Print this page
Saturday, 06 June 2015 13:54

ፕ/ር መርጋ በቃና “በአመራርነቴ መቶ በመቶ ውጤታማ ነኝ” አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  በቦንጋ ገዋታ ጊምቦ ምርጫው ሰኔ 7 ይደረጋል
“ኢህአዴግ መቶ በመቶ አላሸነፈም”
         
   በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና፤ በምርጫ ቦርድ አመራርነታቸው መቶ በመቶ ውጤታማ እንደሆኑና በብቃት ቦርዱን እየመሩ እንደሚገኙ ለጋዜጠኞች ገለፁ፡፡
ፕሮፌሰሩ ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ “በአመራር ብቃትዎ ላይ ጥያቄ ይነሳል” በሚል ለተነሳ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ወደ ምርጫ ቦርድ አመራርነት ተፈልገው እንደመጡ ጠቁመው በእውቀታቸውም ቢሆን በቂ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እውቀቴ ጠባብ አይደለም ያሉት ፕ/ር መርጋ፤ በሣይንስ ያልደረስኩበት አለም የለም ብለዋል፡፡ “ስለራሴ ብዙ ባልናገር እመርጣለሁ፤ ስለኔ ማወቅ የፈለገ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ የቤልጂየም፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን ዩኒቨርሲቲዎችን ጠይቆ መረዳት ይችላል” ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የዶክትሬት ማዕረጋቸውን የኢትዮጵያ ባንዲራ ተሠቅሎ፣ በታላቅ ክብር እንደተቀበሉ አስታውሰው፣ በአውሮፓ ተጋባዥ ፕሮፌሰር መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን ካለፉት 8 አመታት ጀምሮ እየመሩ የሚገኙት ፕሮፌሰር መርጋ፤ ቦርዱን የመምራት ሙሉ ብቃት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ፕ/ር መርጋ ከምክትላቸው ዶ/ር    አዲሱ ገ/እግዚአብሔር ጋር በመሆን በእለቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ከየትኛውም በምርጫው የተወዳደረ ፓርቲ ምርጫውን የተመለከተ አቤቱታ አለመቅረቡን ጠቁመው፣ ፓርቲዎች ያላቸውን ቅሬታ በህጉ መሠረት ለቦርዱ ማቅረብ ሲገባቸው በየሚዲያው የምርጫውን ገጽታ በሚያበላሽ መልኩ መግለጫ መስጠታቸው ከህግ ውጭ ነው ሲሉ አውግዘዋል፡፡
ፓርቲዎች የምርጫ ውጤቱን አንቀበልም ማለታቸው የመራጩን ህዝብ ድምጽ ያለማክበር ነው ያሉት አመራሮቹ፤ ለታዛቢዎች፣ ለምርጫ አስፈፃሚዎችና ለአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን ድካምም ክብርና እውቅና ያለመስጠት ነው ብለዋል፡፡
“ምርጫው የተረጋጋና አሣታፊ ነበር” ያሉት የቦርዱ አመራሮች፤ በምርጫው እለትም ሆነ በቆጠራው ላይ ምንም አይነት ቅሬታ ለቦርዱ ያላቀረቡ አንዳንድ ፓርቲዎች ጊዜያዊ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ምርጫው እንደተጭብረበረና ጉድለቶች እንደነበሩ በማስመሰል የስም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
“በነቂስ ወጥቶ በምርጫው የተሣተፈው ህዝብ መከበር አለበት፣ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች መከበር አለባቸው፣ የህዝብ ታዛቢዎች፣ ምርጫ አስፈፃሚዎች እና የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች መከበር ይገባቸዋል  ብለዋል” የቦርዱ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና፡፡
ኢህአዴግ መቶ በመቶ አሸንፏል የሚለው አገላለፅ ተገቢ አይደለም ያሉት የቦርዱ አመራሮች፤ ኢህአዴግ ከ547 የምክር ቤት መቀመጫ በ501 ብቻ ነው የተወዳደረው፤ በሌሎቹ መቀመጫዎች ስላልተወዳደረ መቶ በመቶ አሸንፏል አይባልም - ብለዋል፡፡
በአካባቢው በተፈጠረ የደጋፊዎች አለመግባባት ተራዝሞ የነበረው በደቡብ ክልል በቦንጋ ዞን ገዋታ ጊምቦ የምርጫ ክልል ምርጫ፤ በቀጣዩ ሳምንት ሰኔ 7 እንዲካሄድ መወሰኑን ቦርዱ አስታውቆ፤ በአካባቢው የሚወዳደሩ ፓርቲዎችም የምረጡኝ ቅስቀሳ በሠላም እያካሄዱ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በዚህ የምርጫ ክልል በ2002 ምርጫ ብቸኛው የግል ተወዳዳሪ ሆነው ፓርላማ የገቡት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፤ በድጋሚ በግል እንደሚወዳደሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

Read 5601 times