Print this page
Saturday, 06 June 2015 13:51

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት እና ሲቪል ሰርቪስን ጨምሮ በ19 ትላላቅ የመንግስት ተቋማት የወጪ ሂሳብ አሠራር ላይ ጉድለት ተገኘ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

 “የሬዲዮና የቴሌቭዥን ማሻሻያ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ሲገባቸው ገና አልተጀመሩም”
ዩኒቨርሲቲዎች ከበጀት በላይ ወጪ አድርገዋል ተባለ
               
    የብሔራዊ መረጃና ደህንነት እና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴርን ጨምሮ በ19 ትላልቅ የመንግስት ተቋማት ላይ በተደረገ የኦዲት ምርመራ፤ ጉድለት መገኘቱና ማስረጃ ሳይኖራቸው በመመዝገባቸው የወጪያቸውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ አለመቻሉን የፌደራል ዋና ኦዲተር ቢሮ አስታወቀ፡፡
የፌደራል ዋና ኦዲተር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የ2006 በጀት ዓመት ሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ይፋ እንዳደረገው፤ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት 273‚845‚378.34 ብር፣ እንዲሁምየሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር 110.930.205.38 ብር የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለበት ሂሣብ ተገኝቶባቸዋል፡፡ ሪፖርቱ ጉድለት ተገኘባቸው ባላቸው 19 ታላላቅ የመንግስት መ/ቤቶች በአጠቃላይ 473.469.940.34 መገኘቱንም አመልክቷል፡፡ ይህ የወጪ ማስረጃ ያልቀረበለት ሂሣብ በቂ ማስረጃ እንዲቀርብለት አሊያም ገንዘቡ ለመንግስት ካዝና ተመላሽ እንዲደረግና ለወደፊቱም ማንኛውም ወጪ ከመመዝገቡ በፊት ተገቢው ማስረጃ መቅረቡ እንዲረጋገጥ ማሳሰቡን በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል፡፡
የሬዲዮና የቴሌቭዥን ማስፋፊያና ማሻሻያ ፕሮጀክቶችንና ከአናሎግ ወደ ዲጂታል የሚደረገውን ሽግግር አፈፃፀም አስመልክቶ የፌደራል ዋና ኦዲተር ባቀረበው ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው፤ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ መርሃ ግብር መሰረት፤ ተጠናቆ ሥራ ሊጀምር ሲገባው፣
የህንፃ ግንባታውም ሆነ የዲጂታል ስርጭት ሽግግር ሥራው ገና አልተጀመረም፡፡ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ለሚደረገው የሽግግር ሥራ በፕሮጀክቱ ላይ ከተጠቀሰው 642 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ተጠቁሟል፡፡
በዓመቱ ከተደለደለላቸው በጀት በላይ ወጪ አድርገዋል ተብለው በኦዲት ሪፖርት ላይ ከተጠቀሱት የመንግስት ተቋማት መካከል የአዳማ፣ አዋሣ፣ ዲላ፣ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚገኙበትም ተገልጿል፡፡ የኦዲት ሪፖርቱ እንደገለፀው፤ ድርጊቱ የዘመኑን የፌደራል መንግስት አመታዊ ገቢና ወጪ ሂሳብ የተዛባ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ የመ/ቤቶቹ ትክክለኛ የፋይናንስ አፈፃፀምና ገጽታ እንዳይታወቅ ያደርጋል፡፡
የባቡር ፕሮጀክቶቹን አስመልክቶ በኦዲት ሪፖርቱ ላይ የቀረበው መረጃ እንደሚያመለክተው የባቡር ፕሮጀክቶቹ ሲተገበሩ ከኮንትራት ውሉ ውጪ ለሚጨመሩና ለሚቀነሱ ጉዳዮች ኮርፖሬሽኑ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጉዳዩን አቅርቦ እንዲፈቀዱ ማድረግ የሚገባው ቢሆንም ያለሚኒስቴር መ/ቤቱ ፈቃድ 1.841.401.000 ዶላር ጭማሪ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡

Read 3224 times