ታረቀኝ ሲሆኑ የገጠመኙ ባለታሪክ ወ/ት ናርዶስ እምቢበልም የጠቀሰችውን ለንባብ ብለናል፡፡

‹‹...እንዲያው ይህ ሰው የት ነበር? ያሰኘኝ አንድ ነገር ነው፡፡ ልጄ በአንድ ወቅት ድንገት መነሳት መቀመጥ አቃተኝ ትለኛለች፡፡ እኔና ባለቤቴም በመጀመሪያ እቤት ውስጥ በጋለ ድንጋይ በፈላ ውሃ በመሳሰሉት ብናሞቃት ምንም ለውጥ አልተገኘም፡፡ በሁዋላም በወጌሻ አስሞከርናት፡፡ ወጌሻው አሁን ትድናለች እያሉ ለሰባት ቀን ወገብዋን እያገላበጡ እያሹልን ተሸክመን ወደ ቤት እናመጣለን፡፡ ነገር ግን እርስዋ ምንም ሊሻላት አልቻለም፡፡ ከዚያም ወደ ሐኪም ቤት መሔድን ተመካከርንና ወደሶስት የሚሆኑ የግል እና የመንግስት ጤና ተቋማት ወሰድናት፡፡ ሁሉም የተለያየ ምክንያት እየሰጡ መድሀኒት ያዙናል፡፡ ነገር ግን  መፍትሔ ሊሆን አልቻለም፡፡

አንዳንዶች ከጨጉዋራ ጋር ያያይዙታል፡፡ ሌሎች ደግሞ ጣፊያሽ ተቃጥሎአል በረሀ ነው እንዴ የምትኖሪው? ይላሉ፡፡ አንዱ ሐኪም ደግሞ ማህጸንሽን ተመርመሪ ኢንፌክሽን ሊሆን ይችላል አለ፡፡ ጭርሱንም ጉበትሽን ታዪ ጉበት ሳይሆን አይቀርም ያለን ሐኪም ተስፋ አስቆረጠን፡፡ ምክንያቱም ጉበትዋን እስክትታይ ድረስ በሚል የሰጣትን መድሀኒት ስትወስድ ሌሊቱን ሙሉ ተቃጠልኩ ስትል አሳደራት፡፡

እኔና ባለቤቴ ተመካከርን፡፡

በቃ ፡፡ ከዚህ በሁዋላ ወደ ሐኪም ቤት አንሞክርም፡፡ ጸበል ነው የምንወስዳት ብለን በሶውንም ዳቦቆሎውንም ማዘጋጀቱን ጀመርን፡፡ ለጸበሉም እጣ ስናወጣ አንዲት ጎረቤታችን የታማሚዋን ውሎ አዳር ለመጠየቅ አመሻሹ ላይ መጣች፡፡..

እንደምን አመሻችሁ?

እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ግቢ ግቢ...

እየተቀባበልን ጋበዝናት፡፡

ናርዶስ አንዴት ነች?

አረ ምንም አልተሸላት፡፡

ትንሽም አልተሸላት?

ጭርሱንም ብሶባታል፡፡

እንዴት?

በቃ፡፡ ሐኪሞቹ ምንም አላወቁላት፡፡ እኛም ሰለቸን፡፡

ምንድነው የተጠቀለለ ወረቀት ጠረጴዛውን የሞላው?

በቃ፡፡ ከዚህ በሁዋላ ሐኪም ምን ያደርግላታል፡፡ ያልወሰድንበት ቦታ የለም፡፡ ወጌሻው አልቀረ ሐኪሙ አልቀረ፡፡ ሁሉም ምንም መፍትሔ አልሰጡዋትም፡፡ ጭርሱንም እየባሰባት መጣ፡፡ ይኼው እንግዲህ ወደ ስድስት ወር ሆናት፡፡ እርስዋ ጭርሱንም ምግብ መብላት እያቆመች መጣች፡፡

ምን ታድርግ? መቀመጡ እያስቸገራት ነዋ፡-

አዎን ፡፡ እኛም ገብቶናል፡፡ አይዞሽ ...ምንም ችግር የለም ብንላትም ...እርስዋ ግን ልትቀበለው አልቻለችም፡፡

እና ታድያ ምን ልታደርጉ አሰባችሁ?

በቃ...ይኼው እንደምታይው እጣ ጥለን ወደ ጸበል ልንወስዳት እየተዘጋጀን ነው፡፡ እንዲያውም አንቺ እንኩዋን መጣሽ ...እጣውን ታወጪልናለሽ፡፡

ጥሩ፡፡ ነገር ግን እኔ እጣውን ከማውጣቴ በፊት አንድ እድል ይሰጠኝና ልሞክር፡፡

ምን ትሞክሪያለሽ?

