Saturday, 06 June 2015 14:23

የዕብደት ዋዜማ

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(12 votes)

 “ተራሮች ጫፍ ላይ ጸጥታ ሰፍኗል”  ዛፎች ሁሉ ረጭ ብለዋል፡፡ አዕዋፍ በዛፎቹ ላይ አሸልበዋል - ጠብቅ! አንተም አንድ ቀን እንዲህ ጸጥ ትላለህ!!!” የሚል የት እንዳነበብኩት የማላስታውሰው ጥቅስ በተደጋጋሚ በእዝነ ህሊናዬ አስተጋባ፡፡
“ጸጥ ትላለህ” ምን ማለት ነው?
በዚህ ስገረም ይባስ ብሎ፣ ከእንቅልፌ በነቃሁበት ቅጽበት “ዛሬ ትሞታለህ” የሚል ጥርት ያለ ድምጽ በጆሮዬ ሰማሁ፡፡ ማነው ሹክ ያለኝ? ሰይጣን ወይስ መላእክት? የዕብደት ዋዜማ ላይ ነኝ ልበል፡፡
ስለ አይቀሬው ጥቁር እንግዳዬ ሞት ማውጠንጠን ጀመርኩ…፡፡ ሞት!!
የሞት መንገደኞች ነን፡፡ ዝንተ ዓለም የሰው ልጅ የተመላለሰበት ማለቂያ የሌለው መንገድ፡፡ ወትሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው እንዲሉ… ሞት የተራ ጉዳይ ነው፡፡ መንትዮች እንኳን ተራ በተራ አይደል የሚወለዱት! የባለ ቅኔው ጆን ዶን ግጥም ትዝ አለኝ….
No man is Island entire of it self
Every man is a piece of continent
A part of the main
And therefore never sent to know
For whom the bell tolls….
ቀጣዩ ደወል የሚደውለው ለማን ነው? የሞት ደወል የሚደወለው ….
“ላንተ! ላንተ ነዋ!”… ጥርት ባለ ድምጽ አይምሮዬ ላይ አቃጨለ፡፡ ተርበተበትኩ፡፡ የመኖር ጥማት ውስጤ ተላወሰ፡፡ ህይወት፡፡… ህይወትማ በምድር ላይ ለሚታይ ትርኢት የመግቢያ ትኬት ናት። ትርኢቱን በቀጥታ ስርጭት እነ አልጄዚራ፣ ሲኤንኤን…ፕሬስ ቲቪ በየደቂቃው ያሳዩናል፡፡ ምድር ዛሬ ተነስቶ ሲያንቀጠቅጣት - ሆድ ብሷት እሳተ ጎመራዋን ስታስመልስ -  እንደጧፍ ቦግ ብላ ስትነድ።….
እንደ ምጽአት ቀን ውርጅብኝ ሁሉም ነገር ሲደበላለቅ! ብው! ድም!  ዶግ አመድ! ወይ ዓለም! - የራሷ ጉዳይ ድራሽ አባቷ ይጥፋ!! …. የዕብደት ዋዜማ ላይ ነኝ ልበል፡፡ እንዲህ ቦግና ዕልም፣ ብልጭና ድርግም የሚሉ አሳቦች ጭንቅላቴ ውስጥ መፈንዳት ጀመሩ፡፡ ለማንኛውም የዛሬው ውሎዬ ህይወቴን ለማዳን በሚደረግ ጥንቃቄ ያልፋል፡፡
ከቤት መውጣት የለብኝም - በየመንገዱ በሀሳብ ስናውዝ አንዱ ከላባ ሲኖትራከር ቢጨልቀኝስ? ከዚህ ሁሉ ቤት መሰብሰቡ ይሻላል። ክፍሌ አስተማማኝ ናት ደራሲውን በድንገተኛ ርዕደ መሬት ዶግ አመድ ካልሆነች …. አልያም መብረቅ ወርዶ ሁለት ቦታ ካልተሰነጠቀች በቀር በቤቴ ውስጥ ለህይወቴ የሚያሰጋኝ አንዳች ነገር የለም፡፡ አልጋዬ ላይ ተጋደምኩ፡፡ የተገረዝኩበት አልጋ ነው፡፡ በዛሬው እለት ይህችን ምድር የምሰናበት ከሆነም እገነዝበት ይሆናል፡፡ “በተገረዝክበት አልጋ ትገነዝበታለህ” የሚለው በኔ ይደርስ ይሆን፡፡ የሩሲያ ደራሲውን የሚካኤል ሌርሞንቶቭ ልብወለድ ማንበብ ጀመርኩ… አንዱ ገጸ ባህሪ … “በአንድ ውብ ማለዳ በሞት እለያለሁ፤ ምክንያቱም በአንድ በተረገመ ሌሊት ወደዚህ ዓለም በመምጣቴ ….”
