Saturday, 06 June 2015 13:50

ታዋቂው የደቡብ ሱዳን ዐማፂያን መሪ በቤታቸው ሞተው ተገኙ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

አስከሬኑ ወደ ለንደን ተወስዶ እንዲመረመር ተጠየቀ

       በደቡብ ሱዳን ዐማፅያን ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት የነበራቸው ዋኒ ቶምቤ ላኮ በአዲስ አበባ በመኖርያ አፓርትመንታቸው ውስጥ ሞተው ተገኙ፤ ቤተሰቦቻቸው አስከሬናቸው ወደ ለንደን ተወስዶ እንዲመረመር ጠይቀዋል፡፡
በለንደን በስደት ይኖሩ የነበሩት ቶምቤ፤ ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በቀድሞው የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሬክ ማቻር የሚመራውን የመንግሥት ተቃዋሚ ቡድን ተቀላቅለዋል፡፡ በተቃዋሚው ቡድን ውስጥ የተለየ የኃላፊነተ ቦታ ባይሰጣቸውም ሚያዚያ አጋማሽ ላይ በተደረገው የዐማፅያኑ የከፍተኛ ኃላፊዎች ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የተቃዋሚው መሪ ሬክ ማቻር የቶምቤን ሞት ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፣ የእርሳቸው መሞት ለደቡብ ሱዳን፣ ለተቃዋሚ ቡድን እና ለቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ጉዳት እንደሆነ በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
የሞታቸውን መንስኤ በተመለከተ ከሐኪም የተሰጠ መረጃ ባይኖርም በቅርብ የሚያውቋቸው ጓደኞቻቸው በልብ ድካም ህይወታቸው አልፎ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የቶምቤ ቤተሰቦች በበኩላቸው፣ አስከሬናቸው ለንደን ሄዶ እንዲመረመር መጠየቃቸውን “ሱዳን ትሪቢዩን” ዘግቧል፡፡
ቶምቤ፣ በደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ በአሜሪካ፣ በካናዳ እና በአውስትራልያ በመዘዋወር ደቡብ ሱዳናውያን አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ለመጣል የትጥቅ ትግሉን እንዲቀላቀሉ ሰፊ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ይነገርላቸዋል፡፡

Read 2268 times