ሐኪም ጋ ልውሰዳት፡፡

አይ...አይ...አይ...እኛ ስንት ጋ ወስደን የታከተንን ደግሞ አንቺ እንደገና ወደሐኪም ትወስጃለሽ? አይቻልም፡፡

እንዴ..እኔ እኮ ልጅቷ የልጆቼ ጉዋደኛ ...ባልወልዳትም ልጄ ነች፡፡ ስለዚህ ፍቀዱልኝ፡፡

የለም የለም አታሰናክይን፡፡ ይልቁንም እጣውን አውጭልን፡፡

ግድየለህም የናርዶስ አባት... ለአንድ ሁለት ቀን እኮ ነው፡፡ እናንተ ስንቃችሁን ልብሳችሁን እስክታዘጋጁ ድረስ እኔ በመሀከል ወደ ሐኪም ልውሰዳት እና ከውጤቱ      በሁዋላ ትወስዱዋታላችሁ፡፡

በዚህ መሀከል ባለቤቴ አስታራቂ ሆና ፈቀደችላት፡፡ ያች ሴትዮ በማግስቱ ከባለቤቷ ጋር ሆና በመኪናቸው ወደ ሐኪም ቤት ሲወስዱዋት ..አንድ ሰው ብቻ ታማሚዋን እንዲደግፋት ሰጠናቸው እንጂ እኛ አልተከተልናቸውም፡፡ ልጅትዋ ታክማ ስትመለስ ያየችውን እንዲህ ነበር ያወጋችን፡፡

...ወደ ሐኪሙ ጋ ስገባ ልክ አስቀድሞ ለብዙ ጊዜ እንደሚያውቀኝ ነበር ሰላምታው፡፡ እንደምንድነሽ ናርዶስ...? ሲለኝ ገና ልቤ ወከክ ነበር ያለው፡፡ እኔም ስቅቅ ብዬ ሳልቀመጥ እንደቆምኩ ...በማይሰማ ድምጽ...ደህና...ደህና ነኝ... ነበር ያልኩት፡፡ በእርግጥም እናንተ እንዳላችሁትም እኔም ወደ ሐኪም ጋ መሔድን ሰልችቼው ነበር፡፡ ያመጡኝን ሴት ማለትም የጉዋደኞቼን እናት አክብሬ እንጂ እኔም አምቢ ብል ደስ ይለኝ ነበር፡፡

ከዚያም...አይዞሽ አትፍሪ... ምንሽን ነው የሚሰማሽ? የሐኪሙ ጥያቄ ነበር፡፡ እኔም እንጃ...ከማህጸኔ ነው መሰል... መቀመጥ መተኛት አልቻልኩም... በማለት መለስኩለት፡፡ ማህጸንሽን ከአሁን ቀደም ታመሽ ታውቂያለሽ? ወይንስ በምን ጠረጠርሽ?

አ...አ...አይ... ሐኪሞቹ እንዲያውም ሌላም ሌም በሽታ ይኖርብሽ ይሆናል አሉኝ እንጂ በትክክል ይህ ነው በሽታሽ አላሉኝም፡፡ እስቲ ነይ እዚህ መተኛ ላይ... ብሎ ወደ መመርመሪያ አልጋው ሄድ አለ፡፡ ...እኔም በግድ ተነስቼ ከአልጋው ለመውጣት ሞከርኩ፡፡ ግን አልቻልኩም፡፡ ሐኪሙ ግን በጣም ደግና እሩህሩህ ስለነበር.. አይዞሽ ...እኔ እረዳሻለሁ ብሎ... ከመመርመሪያው አልጋ ላይ አሳረፈኝ፡፡ ከዚያም ምርመራውን ሲያደርግ... በማህጸኔም በመጸዳጃዬም በኩል ሲፈትሽ ሳላስበው ከልክ በላይ ጮህኩኝ፡፡ በቃ ተነሽ አለኝ እና ከአሁን በፊት ወድቀሽ ታውቂያለሽ አለኝ፡፡ አዎን ግን በጣም ቆይቶአል... አልኩት፡፡ ቢቆይም የህመምሽ ምክንያት እርሱ ነው፡፡ በዚያ ምክንያት መቀመጫሽ ወይንም ጭራሽ አካባቢ የተጎዳ ነገር አለ፡፡ ለማንኛውም ቀላል ነው፡፡ ይህንን መድሀኒት አሁኑኑ መውሰድ ጀምሪ ብሎኝ ተለያየን፡፡...

 የልጅቷ ታሪክ ይኼው ነው፡፡ ለስድስት ወር ያህል አልጋ ያልለቀቀች ልጅ ...መድሀኒቱን ስትወስድ በሶስት ቀን ተነስታ ወዲያ ወዲህ ማለት ጀመረች፡፡ እኔም በጣም አዝኜ... ሴትየዋን እግዚያብሄር ይስጥልኝ ከማለት ይልቅ እንደዚህ ያሉት ሐኪሞች ምናለ ብዙ ቢሆኑ? ለመሆኑ ይህ ሰው የት ነበር? ስል አፈጠጥኩባት፡፡.. የሚል ነው የአቶ እምቢበል ታረቀኝ ገጠመኝ፡፡

በሚቀጥለው እትም የህክምና ባለሙያዎች እውቀታቸውን ...ክህሎታቸውን እንዴት በየጊዜው ማደስ እንዳለባቸው ስለወጣው አሰራር የምናስነብባችሁ ይኖራል፡፡

 

Read 1410 times