የራሴ ህልፈት ትዝ ብሎኝ መጽሐፉን ዘጋሁት። ምን ማለቱ ነው? የተረገመ ሌሊት… የተወለደበት ወይስ የተጸነሰበት?
ቀኑን ሙሉ “ሞት ሆይ መውጊያህ የታል” በሚል ስቁለጨለጭ ዋልኩ ….
ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ወጣ በል፤ ትንሽ ቀማምስ የሚል ሀሳብ መጣልኝ፡፡ አንድ ሁለት ብዬ መለስ ብልስ -ብዙም ሳርቅ፡፡ ቡና ቤት ገባሁ - ወደ ፈንጅ ወረዳ! በሰላም እወጣ ይሆን ከነሕይወቴ፡፡ ድራፍት አዘዝኩ፡፡ ላጥ አድርጌ ሌላ ደገምኩ… ጆሮዬ ድምጽ መስማት ጀመረ …
“የህልም እንጀራህን እዛው”
“የህልም እንጀራህን ብሎ ነገር የለም - በህልም አብሲት ሳይጣል …”
“ለሚቀጥለው ምርጫ መቀናጀት ብቻ ሳይሆን - መቆራኘት ነው - ለምርጫ 2017”
“ለምርጫ 2017 ወይስ 2077 … ኢሂሂ … ቂቂቂ….”
እያለ የሚገለፍጠው ላይ አይኔ አረፈ፡፡ እዚህ ቤት ሳምንት ሙሉ አይጠፋም፡፡ የአንዳንድ ሰው ሳምንት ሰባት ቅዳሜዎችን የያዘ ነው ልበል፡፡ ሁሌም ከበር ቻቻ፡፡
“የቡና ቤቷ ባለቤት እየተንጎማለሉ ገቡ፡፡ ወደኔ እያመለከቱ ለአስተናጋጁ የሆነ ነገር ሹክ አሉት፡፡
‹ለምን ለዚህ ቀውስ  ወፈፌ ቀዳህለት” እንደሚሉት እርግጠኛ ነበርኩ …
“ድራፍት” ስል አዘዝኩ፡፡
“የለም” ሲል መለሰልኝ፡፡
ውስጤ ተናወጠ፡፡ እልህ ያዘኝ፡፡ ብርጭቆ ላይ የቀረውን ጭላጭ ድራፍት አስተናጋጁ ፊት ላይ ደፋሁበት፡፡ የድራፍቱን ብርጭቆ ከጭንቅላቴ ጋር ቴስታ አጋጠመው … ተፈተንኩ … ቢሆንም ለሞት የሚያበቃ የከፋ አደጋ አልደረሰብኝም… ብርጭቆውም ሆነ ጭንቅላቴ አንዳቸውም አልተሸረፉም፡፡
ቤት ደረስኩ - ምስሌን ለማየት መስታወቱ ላይ አፈጠጥኩ - የለሁም፡፡ አይኔን በድንጋጤ ጎልጉዬ መስታወቱ ላይ ደገሜ አፈጠጥኩ። የለሁም፡፡ ታዲያ የት አለሁ? በቁሜ አልጋዬ ላይ ወደቅኩ፡፡ ወደ እንቅልፍ ይሁን ወደ ሞት ዓለም በስሱ እየተጓዝኩ ነው፡፡ የሬዲዮ ድምጽ ይሰማኛል፡፡ በእውን ይሁን በሰመመን …. በቅዠት … የጋዜጠኛው ድምጽ ቅድም ቡና ቤት ውስጥ ምርጫ 2017 … 2077 እያለ በፍልጥ ጥርሱ ሲገለፍጥ ከነበረው ድምጽ ጋር ተመሳሳይ ነበረ፡፡
“በምርጫ 2017 በክልል 99 የተወዳደረው ፓርቲ፤ አብላጫ የክልሉን ም/ቤት መቀመጫ በማግኘት ማሸነፉ ይታወቃል፡፡ ይህ በተቃዋሚ ፓርቲ ደረጃ የመጀመሪያው ነው፡፡ የክልል 99 ፕሬዚዳንት የካቢኔ አባላት ሹመትን በተመለከተ FM 99.9 በቀጥታ ያስተላልፍላችኋል … የፕሬዚዳንቱ ሙሉ ቃል እነሆ ….
