Saturday, 06 June 2015 13:52

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአፍሪካ ስኬታማ ኩባንያ ሽልማት ታጭቷል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አራት ታላላቅ የአፍሪካ ኩባንያዎች ለመጨረሻው ዙር ደርሰዋል

    የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም በአፍሪካ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ የሚገኙ ስኬታማ ኩባንያዎች  በማለት ለመጨረሻው ዙር ከመረጣቸውና ለቀጣዩ ሽልማት ካጫቸው አራት ግዙፍ የአህጉሪቱ አየር መንገዶች አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ፎረሙ ከአፍሪካ አልፈው በአለማቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚው ዘርፍ መሪ የመሆን አቅም ያላቸው የአህጉሪቱ ኩባንያዎችን ለመምረጥ ባከናወነው ሂደት፣ ለመጨረሻው ዙር የደረሱትን 4 የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ኩባንያዎች ዝርዝር ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ባካሄደው ጉባኤው ይፋ አድርጓል፡፡ ለመጨረሻው ዙር በዕጩነት የቀረቡት አራቱ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የዝምባዌው የንግድና የሆቴል ኢንቨስትመንት ኩባንያ ሜክሌስ፣ የደቡብ አፍሪካው ሲሚንቶ አምራች ፒፒሲ እና የናይጀሪያው ነዳጅ አምራች ኩባንያ ዋልተርስሚዝ ፔትሮማን ኦይል ናቸው፡፡
በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የኒው ሻምፒየንስ ማኔጂን ዳይሬክተርና ሃላፊ የሆኑት ዴቪድ አኪማን በጉባኤው ላይ ባሰሙት ንግግር፣ ፎረሙ ሃላፊነት የሚሰማው የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ፣ የስራ ዕድል በመፍጠርና የስራ ፈጠራን በማስፋፋት ረገድ በአፍሪካ በግንባር ቀደምትነት ለሚመሩት ለእነዚህ አራት ኩባንያዎች እውቅና በመስጠቱ ኩራት ይሰማዋል ብለዋል፡፡
ኩባንያዎቹ በትርፋማነት እድገት፣ በፈጠራ የታገዙ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ተግባራዊ በማድረግና አመራር በኩባንያዎች እንቅስቃሴ ላይ ያለውን ሚና በተግባር በመግለጽ ረገድ በአህጉሪቱ የላቁ ሆነው በመገኘታቸው ለመጨረሻው ዙር መብቃታቸው ተገልጧል፡፡
በመጪው መስከረም ወር በቻይና በሚካሄደው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የኒው ሻምፒዮንስ አመታዊ ጉባኤ ላይ በሚከናወን ስነስርዓት ከአራቱ ኩባንያዎች አሸናፊው ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

Read 2197 times