Saturday, 06 June 2015 13:48

ሳውዲ ውስጥ መጥፋቷ የተገለጸው ወጣት ወደ አገሯ ልትመለስ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 አልስአማኤል በተባለ የውጭ አገር የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ በኩል ወደ ሳውዲ አረቢያ ከተላከች በኋላ ለ27 ወራት ያለችበት ሳይታወቅ ተሰውራ ቆይታለች የተባለችው ወጣት ወደ አገሯ ልትመለስ ነው፡፡
የሥራ ውሏ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጸድቆላት፣ በየካቲት ወር 2005 ዓ.ም ወደ ሳውዲ የተጓዘችው ሀያት አሊ መሀመድ፤ ከአገር ከወጣች በኋላ ከቤተሰቦቿ ጋር በስልክ ሳትገናኝ በመቅረቷ ቤተሰቦቿ ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ኤጀንሲው ወጣቷ ያለችበትን ሁኔታ ተከታትሎ እንዲያሳውቀው ያሳስባል፤ ኤጀንሲውም በክትትሉ ወጣቷ በሳውዲ ከተማ ውስጥ በሰላም እንደምትኖርና በሥራ ላይ መሆኗን በማረጋገጥ በስልክ እንድትገናኝ ከማድረጉም በላይ ለቤተሰቦቿ ገንዘብ እንድትልክ ማድረጉንም ገልጧል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ ወጣቷ የምትገኝበትን ሁኔታና አድራሻዋን የሚገልፅ መረጃ ለሠራተኛና ማኅበራዊ ሚኒስቴርና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማቅረቡን ጠቅሷል፡፡
ወጣቷ ከጥቂት ቀናት በኋላም ወደ አገሯ እንደምትመጣና የጉዞ ትኬቷ ኮፒ በእጃቸው ላይ እንደሚገኝ የኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች ጠቁመዋል፡፡
ሁኔታውን ለማጣራት ወደ ወጣቷ ቤተሰቦች ጋር ደውለን፣ ጠፋች ከተባለችው ልጃቸው ጋር በስልክ መገናኘታቸውን እርሷ መሆኗን ለማረጋገጥም እርሷ ብቻ የምታውቃቸውን አንዳንድ ነገሮች በመጠየቅ ማረጋገጣቸውን ጠቁመው፤ ወጣቷ በቅርቡ ወደ አገሯ እንደምትመጣ በኤጀንሲው የተነገራቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

Read 1599 times