“… ክቡራን …. ፓርቲያችን አሸንፎ  ለዚህ ድል በመብቃቱ የተሰማኝን ደስታ በመግለፅ… ወደ ሹመት ዲስኩሬ እገባለሁ፡፡ በመጀመሪያ የክልሉ ኢንዱስትሪ ኃላፊ ሹመትን በተመለከተ … በክልላችን የምናገኘው የጎጆ ኢንዱስትሪ ነው። ብቸኛ የጎጆ ኢንዱስቱሪ ተረፈ ምርት የሀበሻ አረቄ ወይም ቁንድፍቱ መሆኗን ሁላችንም የምናውቀው ሀቅ ነው፡፡ ለዚህ ኃላፊነት ይገባኛል የሚል በግል ያነጋግረኝ፡፡ ያለበዚያ በአረቄ ምርት አቅራቢነታቸው በክልሉ ዝናን ያተረፉትን ወ/ሮ ደብሪቱን የምንሾምበት ምክንያት የለም - ስራ ለሰሪው … በመቀጠል የከተማ ልማት ሹመትን አቀርባለሁ … የክልል 99 መዲና እንኮዬ አርጅታ … ዝጋ… የጉስቁልና ሕይወቷን እየገፋች ነው። እንደ መንግስተ ሰማያት በር የጠበቡ መንገዶቿ የትም አይደርሱም፡፡
ጉሮሮዋ ታንቆ የጣር ሕይወት እየገፋች ነው - የቀባሪ ማጣት ካልሆነ በቀር … የተባበሩት መንግስታት ‹ግጭት አስወጋጅ›፣ ‹ድህነት ቅነሳ›…. ኮሚሽኖቹ እንዳሉት ሁሉ የሞቱትን ከተማ ቀባሪ ኮሚሽን ቢኖረው ስል እመኛለሁ … የኛዋ እንኮዬ የዚህ እድል የመጀመሪያ ተጠቃሚ ሆና እፎይ ትል ነበር … ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል እያለች … የከተማ ልማት ኃላፊ ሹመት ከላይ የገለጽኩት ያማከለ መሆን አለበት፡፡ ለቦታው የሚጠይቀው መስፈርት ቢበዛ የዕድር ዳኛ፣ ቢያንስ የድር ጥሩንባ ነፊ …. ንግግራችን በሞተችዋ እንኮዬ ላይ በመሆኑ ….
… የክልሉ ሴቶች ጉዳይ ተጠሪን በተመለከተ … እንደሚታውቀው በዚህ ምክር ቤት አንድም እንስት የለችም … ያሳዝናል … ፓርቲያችን ጉሮሯችን እስኪደርቅ - ላንቃችን እስኪሰነጠቅ “ሔዋን ሆይ ለክልል ም/ቤት ተወዳዳሪ” አልን … ግን ማን ሰምቶን? ጩኸታችን እንደ መጥምቁ ዮሐንስ የምድረ በዳ ጩኸት ሆኖ ቀረ … በመሆኑም አንድም እንስት በዚህ ም/ቤት የለችም። ማንን ኃላፊነት ላይ ላስቀምጥ በሚል የአይምሮዬን መዝገብ ሳላገላብጥ ገጽ አንድ ላይ አቶ ማዕረጉን አገኘሁ። ማዕረጉ ከወንዳወንድነቱ ሴታሴትነቱ ያመዝናል፡፡ መቅለስለሱ መሽኮርመሙ፣ ለስላሴ ተፈጥሮው የሄዋንን ውብ ጸጋ ጥዑም ለዛ አላብሶታል፡፡
ተነሳሽነቱ… ጽኑ ፍላጎት ካለው ከክልሉ በጀት ወጪ በማድረግ ፣ ለሙሉ የፆታ ለውጥ ለህክምና ወደ ውጭ ለመላክ ፍላጎቴን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ … በዚህ ንግግሬ አቶ ማዕረጉ ቅር እንደማይለው ዕምነቴ ነው፡፡ ምክንያቱም በልማትና በለውጥ ስለሚያምን - ፆታዊ ለውጥ ቢሆንም

Read 3934 times